ዜና

የሁለት ታዋቂዋን የፍርድ ቤት ውሎ

Views: 2349

ኤፍሬም ታምሩ እና ሚኪያስ መሀመድ

ድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩ በ1977 ዓ.ም. ባሳተመው የካሴት ዘፈን ውስጥ ‹‹የቀይ ዳማ›› ወይም ‹‹የድንገት እንግዳ›› የሚል ርዕስ ያለውን ዘፈን ደራሲ የአቶ ማስረሻ ሽፈራውን ወራሾች ሳያስፈቅድ፣ እንደ አዲስ ሙዚቃዎቹን በማቀናበር በ2007 ዓ.ም. በድጋሚ አሳትሞ ለሕዝብ አሠራጭቷል በሚል የተከሰሰ ሲሆን፣ ጉዳይ ለሰበር ሰሚ ችሎት ደርሷል፡፡

ከሳሽ የአቶ ማስረሻ ሽፈራውን ወራሽ የሆኑት፣ ወ/ሮ ቤተልሔም ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት ክስ እንዳስረዱት፣ አባታቸው አቶ ማስረሻ የ‹‹ቀይ ዳማ›› ዘፈን ብቸኛ ደራሲ ናቸው፡፡

አባታቸው ጥቅምት 19 ቀን 1994 ዓ.ም. አርፈው በማግሥቱ ጥቅምት 20 ቀን 1994 ዓ.ም. ሥርዓተ ቀብራቸው መፈጸሙን፣ እሳቸውም ወራሽ ስለመሆናቸው የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 4239/07 ውሳኔ ማረጋገጡን ለፍርድ ቤቱ አሳውቀዋል፡፡

የአባታቸውን ድርሰት ያለሳቸው ፈቃድ ድምፃዊው በሙዚቃ አቀናብሮና አሳትሞ በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾችና ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች በማሠራጨት፣ የጥቅምና የሞራል ጉዳት እንዳደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ድምፃዊው ዓዋጆቹን በመተላለፍ ያሳተመው ቅጅ እንዲታገድ፣ ፈቃድ ቢጠይቃቸው ኖሮ ሊያገኙ ይችሉ የነበረውን 30,000 ብር፣ እንዲሁም ለደረሰባቸው የሞራል ጉዳት ካሳ ደግሞ 140,000 ብር እንዲከፍላቸው እንዲወሰንላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀው ነበር፡፡

ተከሳሽ ድምፃዊ ኤፍሬም በበኩሉ ባቀረበው መከራከሪያ እንዳስረዳው፣ ሟች አቶ ማስረሻ በ1977 ዓ.ም ዜማውን ያስተላለፉለት ያለ ጽሑፍ ነው፡፡ የዜማው ደራሲ ራሱ እንጂ ሟች ወይም ወ/ሮ ቤተልሔም አይደሉም፡፡

መብቱም የተላለፉለት የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ዓዋጅ ቁጥር 410/96 ከመውጣቱ በፊት ነው፡፡ በመሆኑም፣ ተፈጻሚነት ያለው በፍትሐ ብሔር ሕጉ ላይ የሚገኙት የቅጅና ተዛማጅ መብቶችን የሚመለከቱት ድንጋጌዎች እንጂ፣ ዓዋጁ አለመሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

የዜማው ደራሲ ራሱ ኤፍሬም ታምሩ እንጂ ከሳሽ ካለመሆናቸውም በላይ፣ በዓዋጁ አንቀጽ 7(3) ላይም ‹የአንድ ሥራ አመንጪ የሆነ ሰው ሥራውን ለሌላ ሰው ካስተላለፈ በኋላ ከሚደረገው ድጋሚ ሽያጭ ዋጋ ውስጥ የተወሰነው ድርሻ ለሥራ አመንጪው፣ ወይም ለወራሹ የካሳ ጥያቄ ማቅረብ ተቀባይነት የለውም፤›› በማለትም ድምፃዊው ተከራክሯል፡፡

ኤፍሬምም ከሳሽ እንጂ ተከሳሽ አለመሆኑን ገልል፡፡ በተጨማሪም ዘፈኑ በድጋሚ በመሰራቱ ምንም ያስገኘው ጥቅም ሳይኖር የቀረበ የካሳ ጥያቄ በመሆኑ ዘፈኑም በተለያዩ ማሕበራዊ ድረገጾች እና ኤፍኤም ራዲዎች የተሰራጨ ነው እንጂ እኔ ያሰራጨሁት አይደለም ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በበኩሉ የግራ ቀኝ ክርክር እና ማስረጃ ተመልከቶ ስለጉዳዩ ተጨማሪ ማጣሪያ አድርጎ ተከሳሽ ያለ ከሳሽ ፈቃድ ዘፈኑን ለሕዝብ እንዲደርስ በማድረጉ የከሳሽ ፈቃድ ቢጠየቅ ኖሮ ለከሳሽ ይከፍል የነበረ ገንዘብ 8 ሺህ ነው ብሎ በመወሰን እንዲሁም የሞራል ካሳ 100 ሺህ ብር እንዲከፍል ወስኗል፡፡108 ሺህ እንዲከፍል ቢወስንም፣ ኤፍሬም ታምሩም በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤት ብሏል፡፡

