ዜና

ህወሓት በውህደቱ ጉዳይ ለሁለት መከፈሉ ተገለጸ

Views: 445

‹‹ህወሓት በውህደት ጉዳይ እየዋዠቀ ነው›› አቶ አብርሃ ደስታ

በኢሕአዴግ የውህደት ጉዳይ፣ የህወሓት ከፍተኛ የአመራር አባላት በሁለት ቡድን መከፈሉን ከፓርቲው ከፍተኛ ኃላፊዎችና ከክልሉ መንግሥት ባለሥልጣናት አካባቢ የሚወጡ መረጃዎች አመላከቱ፡፡

ሁለቱ ቡድኖች በዶክተር ደብረፅዩን ገብረ ሚካኤልና በአቶ ስብሃት ነጋ የሚመሩ መሆናቸውን ነው የተጠቆመው፡፡

ኢትዮ-ኦንላይን በስልክ ያነጋገራቸው የህወሓት የቅርብ ሰዎች እንደገለፁት፣ በአንጋፋው የህወሓት መሥራች አቶ ስብሃት ነጋ የሚመራው ቡድን፣ ህወሓት የብልፅግና ፓርቲ አባል ሆኖ እንዳይዋሃድ አቋም ይዟል፡፡

ይህ ቡድን በውስጡ አቶ ስዩም መስፍን፣ አቶ አባይ ፀሃዬ እና ሌሎችን ጉምቱ የህወሓት አመራሮችን ያቀፈ ነው ብለዋል፡፡

በአንፃሩ በዶክተር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው ቡድን ህወሓት ከኢሕአዴግ ጋር እንዲዋሃድና የብልፅግና ፓርቲ አባል ሆኖ እንዲቀጥል አቋም ይዟል፡፡

በውስጡም አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ሌሎች ወጣት አመራሮችን ያቀፈ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡

በእነ አቶ ስብሃት ነጋ የሚመራው ቡድን ትግራይን ከኢትዮጵያ የመገንጠል ሃሳብ አለው፤ በአሁኑ ወቅትም ወጣቶቹን ለጦርነት እያሰለጠነ ነው ብለዋል፡፡

በሌላም በኩል የትግራይ ሕዝብ ወደ ጦርነት ለመግባት ፍላጎት የለውም ሲሉ ለዘጋቢያችን የገለጹት የተንቤን አካባቢ ነዋሪዎች፣ አንጋፋ የህወሓት የአመራር አባላት ድጋፍ ያላቸው በአድዋ አካባቢ ብቻ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡

ምክንያቱ ደግሞ 95 ከመቶ የህወሓት የአመራር አባላት የአድዋ ሰዎች ስለሆኑ ነው ያሉት የተንቤን ነዋሪ፣ የተንቤን ሕዝብ በእዚህ የአመራር አባላት በተደጋጋሚ የተገለለ ሆኗል ይላሉ፡፡

ህወሓት ከዚህ በፊት ከኢህአዴግ ጋር እንደማይዋሃድ በይፋ ቢገልፅም፣ ስለውህደቱ ጉዳይ እንደገና ለመወሰን ደግሞ አስቸኳይ ጉባዔ ጠርቷል፡፡ ይህም ህወሓት እየዋዠቀ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ የገለጹት ደግሞ የዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ ናቸው፡፡

ህወሓት በጉዳዩ ላይ በሰጠው መግለጫ ‹‹ኢሕአዴግ እንዲዋሃድ ሀዋሳ ላይ በተካሄደው ጉባዔ በሙሉ ድምፅ ደግፌያለሁ፡፡ በዚያን ጊዜ የተነጋገርነው የፖለቲካ ፕሮግራሞቹ እና ርዕዮተ ዓለሙ ሳይቀየር እንደሚዋሀድ ነው፡፡

አሁን የሆነው ግን ውህደት አይደለም፤ አዲስ ፓርቲ ነው እየተመሰረተ ያለው፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ከውስጡ አስወግዷል፤ ስለዚህ አልዋሀድም፡፡›› ብሏል፡፡

‹‹ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው እንደማይዋሀድ ከገለፀ በኋላ፣ በዛሬው እለት ስለውህደቱ ለመወሰን አስቸኳይ ጉባዔ መጥራት አያስፈልግም ነበር›› ያሉት አቶ አብርሃ ደስታ፣ ይህም የሀወሓትን የአቋም መዋዠቅ የሚያሳይ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com