ዜና

ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የሞከሩ ተማሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

Views: 298
  • በመኪና ተጭነው ከጊቢው እንዲወጡ ተደርገዋል

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ (ዋናው ጊቢ) ወደ ሰላማዊ ሰልፍ ሊያመራ የነበረ የተማሪዎች እንቅስቃሴ፣ በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋለ፡፡ ሠልፉ ተካሂዶ ቢሆን ኖሮ በፍጥነት ወደ ግርግርና ግጭት ሊያመራ ይችል እንደነበር መረጃ የነበራቸው የጊቢው ፖሊሶች፣ ለፌዴራል ፖሊስ ጥሪ ማቅረባቸውን ለኢትዮ-ኦንላይን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ማዕከሉን ያደረገው የተማሪዎች የሰልፍ እንቅስቃሴ፣ በአራት ኪሎ እና አምስት ኪሎ ካምፓሶችም ከትላንት ማምሻውን ጀምሮ በተማሪዎች የእርስ በእርስ ግንኙነትና በማኅበራዊ የትሥሥር ገፆች ውስጥ ለውስጥ ጥሪ ሲተላለፍ እንደነበር ተማሪዎች ለኢትዮ-ኦንላይ ገልጸዋል፡፡

ይህ ጥሪ፣ ሌሎች ተማሪዎች በሠላማዊ ኹኔታ በትምህርት ገበታ ላይ እንዳይቀመጡ የሚያዝ ሲሆን፣ በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ለሚደርስባቸው ጉዳት ራሳቸው ኃላፊነት እንዲወስዱ ያስጠነቅቃል፡፡

በዚህም ሳቢያም በዛሬው ዕለት መደበኛ የስድስት ኪሎ ተማሪዎች ወደ ክፍል ገብተው ለመማር በመፍራት በዶርማቸውና በቤተመጻሕት ተጠልለው ለማሳለፍ ሞክረዋል ሲሉ ለዘጋቢያችን የገለጹት ደግሞ በዋናው ጊቢ የማኅበራዊ ሳይንስ መምህር ናቸው፡፡

ዩንቨርስቲው ግቢ ውስጥ የነበሩት ተማሪዎች “ግቢው በፌዴራል ፖሊስ ተከቦ ስናየው ከፍተኛ ድንጋጤ ነው የጫረብን ነገር ግን፣ ፖሊስ የግቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ብሎ እንደገባ ስንገነዘብ ለመረጋጋት ችለናል” ብለዋል፡፡

ጠዋት ላይ ተማሪዎች ከክፍል ተወካዮቻቸው ጋር ተወያይተው እንዳበቁ፣ ‹‹በሥጋትና በጭንቀት ውስጥ ሆነን ማጥናት ስላልቻልን በመርሃ-ግብሩ መሠረት በዚህ ሳምንት የሚፈተኑትን ፈተና እንዳራዝምላቸው ተማጽነውኛል›› ሲሉ መምህሩ ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም፣ በዛሬው ዕለት ረፋዱ ላይ የተሰባሰቡ ተማሪዎች፣ ‹‹ሐሙስ ኅዳር 11 ቀን 2012 ዓ.ም ሰልፍ ሊያካሂዱ ሲሉ የተያዙ ተማሪዎች ይለቀቁ›› የሚሉ መፈክሮችን ለማስደመጥና የጊቢውን የዕለት ተዕለት የሥራ እንቅስቃሴ ሊያውኩ ሞክረዋል ሲሉ የነገሩን ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ክፍል ሠራተኛ ናቸው፡፡

ዛሬ እኩለ ቀን ላይ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ሁለተኛው በር አቅራቢያ ሰልፍ ለማድረግ ተማሪዎችን ሲያውኩ በፌዴራል ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተማሪዎች ባሉበት እንዲቀመጡ ተደርገው ከፌዴራል ፖሊስ ጋር የተወያዩ ሲሆን፣ ወደ 7፡10 ሰዓት ላይ በጭነት መኪና ከዩኒቨርሲቲው ተጭነው እንዲወጡ መደረጋቸውን በሥፍራው የነበረችው ዘጋቢያችን ተመልክታለች፡፡ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድርስ ወደ የት አካባቢ እንደተወሰዱ ለማረጋገጥ አልቻልንም፡፡

በግቢው ውስጥ የነበሩ አብዛኛዋቹ የፌደራል ፖሊስ አባላትና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ተማሪዎቹ በመኪና ተጭነው ከወጡ በኋላ፣ እነሱም በመኪናቸው በመሆን ከግቢው ወጥተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በእንግሊዘኛ የትምህርት መስክ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑት አቶ ጌትነት ጥበቡ ለኢትዮ ኦንላይን እንደተናገሩት፣ በዩንቨርስቲው ባለፈው ሳምንት ከተከሰተው ግርግር በኋላ ምንም አይነት የጎላ ችግር እንዳልገጠመ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜም በዩንቨርስቲው ቅጥር ግቢ ውስጥም ሆነ በአካባቢው ቁጥራቸው በርከት ያሉ የፌደራል ፖሊስ አባላት እንደሚገኙና የዩንቨርስቲውን የጸጥታ ሁኔታ በአትኩሮት እየተከታተሉት እንደሆነ አቶ ጌትነት ጠቁመዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com