የዛሬ ሐሙስ የእግር ኳስ ፍልሚያ

Views: 949

ካሳዬ (ቡና) እና ጊዮርጊስ

የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ የቀድሞ የክለቡ ተጫዋች- አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ የሾመው በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ትልቅ ቦታና ስም ካላቸው ተጨዋቾች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ካሳዬ አራጌ በአጨዋወት ፍልስፍናውም በአገሪቱ ከሚገኙ በርካታ አሠልጣኞች እንደሚለይ የሚያምኑ ብዙዎች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ቡና በርካታ የደጋፊ ቁጥር ካላቸው ክለቦች በግንባር ቀደምትነት መጠቀሱ፣ ክለቡ በማንኛውም ጊዜ ጨዋታ ሲኖረው ስታዲየም የሚታደመውን የተመልካች ቁጥር መመልከቱ በቂ ይሆናል፡፡ ለክለቡ ደጋፊዎች መብዛት ዓይነተኛ ሚና ከተወጡ ተጨዋቾች አንዱ አሁን ኢትዮጵያ ቡና አሠልጣኝ ሆኖ የተሾመው ካሳዬ አራጌ ቀዳሚው ነው፡፡

ኢትዮጵያ ቡና፣ አሰልጣኝ ካሳዬን ሲያመጣ ለእሱ አጨዋወት ይመቹኛል የሚላቸውን ተጨዋቾች እንዲያስፈርም፣ በሌላ በኩል ደግሞ የማይመቹትን ተጨዋቾች እንዲያሰናብት ማረጋገጫ መስጠቱን ጭምር ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና ቡድኑን በለቀቁት በርካታ ተጨዋቾች ምትክ፣ ለካሳዬ አጨዋወት ይሆናሉ ተብሎ የታመነባቸው፣ በራሱ በካሳዬ ይሁንታ ያገኙ ተጨዋቾች ቅጥር እና ዝውውር መፈጸሙ የሚታወቅ ነው፡፡

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ክለቡን ለ4 ዓመታት በአሰልጣኝነት የሚመራ ሲሆን፥ በውሉ መሠረት የመጀመሪያው ዓመት ያለ ቅድመ ሁኔታ እንደሚሰራ ተገልጿል።

በቀሪዎቹ 3 ዓመታት ግን ክለቡ በፕሪሚየር ሊጉ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃን ይዞ መጨረስ እንዳለበት ቅድመ ኹኔታ በውሉ ላይ ተቀምጧል።

የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን ወደ ቡና መምጣትን ተከትሎ ክለቡ የቀድሞ አጨዋወቱንና ውጤቱን እንደሚመልስ ተስፋ እንደተጣለበት ተነግሯል።

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ ባሳለፈው የተጫዋችነት ጊዜ ይለብስ የነበረው 15 ቁጥር ማልያም በወቅቱ በነበረው መልክ ታትሞ ተበርክቶለታል።

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ከ1979 እስከ 1994 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቡናን በመሐል ሜዳ ተጫዋችነት ያገለገለ ሲሆን፥ ከተጫዋችነት ዘመኑ በኋላም ለ1 ዓመት ከ6 ወር ገደማ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ዋና አሰልጣኝነት መርቷል።

ከኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ጋር በነበረው የአንድ ዓመት ከግማሽ ቆይታው የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ከክለቡ ጋር ማንሳት እንደቻለ ይታወሳል።

በ1995ዓ/ም የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር ኢትዮጵያ ቡና በተጫዋች ካሳዬ አራጌ አሰልጣኝነት በነበረ ጊዜም፣ ካሳዬም ለሚመጣው ውጤት ኃላፊነቱን ራሱ እንደሚወስድ በመግለፁ ተጫዋቾቹ በነፃነት መጫወት ችለው ነበር።

የ1995ቱ ቡድን በሁሉም ጨዋታዎች ከጨዋታ ብልጫ ጋር በዓመቱ መጨረሻ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ አሸናፊ እና በፕሪሚየር ሊጉ ሶስተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ ሻምፕዮን ከሆነው ቡድን ቀጥሎ ብዙ ግብ ያገባ ከመሆኑም በላይ፣ ጥቂት ግቦች ከተቆጠረባቸው የመጀመሪያው ክለብ ሆኖ አጠናቋል።

የዘንድሮው 2012 ቡድን ከ95ቱ የሚለየው በአዳዲስ እና በአብዛኛው ታዳጊ ተጫዋቾች ያሉበት በመሆኑ ሲሆን፣ ካሳዬ ልጆቹን አዋህዶ ወደ ሚፈልገው አጨዋወት ለማምጣት እና ቡድናችን ሁሌ አሸናፊ ሆኖ እንዲያስደስተን ተጫዋቾቹ ተረጋግተው ከአሰልጣኙ የሚሰጣቸውን ሥልጠና እንዲተገብሩ ጊዜ የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ እንደያኔው ሁሉ ነገን ለመደሰት ዛሬ ከደጋፊዎች ትዕግስት ያስፈልጋል በማለት ለቡድኑ ቅርብ የሆኑ አንጋፋ ደጋፊዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

ካሳዬ ከሁለት ወር በፊት ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጣይ የክለቡ ዋና አሠልጣኝ ተደርጎ መሾሙን የሚታወስ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት አሰልጣኙ በ14ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር ላይ ከቡድኑ ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች እያካሄደ ይገኛል፡፡

እስካሁን ሦስት ጨዋታዎችን ያደረገው ቡና በአንድ ጨዋታ ሲያሸንፍ፣ በአንድ ጨዋታ አቻ በአንድ ጨዋታ ደግሞ ተሸንፈዋል፡፡ ዛሬ ደግሞ ከምጊዜውም ተፎካካሪው ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ለዋንጫ ሽሚያ ለማለፍ ይጫወታል፡፡

የኢትዮ ኦንላይን ዘጋቢ ሃብቴ ታደሰ፣ ኢትዮጵያ ቡና ረቡዕ በማለዳ ከሐሙሱ ጨዋታ በፊት የመጨረሻውን ቀለል ያለ ልምምድ በሚያካሂዱበት ሜዳ ተገኝቶ ከአሰልጣን ካሳዬ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡

(የምሥል ወድምጽ ዘገሀባችንን በዩቲዩብ አድራሻችን ላይ በሚከተለው ሊንክ፡- https://www.youtube.com/watch?v=Zfeb9IQ4DFI መከታተትል ይችላሉ)

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com