ብሥራተ-ጤፍ!

Views: 130

ጤፍ በትውልዱ ኢትዮጵያዊ ሲሆን፣ ዜግነቱን ግን ዓለም እየተሻማው ነው፤ ለምን?

መግቢያ፡-

የጤፍ ጉዳይ ሲነሳ፣ በብዙ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ዘንድ ቁጭት ይፈጥራል፡፡ እንደሚታወቀው ጤፍ በትውልዱ ኢትዮጵያዊ ሲሆን፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እንደ ዋሊያ-አይቤክስ፣ እንደ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ እንደ ቀይ ቀበሮ፣ እንደ ጥቁር አንበሳ፣ እንደ … ከሀገር ውጪ የትም ሥፍራ እስትንፋስ አይኖረውም ተብሎ ይታሰብ ነበር፡፡ ሆኖም፣ ‹‹ከሞኝ ሥፍራ ሞፍር ይቆረጣል›› ሆነና እኛ በአግባቡ ያልያዝነውን ድንቅ ዘር፣ ሌሎች እድሜ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ብለው ጤፍን በዜግነት ከእኛ ሊነጥቁ ተቃርበዋል፡፡ አንድ ተቋም በአውሮፓ የባለቤትነት መብት መውሰዱም ይታወሳል፡፡ ይህ ጉዳይ የሚያብሰለስላት የግብርና ባለሙያዋ ደራሲ በቀለች ቶላ የጤፍን ብሥራት እንደሚከተለው ለአንባቢዎቿ ታበሥራለች፡፡

የጤፍ ጉዳይ ሲነሳ ኢትዮጵያዊያን ቁጭት አለብን፡፡ ለምን ቢባል፡- አንደኛ ጤፍ የዓለም ቁንጮ ምግብ ናት፤ ሁለተኛ ኢትዮጵያ የጤፍ መገኛ አገር ናት፤ ሦስተኛ በምግብ ባለሙያዎች እንደተረጋገጠው ጤፍ ከግሉተን ነፃ እና የጤና ምግብ ናት፤ አራተኛ ጤፍ የነገ የዓለም ህዝቦች የተስፋ ምግብ ናት፡፡ ጤፍ ዛሬም ቢሆን በዓለም ገበያ ውድ ዋጋ የምታስገኝ እህል ናት፡፡ እናም፣ በዓለም መድረክ የጤፍ ጉዳይ ሲነሳ፣ በእኛ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ትልቅ ቁጭት ይፈጥራል፤ ፈጥሯልም፡፡ ለዘመናት ትውልድ እየተቀባበለ እዚህ ያደረሳት ጤፍ፣ ዛሬ ከጉያው ወጥታ ሌላው ሊነግሥባት፣ ሊሸለምባትና ሊከብርባት ነው፡፡ የእሳት ልጅ ዓመድ ሆነን የተቀመጠልንን የዘመናት የኑሮ እውቀት እንኳ ማስከበርና ማስቀጠል ተሳነን፡፡

ምክንያቱም፣ እኛ ጤፍን ይዘን ከዓለም ገበያ ሳንገባ ቀረን፤ ሌሎች የጤፍ ዘርን ከእኛ ወስደው በቅርብ ዓመታት መዝራት የጀመሩት ሳይቀሩ፣ ጤፍን ይዘው ወደ ዓለም ገበያ ገብተው፣ የትሩፋቱ ተቋዳሽ ሆነዋል፡፡ የጤፍ መገኛ በሆነችው አገራችን ውስጥ ብዙ ሰው በረኃብ ይጎዳል፤ ያልቃል፡፡ ሌላም ብዙ ቁጭት አለና ወደ እዛ አንግባ፡፡

የሳይንሱ ማኅበረሰብ፡- “ጤፍ አትጠቅምም፣ ወደ ዋና የምርምር ዘርፍ አትገባም፤ ጤፍን ማደቀል አይታሰብም፤ ምርቱን ማሻሻል አይቻልም፤ የጤፍ ምግብ ጥቅም የለውም፤ ገለባ ማለት ናት፤  ጤፍ ዋና ሰብል ሳትሆን፣ ዝም ብላ ነገር ናት Orphan crop  ናት” ብለዋታል- እኮ፡፡ አቻ ትርጉሙ ‹‹አባት አልባ›› እንደማለት ነው፡፡ ጤፍ ላይ ስንት መጥፎ ዜና ሲሰራበት ነበር እኮ፡፡

ነገር ግን፣ ለምን ቁጭት ብቻ እያወሳን እራሳችንን እናሳምማለን? ስለ ምንስ የጤፍ ብስራትን አንስተን አናወራም!? ስለ ምን እስከዛሬ ብዙ ያልሰማናቸውን በጤፍ ላይ የተደረጉ ሥር ነቀል ለውጦች አንስተን አንወያይም? ስለምን በአርሶ አደሮች እና በተመራማሪዎች የተገኙ ገድሎችን አንጽፍም? አናነብም? ምን ነክቶን ነው? ከወደቀብን አዚም እንውጣ እና መልካሙን ብሥራት ተጠቅመን ምግባችንን በሠፊው እናምርት፡፡

የጤፍ ብስራት ስንት ጊዜ ነበር!?

