በአማራ ክልል የአንበጣ መንጋ እና የግሪሳ ወፍን መቆጣጣር እንዳልተቻለ ተገለጸ
- በ122 ቀበሌዎች ላይ የአንበጣ መንጋ ተከስቷል
በአማራ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ እና የግሪሳ ወፍን ለመከላከል እየተሰራ ቢሆንም፣ ለመቆጣጠር አለመቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ ለኢትዮ-ኦንላይን አስታወቀ።
በምሥራቅ አማራ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ወሎ ዞን ከዘጠኝ ባላነሱ ወረዳዎች ያጋጠመውን የበረሃ አንበጣ መቆጣጠር ፈታኝ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ አለባቸው አሊጋዝ አስታውቀዋል፡፡
የአንበጣ መንጋው ዛሬ ጠፋ ሲባል ነገ መከሰት፣ በማሕበረሰቡ በኩል ቶሎ መሰላቸት፣ የሰው ኃይል እጥረት፣ የግብዓት እና የገንዘብ እጥረት በለፋነው ልክ መቆጣጠር አልቻልንም ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ለዘጋቢያችን ጠቁመዋል፡፡
አሁንም ቢሆን በሁለት አውሮፕላኖች በመታገዝ የመከላከሉን ሥራ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን እየሰራን ነው ብለዋል አቶ አለባቸው አሊጋዝ፡፡
በአንበጣው ምክንያት በሰብል ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመግለፅ እንደየዞኑ እና እንደ የወረዳው ጥናት እያስጠናን ሲሆን፣ በአሁን ወቅት ግን 122 ቀበሌዎች በአንበጣ ሰብሎቻቸው መሸፈኑንም አቶ አለባቸው ተናግሯል፡፡