ዜና

ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎቹ በአስቸኳይ የእርግዝና ምርመራ አድርገው ውጤቱን እንዲያሳውቁ መመሪያ አወጣ

Views: 439

በጊቢው አራስ-ልጅ በውሻ ተበልቷል፤ ሽንት ቤት ተጥሎ ተገኝቷል

የዩኒቨርስቲው ሴት ተማሪዎች ሁሉ፣ በአስቸኳይ የእርግዝና ምርመራ አድርገው፤ ውጤቱን በ48 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ እንዲያሳውቁት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ሴኔት እንዲህ ዓይነት አስቸኳይ መመሪያ እንዲያወጣ ያስገደደው፣ በዩኒቨርስቲው ቅጥር ጊቢ ውስጥና በሴቶች ማደሪያ/ዶርም አቅራቢያ አራስ-ልጆች እየተጣሉ በመገኘቱ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የሚያገለግሉ መምህር ለኢትዮ-ኦንላይን አሳውቀዋል፡፡

በተለይ ደግሞ ሽንት ቤት ውስጥ የተጣለ ህፃን ሞቶ መገኘቱና በዩኒቨርሲቲው ቅጥር-ጊቢ በውሻ ሲበላ የታየ የአራስ-ልጅ አስከሬን፣ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት አስገዳጅ መመሪያ እንዲያወጣ መግፍዔ ምክንያት እንደሆነው ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የዩኒቨርሲቲው መምህር ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡

ስለዚህ ሁሉም ሴት ተማሪዎች አስቸኳይ የእርግዝና ምርመራ አድርገው በ48 ሰዓታት ውስጥ ውጤቱን ለ‹‹ፕሮክተሮች›› /ተቆጣጣሪዎች እንዲያስገቡ መመሪያውን ለተማሪዎች ሁሉ በማሳወቅ፤ በጊቢው ውስጥ ማሳሰቢያውን ለጥፏል ብለዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጊቢው ውስጥ ሴት ተማሪዎች ልጅ ወልደው ጥለው፣ አራስ ልጆች ሞተው እየተገኙ እንደሆነ በዩኒቨርሲቲው የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ለዘጋቢያችን ተነግሯል፡፡

ከዩኒቨርሲቲው ባገኘነው መረጃ መሰረት ከ አምስት ቀናት በፊት አንዲት ተማሪ ልጅ ወልዳ ዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ጥላው ተሰውራለች፡፡

ትላንት ጥቅምት 27 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት  ላይ ደግሞ፣ ሌላ  አራስ-ሕፃን ዶርም አካባቢ እንደተጣለ የዩኒቨርሲቲው ምንጮች ለኢትዮ ኦንላይን ተናግረዋል

በጉዳዩ ላይ ዘጋቢያችን ያነጋገረቻቸው ተማሪዎች፣ ኹኔታው እንደሰቀጠጣቸው ገልጸው፣ ጉዳዩ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነና የዩኒቨርስቲው አስተዳደር ትኩረት እንዲሰጠው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com