“የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲቆም ተወሰነ” የተባለው የሀሰት-ወሬ ነው

Views: 78

 

  • የግድቡ ግንባታ ከ 68.5 በመቶ በላይ ደርሷል!
  • ለ1 ደቂቃ ግንባታው ሊቆም አይችልም!

በማኅበራዊ ሚዲያ፣ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ‹‹የህዳሴ ግድብ ሥራ እንዲቆም ትዕዛዝ ሰጡ›› በሚል የተለቀቀው ወሬ፣ የሀሰት መረጃ መሆኑን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡ በአንፃሩ፣ ግድቡ በየቀኑ በየስምንት ሰዓታት የሥራ ምድብ፣ በሦስት ፈረቃ ለ24 ሰዓታት በግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኝና ለአንድም ደቂቃ ቢሆን ሊቆም የሚችል አለመሆኑን ለኢትዮ-ኦንላይን አስታውቋል፡፡

የህዳሴ ግድብ የሥራ እንቅስቃሴም ሆነ ማንኛውም ግድቡን የተመለከተ ውሳኔ የሚተላለፈው በውጭ ጉዳይ አሊያም በውጭ ጉዳይ ሚንሥትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ሳይሆን፣ በቀጥታ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ነው በማለት ለኢትዮ-ኦንላይን የገለጹት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም፣ ግንባታው መቆም ካለበትም ውሳኔው የኢትዮጵያ ሕዝብና የተወካዩ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በጋራ የሚሳተፉበት የልማት ፕሮጀክት በመሆኑ፣ ምንም ዓይነት የገንዘብ እጥረት የለበትም፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም ከልማት ሥራዎች ሁላ ቁጥር አንድ በጀት የሚበጅተው ለዚህ ግንባታ ነው፤ እውነታው ከመቼውም ጊዜ በላይ ግድቡ በፍጥነት እየተገነባ መሆኑ ነው፤ ሃቁ ይሄ ነው፤ ሌላው ሁሉ ሆን ተብሎ በሆኑ አካላት የሚነዛ የሀሰት ወሬ እና የማዳከሚያ ፕሮፓጋንዳ ነው- ብለዋል፡፡

የሕዳሴ ግድብ ቀደም ሲል በሜቴክ ኃላፊዎች የደረሰበት ንቅዘትና የሥራ ጉድለት ታርሞ፣ ችግሮቹም ተፈተው ግንባታው እየተፋጠነ ነው በማለት ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የግድቡ ግንባታ ከ 68.5 በመቶ በላይ ደርሷል ያሉት የኮሙኒኬሽን ኃላፊው አቶ ኃይሉ አብርሃም፣ በግንባታው ሂደት አስፈላጊ የነበረው የጉልበት ሠራተኞች ሚና በአሁኑ ጊዜ በመጠናቀቁ ቀደም ሲል ይሰሩ ከነበሩት 12 000 በላይ ሠራተኞች ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ላለው ሥራ አስፈላጊ የሆኑ 4 000 የጉልበት ሠራተኞች እና ሌሎች የሙያ ሠራተኞች ቀን ከሌት በማገልገል ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

ግድቡ የተለያዩ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ የኮርቻ ግድብ የሚባለው ክፍል ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የሚሸፍነውም 5 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ነው፤ ወደ ላይ ቁመቱ ደግሞ 50 ሜትር ነው፡፡ ሌላው ክፍል ደግሞ ውኃው ሲሞላ ለጎርፍ ማስተንፈሻ የሚያገለግለው ክፍል ሲሆን፣ ይህም 97 ከመቶ አካባቢ ግንባታው ተጠናቋል ብለዋል፡፡

የሲቭል ሥራው በሙሉ የተያዘው በዓለማቀፉ የግንባታ ተቋም በሳሊኒ ኮንስትራክሽን ነው ሲሉ የገለጹልን የመረጃ ኃላፊው፣ ሳሊኒ በአሁኑ ጊዜ ለመንግሥት እንዳሳወቀው 82 ከመቶ ሥራው ተጠናቋል ብሏል፡፡

ነገር ግን፣ ቀደም ሲል ሜቴክ ይዞት የነበረው የብረታ-ብረት ሥራ በንቅዘት፣ በጉድለትና በችግር ተተብትቦ የነበረ ሲሆን፣ ጠ/ሚ ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በወሰዱት የማስተካከያ እርምጃ፣ ታርሞ በአሁኑ ጊዜ ወደ 25 ከመቶው አካባቢ ተጠናቋል ሲሉ ኃላፊው ለኢትዮ-ኦንላይን አስረድተዋል፡፡

ቀደም ሲል የብረታ ብረት ሥራው ከፍተኛ ችግር የነበረበት ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚንሥትሩ ሥራ ሲጀምሩ  13 ከመቶ ብቻ ነበር ተጠናቆ የነበረው፡፡ በተቀናጀ የሀሰት ወሬ ሳንዳከም፣ ልማታችንን እናፋጥናለን፤ ከዚህም የሚገታን ኃይል አይኖርም ብለዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com