ዓባይ ወዲህ እና ዓባይ ማዶ ለሰዓታት የተሸከርካሪ ግንኙነት አቆሙ

Views: 194

ዓባይ ወዲህ እና ዓባይ ማዶ አካባቢዎች የተሸከርካሪ ግንኙነታቸውን ዛሬ ለሰዓታት ማቋረጣቸውን ተጓዦች አስታወቁ፤ ምክንያቱ ደግሞ የመኪና አደጋ ነው ተብሏል፡፡ የሁለቱ ሥፍራዎች አካፋይ በሆነው ዓባይ በረሃ ላይ የመኪና ግጭት አደጋ  የተከሰተው ዛሬ ዓርብ ጥቅምት 28 ቀን 2012 ዓ.ም እኩለ ቀን ላይ ነው፡፡ በሰውና በንብረት ላይ የደረሰ የከፋ ጉዳት ባይኖርም፤ በአደጋው ሳቢያ መንገድ ተዘግቶ መንገደኞች (ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ) በመጉላላት ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከአዲስ አበባ መነሻውን በማድረግ ወደ ደጀን መስመር በማምራት ላይ የነበረ አንድ አይዙ የደረቅ ጭነት መኪና፣ ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ላይ በደጀን ወረዳ ዓባይ በረሃ ውስጥ ኩራር በተባለ ቦታ ከሌላ ተሸከርካሪ ተሳቢ ጋር በመጋጨቱ መንገዱ ሊዘጋ እንደቻለ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የመገልበጥ አደጋ የደረሰበት መኪና ተንሸራቶ አውራ መንገዱን በመዝጋቱ ነው ከሁለቱም አቅጣጫዎች መንገደኞች ከጉዞ የታቀቡት፡፡

መንገዱ ከአሁን በፊትም የተበላሸ በመሆኑ፣ በሁለቱም አቅጣጫዎች በዓባይ በረሃ የሚያልፉ መንገደኞች እና ተሽከርካሪዎች ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ ነው ሲሉ የተናገሩት በአማራ ክልል ደጀን ወረዳ የኩራር ቀበሌ የኅብረተሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ኦፊሰር ሳጅን ደመላሽ ፍሬው ናቸው፡፡

ሳጅን ደመላሽ፤ አይሱዙ መኪናው ወደ ኋላ ተንሸራትቶ ከዚህ ቀደም በብልሽት ምክንያት ከቆመ ተሳቢ ጋር የተጋጨው፤ በዚህም የተነሳ ከጎንደርና ጎጃምም ሆነ ከአዲስ አበባ መስመር ተነስተው ዓባይ በረሃን አቋርጠው የሚያልፉ መንገደኞች ከጉዞ ታቅበው ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በሥፍራው የሚገኙት በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን መሀንዲስ የሆኑት  ማረልኝ ጋሻው በበኩላቸው፣ መፍትሔ ለመስጠት ተለዋጭ መንገድ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም የተበላሸውን መንገድ በአስፓልት ለመስራት እንደታቀደ ያስታወቁት አቶ ማረልኝ፤ መቼ እንደሚጀመር ግን በእርግጠኝነት ጊዜውን መናገር አልችልም ብለዋል፡፡

(ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ መንገዱ አለመከፈቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡)

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com