ጉዳዩ የቀረበለት ጠቅላይ ፍርድቤት፣ ያስቀርባል አያስቀርብ የሚለውን ጉዳይ መርመሮ- ያስቀርባል ብሏል፡፡ በመሆኑም የእስር ፍርድ ቤት ጉዳዩን መርምሮ የተለያዩ ውሳኔዎች ላይ ስህተት እግኝቷል፡፡ እናም  መታረም አለባቸው ብሎ የኤፍሬም ታምሩ እና የከሳሹ ጉዳይ ግራ ቀኝ ክርክር በጽሁፍ አቅርበው እንዲከራከሩ አድርጓል፡፡

ይህንን ካደረገ በኋላም የእስር ፍርድ ቤት የተወሰኑ ውሳኔዎች ላይ ማሻሻያ ያደረገ ሲሆን፣ ከተደረጉት ማሻሻያዎች ውስጥ  የ100 ሺህ ብር የሞራል ካሳ ይከፍላል ብሎ የሰውም ይሁን የሕግ ማስረጃ ድጋፍ ያለው ባለመሆኑ  በጠቅላይ ፍርድ ቤት በኩል ተቀባይነትን ባለማግኘቱ የሚነቀፍ እና ሊሻር የሚገባው ሆኖ ተገኝቷል በማለት ውሳኔዎችን ሽሮታል፡፡

በመሆኑም፣ ይህንን ውሳኔ የተሻረባት ከሳሽ፣ የኤፍሬም ታምሩን ጉዳይ ይዞ ለሰበር ሰሚ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፊታችን ሰኞ ይቀርባል አይቀርብ ለማለት ቀጠሮ ተይዟል ፡፡

በተመሳሳይ የፍርድ ቤት ዜና፣ አርቲስት ሚኪያስ መሀመድ በሚሊየን የሚቆጠር ብር እንዲከፍል እንደተወሰነበት ለማወቅ ተችሏል፡፡

በባለታኪሲው ፊልም እና በተከታታይ ፊልሞች እንዲሁም በማስታወቂያ ብዙዎች የሚያውቁት አርቲስት ሚኪያስ መሀመድ በከሳሽ ከድር አህመድ፣ ፋሲል አህመድ፣ ፍርዶስ አህመድ፣ አቶ ገዛኸኝ መሀመድ  አቶ ሠይፉ ዳሳ እና በወ/ሮ ገላቲያ ተስፋዬ ነው፡፡

አርቲስት ሚኪያስ በአንደኛ ደረጃ ተከሳሽ ሲሆን፣ ሁለተኛ ተከሳሽ ወላጅ እናቱ ወ/ሮ ፈለቀች እንግዳ ናቸው፡፡

የክስ ጭብጡም፣ ሚኪያስ ከ6ቱ ግለሰቦች የተለያየ መጠን ያለው በአጠቃላይ 4 ሚሊየን 305 ሺህ  ብር ተበድሮ ሊከፍለን አልቻለም በሚል ነው፡፡

ከሕዳር 20 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ከሚታሰብ  ወለድ ጋር እንዲከፈለን ሲሉ ከሳሾቹ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

በገንዝብ የማይከፈለን ከሆነም በእናቱ ስም ተመዝፍቦ በበሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ቤት ወስጥ የሚገኘው የቤት ቁጥሩ 404 መኖሪያ ቤት በብድር መያዣነት ያስያዙን ስለሆነ፣ ብድሩ ካልተከፈለን ተሽጦ ይከፈለን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በ26/12/2008 ዓ.ም ተከሳሽ ሚኪያስ  ተደረገ በተባለው የብድር መያዣ ውል በተመለከተ ውሉ ሕጋዊ አይደለም በማለት ሃሳቡን አቅርቧል፡፡

ምክንያቱን ለፍርድ ቤት ሲያስረዳም፣ ከከሳሾቹ በዕለቱ ገንዘብ አልተበደርኩም ውሉ የመያዣ እንጂ የብድር ውል አይደለም በመካከላችን የተደረገው ውል አራጣ ነው  ሲል ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

በ20/10/2007 ዓ.ም ንግድ ፈቃድ አውጥቼ ባጋጠመኝ የብድር ማጣት በከፍተኛ ወለደ በአራጣ መልክ ነው ከከሳሾች የተበደረኩት ሲል ለፍርድ ቤቱ መልስ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱም የተደረገው ውል ህጋዊ ነው አይደለም የብድር ውል ነው አይደለም የሚሉትን ምርመራ በማድረግ እና የምስክር ቃል በማድመጥ በተጨማሪም የግራ ቀኝ ክርክር ካዳመጠ በኋላ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በዚህም መሰረት፣ በከሳሽ እና በተከሳሽ መካከል ነሀሴ 16 ቀን 2008 ዓ.ም በተደረገው የብድር ውል መሠረት፣ አንደኛ ተከሳሽ ከስድስቱ ከሳሾች 4 ሚሊዮን 305 ሺህ ብር ብድር ከህዳር 23 ቀን 2010ዓ.ም ጀምሮ በ9 ፐርሰንት ህጋዊ ወለድ ለካሳሾች እንዲከፍል ወስኗል፡፡

ተከሳሽ መክፈል ካልቻለም በተከሳሽ ስም ቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ 04 ውስጥ የቤት ቁጥር 404 በተጠቀሰው ገንዘብ ተሽጦ ለከሳሾች እንዲክፍል ውሳኔ ተላልፏል፡፡

በተጨማሪም ወጪ እና ኪሳራን በተመለከተም ከሳሾች ለዳኝነት 45 ሺህ ዘጠኝ መቶ ብር፤ ለጠበቃ አበል 100 ሺህ ብር በድምሩ 145 ሺህ ዘጠኝ መቶ ብር ለአንደኛ ተከሳሽ እንዲከፈል ውሳኔ ተላልፏል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com