ጠብታ-ውኃ ለችግኞች

Views: 70

ስብጥር ዛፍ ውስጥ (የደላው ሮዝመሪ ዛፍ ይመስላል)

የዛሬ ችግኞች የነገ ደን ናቸው፤ በቂ ውኃ ካለገኙ ግን ጭራሮ ሆነው ይቀራሉ!

መነሻ፡-

በዚሁ ድረ ገጽ ላይ “ችግኝ ተከላው በእንክብካቤ መታገዝ አለበት” (https://ethio-online.com/archives/4303) በሚል ርዕስ ሃሳብ አስፍረን ነበር፡፡ ነገር ግን እዚያ ላይ እንዴት ውኃን በቁጠባ ማጠጣት እንደሚቻል በሚገባ አልተገለፀም ነበር፡፡ እነሆ አሁን ይቺን መላ ተመልከቱ፡-

ሀ/ ከፍተኛ የውኃ መጠን እየባከነ ነው

ክረምቱን የተተከሉትን ችግኞች ለመንከባከብ ሲባል፣ በግልጽ እንደምትመለከቱት ለችግኞቹ ውኃ በማጠጣቱ ሂደት ከልክ በላይ የሆነ ውኃ ይባክናል፡፡ ውኃው ከመጠን በላይ በሚረጭበት ጊዜ ትንሽ ጎርፍ ሰርቶ ይፈሳል፡፡ አትክልቱ ወይም መሬቱ በዚያ ቅጽበት ውኃውን መምጠጥ አይችልም፡፡

ውኃው አንዳች የቁጠባ ዘዴ ያስፈልገዋል፡፡

  • አንድም ውኃን ከብክነት ለማዳን፤
  • ሁለትም ተክሉ ወይም መሬቱ ውኃውን በቀስታ ስለሚመጠው፤
  • ሦስትም ውኃው ለታሰበለት ዛፍ ሥር በበቂ ይደርሳል እንጂ ለአረም አይፈስም፣
  • አራትም ጊዜን ለመቆጠብ እና በሰፈሩ የሚኖሩ ሰዎች ተራ ገብተው በዚህ ዘዴ በቀላሉ መንከባከብ ይችላሉ፡፡

ለ/ የውኃ ፕላስቲኮችን እና ጀሪካን እንደ አማራጭ ተጠቀሙ

መንገድ ዳር ላለ ግራቪሊያ ችግኝ

ውኃ ከፕላስቲክ ሲፈስለት

እንደ ዛፉ መጠን፣ እንደቦታው ኹኔታ፣ እንደ አፈሩ ዓይነት የተለያየ መጠን ያላቸውን አሮጌ ፕላስቲኮች መጠቀም፡፡ ውኃው በጣም ቀስ ብሎ እንዲፈስ ከታች ፕላስቲኩን አንድ ሳንቲ ሜትር ከፍ ብሎ በመርፌ መብሳት፤ ከላይ በክዳኑ አናት ላይ ወይም ከፕላስቲኩ አንገት ዝቅ ብሎ ውኃው እንዳይታፈን ዓየር ማስገቢያ በተመሳሳይ በመርፌ መብሳት፡፡ አሁን የፕላስቲክ ጠርሙሱን እያንዳንዳቸውን ውኃ መሙላት፣ በእያንዳንዱ ችግኝ ወይም ዛፍ ሥር በአግባብ ማስቀመጥ፡፡ ውኃው ሲያልቅ ንፋስ ይዞት እንዳይሄድ ከዛፉ ወይም ከችግኙ ጋር ማሰር ያስፈልጋል፡፡

ለምሳሌ አንድ የመርፌ ቀዳዳ ከታች እና ከላይ ያለው ባለ ሁለት ሊትር የፕላስቲክ ዕቃ ከ 2ዐ እስከ 3ዐ ደቃቂ ያህል ውኃውን በቀስታ ሊያፈስ ይችላል፡፡ በዚሁ ዓይነት የትም የሚጣሉትን ቢጫ ጀሪካን መጠቀም ይቻላል፡፡ ጀሪካኖቹ ከዘይት፣ ከጨው፣ ከቆሻሻ ሁሉ ንፁህ መሆን አለባቸው፡፡፡

አሮጌ ጀሪካን አንዱ አንድ ዛፍ ስር ቢሆን

ይህ ሁሉ አሮጌ ጀሪካን ብዙ ቦታ ተከምሮ ፀሐይ ሲነካው ይታያል፡፡ በብለሃት ቢያዝ ከመወገዱ በፊት ለጥቂት ዓመታት ውኃን በዛፍ ሥር በማንጠባጠብ ሊያገለግል ይችላል፡፡

ሐ/ የውሃ ፕላስቲኮች እና ጀሪካን ብክለት እንዳያስከትሉ

በየመንገዱ ዳሩ እና ደን ውስጥ ለውኃ ቁጠባ ሲባል የተቀመጡ ፕላስቲክ እና ጀሪካን ግልጋሎታቸው ሲያበቃ ሰብስቦ ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ እዳ ከሜዳ ሆነ ማለት ነው፡፡

መ/ ፍግ ወይም ኮምፖስት ጨምሩ

ለተክሉ እድገት እና ውሃን ቋጥሮ ለመያዝ እንዲችል የከብት ፍግ ወይም የዳበረ ኮምፖስት ከተክሉ ሥር ጨምሩ፡፡

ሠ/ ማረም እና መኮትኮት

ችግኞቹ ዙሪያ ያሉትን አረም ማንሳት፣ መኮትኮት እና ውኃን ሰብሰብ እንዲያደርግ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡

ረ/ የአካባቢው ሰዎች መተባበር አለባቸው

የዛፍ ችግኞቹ በተተከሉበት አካባቢ እና በአቅራቢያ ያሉት ነዋሪዎች ወጥተው ተራ ገብተው ውኃን በቁጠባ ማጠጣት፣ መንከባከብ፣ የጠፋውን ተክቶ መትከል፣ ወዘተ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ማጠቃለያ፡-

ውኃ ማጠጫ ቀላል ዘዴ ይህ ብቻ አልነበረም፡፡ ግን ቴክኖሎጂው ብዙ ወጪ ስለሚጠይቅ ነው፡፡በከተሞች ዛፎቹ ጠቀሜታቸው ለውበት ብቻ አይደለም፣ የመጣውን የሙቀት ቁጣ ልብ በሉ፡፡ በከተሞች ውስጥ መንገድ ላይ በእግር ለመጓዝ ከባድ ከሚያደርጉት ጉዳዮች አንዱ በሙቀት መጨነቅ ነው፡፡ መኪና ወይም ታክሲ እስክንሳፈር እንኳን ንዳዱን ፈርተን ወደ ዛፍ ጥላ እንጠጋለን፡፡ ያለን ምርጫ በርትተን መሥራት ብቻ ነው፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com