ሢራራ የጤፍ ነጋዴዎች ንብረታቸው አለ አግባብ መወረሱን ገለጹ

Views: 74

ሀገር አቋራጭ ሢራራ የጤፍ ነጋዴዎች፣ ንብረታቸው ያለ አግባብ በኢ-ሕጋዊ መንገድ፣ በአዲስ አበባ መሥተዳደር መወረሱን፣  ለኢትዮ-ኦንላይን አስታወቁ፡፡

ነጋዴዎቹ፣ ከአማራ ክልል ጎጃም እና ሰሜን ሸዋ ጤፍ ከአርሶ አደሮች ገዝተው ወደ አዲስ አበባ በማምጣት ለገበያ የሚያቀርቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር፤ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የመንግሥት ባለሥልጣናት ብዛቱ 53 አይሱዙ የጭነት ተሸከርካሪ ሙሉ የሆነ ጤፍ. ከመስከረም 9 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ፣ ከነጋዴዎቹ በኃይል በመንጠቅ እንዲወረስ ማድረጋቸውን ነው ነጋዴዎቹ ለኢትዮ-ኦንላይን ያሳወቁት፡፡

ከ53ቱ ተሸከርካሪዎች መካከል 50ዎቹ ከጎጃማ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሽያጭ ሊቀርቡ የመጡ ሲሆን፣ ሦስቱቱ ደግሞ ከሰሜን ሸዋ ለአዲስ አበባ ገበያ የቀረቡ ናቸው፡፡

በአንድ ተሸከርካሪ የተጫነው ጤፍ ብቻ፣ ከመቶ ሰባ እስከ መቶ ስልሳ ሺህ ብር ይገመታል ተብሏል፡፡

ከነጋዴዎቹ መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አበበ ሽታዬ፣ በተለይ ለኢትዮ ኦን ላይን እንደገለፁት፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት ንብረቱን ሲይዙ ያቀረቡት ምክንያት ‹ለሕገ ወጥ ደላላ ትሰጣላችሁ› የሚል ነው፡፡ ነጋዴዎቹ ንብረታቸው እንዲመለስላቸው ቢሯቸው ድረስ ሄደው ሲጠይቁም በፖሊስ እንዳስደበደቧቸው አቶ አበበ ለኢትዮ-ኦንላይን ገልፀዋል፡፡

ነጋዴዎቹ ቅሬታቸውን ለአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት በደብዳቤ ቢያቀርቡም፣ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ምልሽ አልተሰጣቸውም፡፡

በጉዳዩ ላይ በእነርሱ በኩል ያለውን ዕይታ ማብራሪያ እንዲሰጡን ወደ ከንቲባው ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ጥሪው አልተመለሰም::

ነጋዴዎቹ ሕጋዊ የንግድ ሥራ ፈቃድ ያላቸው ሲሆን፣ ተገቢውን ግብር ለመንግሥት እየከፈሉ መሆኑንም ጨምረው አሳውቀዋል፡፡

ንብረታቸው ከተወረሰበት መስከረም 9 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ግን ሥራ ማቆማቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ይህንን ተከትሎ ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው የከተማው ነዋሪዎች ይህ ዓይነት አግባብነት የሌለው ውሳኔ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የጤፍ አቅርቦት እንዲቀንስ ስለሚያደርግ፣ በነዋሪው ላይ ዋጋ እንደሚጨምር ያደርጋል፡፡

በተጓዳኝም፣ በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የኑሮ ውድነትን ይጨምራል፤ በሌላም በኩል ነጋዴዎቹ ጤፍ ይገዙበት በነበረው ጎጃም እና ሰሜን ሸዋ አካባቢዎች ደግሞ የጤፍ ፍላጎት በመቀኑ፣ አርሶ አደሮች የሚሸጡበት ዋጋ እንዲቀንስ ስለሚያደርግ፤ ይህም የአካባቢውን አርሶ አደሮች ላልተገባ ኪሳራ መዳረጉ እሙን ነው ሲሉ ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com