ዜና

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የአንድ ተማሪ ሕይወት አለፈ

Views: 878

አንድ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተማሪ፣ ከዩኒቨርሲቲው ግቢ ውጭ ጉዳት ደርሶበት ሕይወቱ ማለፉን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር አስታውቋል፡፡

ተማሪው ትናንት ሕዳር 4 ቀን 2012 ዓ.ም ምሸት አንድ ሰዓት ገደማ ደብረ ብርሃን ከተማ ቀበሌ ዘጠኝ ልዩ ስሙ ባሶ ትምህርት ቤት አካባቢ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት ተገልጿል፡፡

በወቅቱ በደብረ ብርሃን ሆስፒታል ሕክምና ቢደረግለትም ሕይወቱን ማትረፍ አልተቻለም ተብሏል፡፡ ሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ በይፋዊ የማሕበራዊ ትስስር ገፁ ይህንን በገለፀበት ጽሑፍ፣ ኦሮሚያ ውስጥ በሚገኙ ልዩ-ልዩ ዩኒቨርሲቲዎች ስለሞቱ ተማሪዎች ያለው ነገር የለም፡፡

በተመሳሳይ፣ በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ አንድ ተማሪ በመታጠቢያ ቤት ውስጥ ጉዳት ደርሶበት በሕክምና ላይ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር አስታውቋል፡፡ የጉዳቱ ምንነትና መንስዔ ገና እየተጣራ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተቀሰቀሰው ኹከትና ግጭት ወደ መረጋጋት መመለሱንም ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡

በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሂደቱ ሙሉ በሙሉ የተጀመረ ሲሆን፣ በአንዳዶቹ ደግሞ በከፊል ተጀምሯል፡፡

ጅማ፣ መቱ፣ መዳወላቦ፣ ወልዲያ እና ወሎ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በአንፃራዊነት የተሻለ መረጋጋት መኖሩን የሳይንስና ከፍተኛ ሚንስቴር ገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ 28 የአማራ ተወላጅ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲውን ለቀው ዛሬ ወደ ባሕር ዳር መመለሳቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የዩኒቨርሲቲዎችን ሰላም ለማስጠበቅ የትምህርት ዘርፍ እና የፖለቲካ አመራሮች በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እየተወያዩ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com