የጤፍ ብስራት ስንት ጊዜ ነበር? ቢባል ብዙ ነው፡፡ ለሁሉም እንደምልከታው ነው፡፡ ወደ ፊት ጉባዔ ተቀምጠው “የጤፍ ብስራት እነዚህ ናቸው” ተብሎ እስኪለይ፣ በእኔ ምልከታ ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉትን እንመለከታለን፡፡

አንደኛው ብሥራት፡-

የመጀመሪያው የጤፍ ተመራማሪ፣ ዶ/ር መላከ ኃይል መንገሻ፡- ስለ ጤፍ ሥነ ፍጥረት እና ሥለ ጤፍ ሥነ ፆታዊ ኹኔታ፣ ከ5ዐ ዓመታት በፊት አውቀው እና ለተከታይ ተመራማሪዎች ማስተማር ችለዋል፡፡ ይህንንም ሃቅ በጊዜው ለዶ/ር ታረቀ በረሔ በማስረዳት፣ “ጤፍን ማዳቀል ትችላለህና ሞክር፤ ካዳቀልክ ደግሞ፣ አንድ መቶ ብር እሸልመሃለሁ”  ብለው ሥራውን አሃዱ ብለው ማስጀመራቸው በዘርፉ አንደኛው ብሥራት ነው፡፡

ሁለተኛው ብሥራት፡-

በ1959/ 196ዐ አሁንም ከ 5ዐ ዓመታት በፊት ታላቁ የጤፍ ተመራማሪ ሳይንቲስት ዶ/ር ታረቀ በረሔ ጤፍን ማዳቀል እንደሚቻል ብልሃቱን አገኙ፡፡ በደብረዘይት እርሻ ምርምር ውስጥ የግኝቱን ትግበራ እና መርሕ ለሌሎች የእውቀት ተከታዮቻቸው አስተማሩ፡፡ ዛሬም ድረስ ጤፍ የማዳቀል ሥር የሚከወነው በዚያው ዘዴ ነው፡፡

ሦስተኛው ብሥራት፡-

የጤፍ ዘርን በመረጣ ዘዴ እና በዶ/ር ታረቀ በረሔ በተገኘው የጤፍ ማዳቀል ብልሃት ተጠቅመው በደብረዘይት ምርምር ማዕከል ውስጥ ብዙ አዳዲስ የጤፍ ዘሮች መገኘት ችለዋል፡፡ እነዚህ አዳዲስ በመረጣ እና በማዳቀል የተገኙ የጤፍ ዓይነቶች ወደ አርሶ አደሩ ማሳ ደረሱ፡፡ ይህም የጤፍ ምርትን ድሮ ከነበረበት በእጥፍ የበለጠ ሊያስገኝ ቻለ፡፡ በተለይም፣ እስከዛሬም ባለዝና የሆኑት ‹‹ማኛ›› እና ‹‹ቁንጮ›› ጤፍ አርሶ አደሮች ለእህሉ እና ለጭዱ ከፍተኛ ምርት ብለው አብዝተው ይዘራሉ፡፡ በቁንጮ ግኝት ደብረዘይት እርሻ ምርምር በ2ዐዐ5 ዓ.ም ከመንግስት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልሞበታል፡፡

አራተኛው ብሥራት፡-

በደብረዘይት እርሻ ምርምር ውጤት መሠረት፣ በቅርብ ዓመታት የጤፍ ዘርን መጠን ከ6ዐ ኪሎ/በሄክታር ወደ 3ዐ ኪሎ በሄክታር በመቀነስ ምርታማነትን ማሻሻል መቻሉን ማሳየታቸው፡፡ አርሶ አደሮችም ለመዝራት የሚጠቀሙትን የዘር መጠን በሄክታር 3ዐ ኪሎ በማድረጋቸው የምርቱን መሻሻል በተግባር ተመለከቱ፡፡

