ዜና

በቦሌ ሚካኤል “ቄሮ” ነን ያሉ ቡድኖች እና የአካባቢው ወጣቶች ተጋጩ

Views: 298

በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ቦሌ ሚካኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ትላንት ኅዳር 15 ቀን 2012 ዓ.ም በአካባቢው ወጣቶችና እራሳቸውን “ቄሮ” ብለው በሚጠሩ ቡድኖች መካከል ግጭት መፈጠሩን የኢትዮ ኦንላይን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ትላንት ማምሻውን ቦሌ ሚካኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች በየዓመቱ ኅዳር 12 ቀን የሚነግሰውን የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ክብረ በዓልን ለማክበር ከዋዜማው ዕለት ጀምሮ የሰቀሉትን ሠንደቅ ዓላማ፣ እራሳቸውን “ቄሮ” ብለው የሚጠሩ ቡድኖች ሊያወርዱት ሲሞክሩ በአካባቢው ወጣቶችና በቄሮዎቹ መካከል ግጭት መፈጠሩን የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡

የተፈጠረውን ግጭት የፌደራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ፖሊስ በጋራ በመሆን መቆጣጠር እንደቻሉ እና ችግሩን ለመቆጣጠርም መሳሪያ እንደተኮሱ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች በተተኮሰው ጥይት አንድ ሰው ሕይወቱ እንዳለፈና ሁለት ሰዎች እንደቆሰሉ ለኢትዮ ኦንላይን ዘጋቢ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን፣ የሰዎች ሕይወት ይለፍ አይለፍ ከፖሊስ የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡

በግርግሩ ተሳታፊ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ወጣቶች በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደዋሉ እና አካባቢውም በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደዋለ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

ሆኖም፣ በአንድ አንድ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ግጭቱ ቤተክርስቲያን ለማቃጠል ተብሎ የተደረገ እንደሆነ የሚወራው ሀሰት እንደሆነ እና ግጭቱ የተነሳው በሠንደቅ ዓላማ አውርዱ አናወርድም በሚል አለመግባባት እንደሆነ የመረጃ ምንጮቻችን አብራርተዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com