ዜና

“ኢሕአዴግ በሁለት ክንፎች ተከፍሏል”

Views: 337

ህወሓት እና በውህደት ብልጽግና ፓርቲ የተሰኘው ኢህአዴግ፣ በመካከላቸው ያለውን ጭቅጭቅ እና ልዩነት ወደ ሀገሪቱ በማምጣት ኢትዮጵያን ወደ አልተፈለገ አለመረጋጋት እና ግጭት እንዳያስገቧት፣ ሁለቱም ወገኖች በጥንቃቄ ሊያስቡበት ይገባል ሲሉ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረንስ (ኦፌኮ)  ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ተናገሩ፡፡

ፕሮፌሰር መረራ ትላንት ህዳር 15 ቀን 2012 ዓ.ም የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ አስመልክተው ለኢትዮ-ኦንላይን እንደተናገሩት ኢሕአዴግ በሁለት ክንፎች ተከፍሏል፡፡

አንደኛው  ክንፍ ውህደት ፈጽሜያለሁ ይላል፤ ሌላኛው ክንፍ ደግሞ ውህደት አልተፈጠረም፤ እንደውም በኢህአዴግ የፖሊሲና የፖለቲካ አመለካከት ላይ ክህደት ተፈጽሟል የሚል ሀሳብ ይዞ መግለጫ ሰጥቷል፡፡  ስለዚህ፣ በእኔ አተያይ ኢሕአዴጎች እርስ በእርሳቸው እየተወዛገቡ ነው ያሉት- ብለዋል፡፡

ኢሕአዴግን የፈጠርኩት እኔ ነኝ የሚለው ህወሓት፣ ኢህአዴግ ከድቶኛል እያለ ነው፤ በኢህአዴግ ውስጥ የነበሩ ሌሎች አጋር ፓርቲዎች ደግሞ ድሮ በህወሓት ተተብትቦ የተያዘውን ኢሕአዴግን እየለወጥነው ነው ያለነው እያሉ ነው፡፡

ከነዚህ የተለያዩ ሀሳቦች ተነስተን ስናይ፣ የኢህአዴግ ውህደት በተፈለገው መንገድ በአንድነትና በስምምነት የተደረገ እንዳልሆነ ማወቅ እንችላለን ሲሉ ፕሮፌሰር መረራ ለኢትዮ ኦንላይን ዘጋቢ አብራርተዋል፡፡

የተዋሃደው ኢሕአዴግ ገዢ ለመሆን የሕግም፣ የሞራልም ልዕልና የለውም ብሎ ህወሓት የዚህን ድርጅት ውሳኔዎች አልቀበልም ካለ፣ በተለይም በመንግሥት ደረጃ እስከ ምርጫው ድረስ ውህዱ ፓርቲ የሚወስናቸውን እና የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎች ለመቀበል ከተቸገረ፤ ያን ጊዜ ወደ አላስፈላጊ ፍጥጫ ከገዢው ፓርቲ ጋር ሊገቡ ይችላሉ፡፡

ይህን ፍጥጫ እንዴት በአግባቡ ይይዙታል የሚለው ገና መልክ ያልያዘ ጉዳይ ነው ብለዋል ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com