አምስተኛው ብሥራት፡-

አንድ ተመራማሪ አርሶ አደር ሦስት የጤፍ ዝርያዎችን በአስር ዓመታት ጥረት በመረጣ ዘዴ አግኝተው፣ በሳይንሱ ማኅበረሰብ ታምኖባቸው ስያሜ አሰጡዋቸው፡፡ የጤፍ ዝርያዎቹ የተሰየሙት በልጆቻቸው ሲሆን፣ እያሱ፣ ፍፁም እና ቅድስት ይሰኛሉ፡፡ እነዚህም በብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ውስጥ አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለይም ኢያሱ እና ፍፁም የተባሉትን ዝርያዎች ለይተው የሚዘሩ አርሶ አደሮች አሉ፡፡

ስድስተኛው ብሥራት፡-

በደብረዘይት እርሻ ምርምር ውጤት ጤፍን በመስመር በመዝራት ከ 15 ኪሎ እስከ 2ዐ ኪሎ ጤፍ ለሄክታር እንደሚበቃ አወቁ፡፡ እናም ለአርሶ አደሩ አስተማሩ፡፡ ብዙዎች የምርምሩን መርህ የሚከተሉት በዚህ ዘዴ ተጠቅመው ምርታቸውን አሻሽለዋል፡፡

ሰባተኛው ብሥራት፡-

ሦስት የጤፍ ዝርያዎችን በመረጣ ያገኙት አርሶ አደር እራሳቸው በ2ዐ ዓመታት ልፋት እና ትጋት ጤፍ እና ማዳበሪያን በመስመር የሚዘራ በእንስሳት ጉልበት የሚጎተት ማሽን ሠሩ፡፡ ይህ ማሽን ጊዜን ይቆጥባል፣ ጤፍን ይቆጥባል፡፡ ታርሶ ለስልሶ ለዘር የተዘጋጀ አንድ ጥማድ ማሳ በአንድ ሰዓት ውስጥ ዘሩን እና ማዳበሪያውን  በመስመር  ዘርቶ አፈሩን በስስ አልብሶ መጨረስ ይቻላል፡፡ በዚህ ስሌት አንድ ሄክታር በ4 ሰዓት ማጠናቀቅ ይቻላል፡፡ በዚህ ማሽን ሲዘራ ለአንድ ሄክታር ከ 5 ኪሎ እስከ 8 ኪሎ የጤፍ ዘር ይበቃል፡፡

ስምንተኛው ብሥራት፡-

ከምርምር ማዕከል ውጪ በግል ተመራማሪዎች ጤፍን የሚወቃ ማሽን ተሠራ፡፡ ማሽኑ አሁን በጥቂት አርሶ አደሮች ዘንድ አለ፡፡ ቀድሞ በመሬት ላይ በብዙ በሬዎች ሲወቃ እና በሰው ጉልበት ሲበጠር የነበረው፣ ዛሬ በአንድ የመውቅያ ማሽን በሰዓት እስከ 4 ኩንታል ንፁህ ጤፍ ተበጥሮ ምርት ይገኛል፡፡ ጊዜ እና ጉልበት ይቆጥባል፤ የእንስሳት እና የሰው እንግልት የለም፡፡ የጤፍ ንጽህና የተጠበቀ ነው፡፡

ዘጠነኛው ብሥራት፡-

ክዊን ሼባ የኢትዮጵያ ሬስቶራንት በአሜሪካ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን (Queen Sheba Ethiopian restaurant in Sacramento) የጤፍ እንጀራ ምግብ ያቀርባሉ፡፡ የክዊን ሼባ ባለቤት ጽዮን ታደሰ ናት፡፡  ጤፉን የሚያገኙት የአሜሪካ አምራች ከሆነው ኤዳሆ (U.S. Idaho.) ሲሆን፣ ዋጋው ግን እየናረ ስለሄደ፣ ጤፍን በካሊፎርያ ለማሳረስ አሰበች፣ ብዙ ጥረት አደረገች፡፡ ሼባ ፋርምስ የተባለ ኩባንያ ከፈተች፡፡ ጤፍን ለማሳረስ ሥራው ቀላል አልነበረም፡፡ አማካሪ ባለሙያ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ በቅርቡም ከሌሎች አጋሮችዋ በተጨማሪ ከዶ/ር ታረቀ በረሔ የምክር አገልግሎት በማግኘትዋ ነገሮች ወደ ጥሩ መንገድ እያመሩ ነው፡፡ በመሆኑም፣ አሜሪካ ውስጥ ሼባ ፋርምስ በራሳቸው በታላቁ ተመራማሪ የምክር አገልግሎት ተደግፈው በካሊፎርንያ ምድር ጤፍ አዘሩ፡፡

