ኤል ቴቪ የአሐዱ ራዲዮን ሥም ማጥፋቱን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን አስታወቀ

Views: 64

ኤል ቴቪ የተባለው የግል ሳተላይት ቴሌቪዝን ጣቢያ፣ ‹ኤል ቴቪ ሾው› በተሰኘው ሳምንታዊ የቃለ-መጠይቅ ፕሮግራሙ ላይ አሐዱ ራዲዮ 94.3 ፀረ ኦሮሞ አስመስሎ ማቅረቡን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ለኤል ቴቪ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በፃፈው ደብዳቤ ድርጊቱ ከብሮድካስት ዓዋጁ ብሎም ከጋዜጠኝነት መርሆ እና ሥነ ምግባሮች ያፈነገጠ በመሆኑ በተመሳሳይ ፕሮግራም ላይ በተመጣጣኝ የጊዜ ገደብ ማስተባበያ ጥፋቱን አምኖ እንዲያስተባብል አዝዟል፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዶክተር ገመቹ መገርሳ የተባሉ ግለሰብ ከቴሌቪዥን ጣቢያው ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ አሐዱ ራድዮ 94.3 ኦሮሞነትን እና ኦሮሞ ዋጋ የሚሰጣቸውን እሴቶች ሁሉ የሚያቋሽሽ እንደሆነ መግለፃቸውን ከፕሮግራሙ ቀን ጅምሮ በደብዳቤው ጠቁሟል፡፡

የፕሮግራሙ አዘጋጅም የግለሰቡን አገላገፅ ከመሞገትና ሃሳቡን ሚዛናዊ ከማድረግ ይልቅ ‹‹መልካም›› ብላ በማለፍ ከጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ውጭ ድጋፏን ገልፃለች ብሏል፡፡

በመሆኑም ድርጊቱ የራዲዮ ጣቢያውን ስም የሚያጠፋ ብሎም ከዓዋጁና ከሥነ ምግባሩ ውጭ በመሆኑ ጉዳዩን እንዲያስተባብል ጠይቋል፡፡ አፈፃፀሙንም ከዛሬ ጀምሮ ባሉት ሰባት ተከታታይ ቀናት ውስጥ በደብዳቤ እንዲያሳውቅ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ዛሬ ሕዳር 5 ቀን 2012 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ አዝዟል፡፡

አሐዱ ራዲዮ 94.3 ኤል ቴቪን ጉዳዩን እንዲያስተባብል ቢጠይቅም ተግባራዊ እንዳልተደረገለት ጠቁሟል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣንም ደብዳቤውን የፃፈው ከራዲዮ ጣቢያው በደረሰው ቅሬታ መሠረት ነው፡፡

 

 

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com