‹‹ሰው ነኝ ለሰው ክብር ያለኝ›› የታላቁ ሩጫ ተሳታፊዎች የጋራ ተግባቦት መርህ ነበር ተባለ

Views: 61

ዓመታዊው ታላቁ ሩጫ፣ ለየት ባለ መልኩ፣ ዜጎች ሀገራዊ ምልከታቸውን የሚገልጹበት፣ ፖለቲካዊ አቋማቸውን የሚያንጸባርቁበት እና ለመንግሥት መልዕክት የሚያስተላልፉበት ዓውድ (መድረክ) እየሆነ መምጣቱን ተሳታፊዎች ተናገሩ፡፡

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫም፣ ከማኅበራዊ ጉዳዮች ይልቅ ፖለቲካዊ ሀሳቦች ጎላ ብሎ የተንጸባረቁበት፤ ግጭትና ኹከትን ፈጣሪዎችን ደግሞ በጋራ ያወገዙበት እንደነበር- ተሳታፊዎች ለኢትዮ-ኦንላይን ገልጸዋል፡፡

19ኛው የቶታል ታላቁ ሩጫ ከስፖርታዊ ክንውኑ በተጨማሪ፣ የተለያዩ የፖለቲካ ሃሳቦችን በጽሑፍ፣ በክዋኔ ጥበብ (እንቅስቃሴ)፣ በጋራ ሙዚቃዎች እና ነፃ ሃሳቦች የታዩበት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ተወዳዳሪዎች አሁን ኢትዮጵያ እየታመሰችበት ያለውን የዘረኝነት መንፈስን የሚኮንን “ሰው ነኝ- ኢትዮጵያዊ”፣ “ሰው ነኝ ለሰው ክብር ያለኝ”፣ “ሁላችንም ከአዳም ነን፤ አዳም ደግሞ አፈር ነው”፣ “አክቲቪስት ነኝ አንዳትከተለኙ”  ወ.ዘ.ተ የሚሉ ጽሑፎችን በመለያ ካናቲራቸው (ቲ-ሸርት) ላይ በመለጠፍ፣ በዘር በመከፋፈል የሚያገዳድሉን ፖለቲከኞች ለራሳቸው የፖለቲካ ጥቅም ብቻ አስበው ነው በማለት ሀሳባቸውን ገልጸዋል፡፡

ወጣቶች አንድ ላይ በመሰብሰብ “እየገደሉ ሠላም ነው አሉ” በማለት አሁን ሀገሪቷን የምትገኝበትን የሠላም ማጣት ችግርን እንዲሁም በመሐል ሩጫቸውን ገታ አድርገው በፕላስቲክ ጠርሙስ ራሳቸውን በመክበብ “ተከብቤያለሁ…መንገዱን ዝጋው” በማለት በተጨማሪም “ቄሮ ጥረህ ግረህ ብላ” የሚል ፖለቲካዊ ሀሳባቸውን ለማንጸባረቅ ሞክረዋል፡፡

በዚህ ውድድር 45 ሺህ ተሳታፊዎች የተካፈሉ ሲሆን፣ ካለፉት ዓመታት የዘንድሮው ውድድር በብዛት የፖለቲካ ሃሳቦች ጎልተው የተንጸባረቁበት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com