ዜና

“በመዳ ወላቡና በኦዳ ቡልቱ ዩንቨርስቲዎች ብቻ ነው ትምህርት ያልተጀመረው” ሲል ሚ/ሩ ገለጸ

Views: 220

ከመዳ ወላቡ እና ኦዳ ቡልቱ ዩንቨርስቲዎች በስተቀር፣ ሁሉም ዩንቨርስቲዎች ወደ መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደታቸው እንደገቡ፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር አስታወቀ፡፡

በሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ወጥ የሆነ የትምህርት ጅማሮ የሌለበትን ምክንያት በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ደጃሳ ጉርሞ ለኢትዮ-ኦንላይን እንዳብራሩት በዩንቨርስቲዎቹ የተጋጩ ተማሪዎችን ለማስታረቅ እና አስማምቶ ወደ አንድ የማምጣቱ ሂደት ትንሽ ጊዜ ስለወሰደ ነው ትምህርት እስከ አሁን ያልተጀመረው ብለዋል፡፡

በሀረማያ ዩንቨርስቲ እስካሁን ትምህርት አልተጀመረም የሚባለው ትክክለኛ መረጃ እንዳልሆነ እና ከተማሪዎች ተንጠባጥቦ ወደ ትምህርት ገበታ ከመምጣት ውጭ መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንደሌሎች ዩንቨርስቲዎች ሁሉ በሀረማያም እንደተጀመረ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ ባለው ሀገራዊ ሁኔታ ምክንያት፣ ተማሪዎች ለጊዜው ትምህርት የማቋረጥ ‹‹ዊዝድሮዋል›› ቅጽ እንዳይሞሉ መከልከላቸው፣ ጉዳት እየደረሰባችሁም ቢሆን ትምህርታችሁን ቀጥሉ ማለት አይሆንም ወይ በሚል ከኢትዮ-ኦንላይን ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ከዚህ በፊት ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ ተማሪዎች በማህበራዊና ግላዊ ጉዳያቸው ምክንያት ‹‹ዊዝድሮ›› ቅጽ ሞልተው ይጠይቃሉ፤ ዩንቨርስቲውም ጉዳያቸውን ከመረመረ በኋላ ይፈቅዳል፡፡

ያሁኑ ግን ለየት ባለ መልኩ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ‹‹ዊዝድሮዋል›› ለመሙላት ጠይቀዋል፤ ይህ ደግሞ ፈጽሞ የማይፈቀድ ነገር ነው፤ የአንድ ዩንቨርስቲ ከሀምሳ በመቶ በላይ ተማሪዎቹ ግቢውን ለቀውት ከወጡ፣ የመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ስለሚኖረው ክልከላ አድርገናል ብለዋል፡፡

ተማሪዎችም ‹‹ዊዝድሮ›› ቅጽ ከመሙላት ይልቅ፣ ከዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ጋር በመሆን ራሳቸውና የግቢያቸውን ሠላም ለማስጠበቅ መስራት ይኖርባቸዋል እንጂ፣ ከአንድ ዩኒቨርሲቲ ወደ ሌላ ዩኒቨርሲቲ በመዘዋወርና ‹‹ዊዝድሮ›› በመሙላት ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት አይቻልም ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለያዩ ዩንቨርስቲዎች አካባቢ በመገኘት ወደ ሌላ ዩንቨርስቲ እንድትዘዋወሩ እናመቻቻለን እያሉ ተማሪዎች ዩንቨርስቲያቸውን ለቀው እንዲወጡ የሚያነሳሱና ምዝገባ የሚያካሂዱ አካላት እንዳሉ ተደርሶበታል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ተማሪዎችም ሆኑ የተማሪ ወላጆች በዚህ አይነት የተሳሳተ መረጃ እንዳይጭበረበሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com