ሌሎችም በብዙ አገራት ጤፍ ዘርተዋል፤ ነገር ግን ይኼኛዉ ብሥራት የሆነበት ምክንያት የተዘራበት ቦታ ከባሕር ጠለል በላይ 3ዐዐ ሜትር ከፍታ ላይ መሆኑ እና ከተዘሩትም ውስጥ ቦሰት የተባለችው ጤፍ ጥሩ ውጤት ማስገኘትዋ ነው፡፡ ቦሰት የተባለችው ጤፍ በዘር ሐረጓ የቁንጮ እህት ናት፡፡ ነገር ግን ቦሰት በተፈጥሮዋ ቆላማነትን እና ሙቀትን መቋቋም  ትችላለች፡፡ ቦሰት በእኛም አገር በቦሰት ወረዳ ውስጥ እስከ 8ዐ በመቶ የሚሆን ማሳ ላይ ትዘራለች፡፡ በደብረዘይት ዙሪያ፣ በኤጄሬ እና በሌሎችም ቦታ ትዘራለች፡፡ ነገር ግን በካሊፎርንያ መዘራቷ እና ከሌሎች የጤፍ ዓይነት ተሽላ ውጤት ማሳየቷ ልዩ ተስፋ ሰጪ ብሥራት ነው፡፡ በእኛም አገር ዓባይ በረሐ፣ ጊቤ በረሐ፣ ቦረና፣ አፋር፣ ሶማሌ እና ሌሎችም ቆላ እና በረሐ መሬት ላይ ቦሰትን መዝራት እንደሚቻል ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ተስፋ ብቻውን ሳይሆን የተሟላ የቴክኖሎጂ ፓኬጅ አብሮ ያስፈልጋል፡፡

የቦሰት ጤፍ ዘለላ

ማጠቃለያ፡-

መቼም የታወቀ ነው፡፡ ዋናዎቹ የጤፍ ባለጉዳዮች በተለይም የጤፍ ተመራማራዎች ሥራችሁን እዚያው በተለመደው አሠራር በራሳችሁ የሳይንስ ዓመታዊ ሪፖርት፣ በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ታሳትማላችሁ፡፡ ወይም በሸልፍ ላይ ታስቀምጣላችሁ፡፡ ህዝቡ ያነበው ዘንድ፣ ስለ ድካማችሁ ያመሰግናችሁ ዘንድ በሚረዳው ቋንቋ ፃፉለት፡፡ ለመገናኛ ብዙኋን በሰፊው ቀርባችሁ አስተምሩ፣ ምከሩ፡፡ እስቲ ብቅ በሉ፡፡ ለጤፍ ምርምር እና ማሻሻል ያደረጋችሁትን ተጋድሎ እንስማ፣ እናንብብ፡፡ እናም እናመስግናችሁ፡፡ በምርምራችሁ ውጤት ሌሎች ተጠቅመው ጤፍን በሰፊው ያምርቱ፡፡

እኛማ እንደአቅማችን የተረዳነው ያህል በዚህ መረጃ መረብ ላይ ከላይ የተነገሩትን ብሥራት እና ሌሎችንም የጤፍ ነገረ ጉዳዮች አቅም በፈቀደ መጠን ወደፊት እናቀርባለን፡፡

የመረጃ ምንጭ

1ኛ/ Kebebew Assefa, Solomon Chanyalew, and Zerihun Tadele (eds.) 2013. Achievements  and Prospects of Tef Improvement; Proceedings of the Second International Workshop, November 7-9, 2011, Debre  Zeit, Ethiopia Ethiopian Institute of Agricultural Research, Addis Ababa, Ethiopia  Institute of Plant Sciences University of Bern, Switzerland. Printed at Stämpfli AG, 3001 Bern, Switzerland

2ኛ/ youtube.com/ethio online/   -የጤፉ ጉዳይ  /ከዶ/ር ታረቀ በረሔ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ

3ኛ/ youtube.com/ethio online/  የጤፍ ጉዳይ ክፍል ሁለት /ከዶ/ር ታረቀ በረሔ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ

4ኛ/ youtube.com/ethio online/  የጤፍ ጉዳይ ክፍል ሶስት /ከዶ/ር ታረቀ በረሔ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ

5ኛ/- https///ethio online.com/ የእንጀራ /Injera/ ጉዳይ

6ኛ/Emily Hamann, EDT  Zion Taddese owns the Queen Sheba  Ethiopian restaurant in Sacramento,

Sacramento Business Journal  https://www.bizjournals.com/

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com