የኅሊና እሥረኞች ሥለ ኢ-ሰብዓዊ እሥር መግለጫ ሰጡ

Views: 213
  • የሰብዓዊ መብት ተቋማት ተወካዮች፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላትና አክቲቪስቶች ተገኝተዋል

75 የኅሊና እሥረኞች፣ ሥለ-ታሰሩበት ድርጊት፤ ሥለ-ፖሊስ የተጠርጣሪ አያያዝ፤ ሥለ-ፍትሕ ሥርዓቱና ዐቃቢያን-ሕግ የሥራ ሂደት፤ ሥለ-እስር ቤት ቆይታቸው አየነው ያሉትን ሁሉ በይፋ ገለጹ፡፡

ዛሬ ዓርብ ጥቅምት 28 ቀን 2012 ዓ.ም ረፋዱ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ የ‹‹ባለ አደራ ምክር ቤት›› (ባልደራስ) ጽ/ቤት የተገኙት በርካታ የኅሊና እሥረኞች የገጠማቸውንና የተመለከቱትን የሰብዓዊ መብት ግድፈት ለሰብዓዊ መብት ተቋማትና ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት አብራርተዋል፡፡

የታሰርንበት እሥር ቤት ሁለት በአንድ (ካሬ) የሆነ እጅግ ጠባብ ክፍል ነው በማለት የገለጸው የሕግ ባለሙያው አቶ ታከለ በቀለ፤ በጣም ቀዝቃዛ ከመሆኑ የተነሳ እረፍት ይነሳል፡፡

ከለውጥ በኋላ፣ እሥረኞችን ማሰቃየት ቀርቷል ቢባልም፤ በተጨባጭ ለሠላሳ ቀናት ያህል ማግለያ ቤት (ጨለማ ክፍል) ውስጥ ነጥለው አስረውናል ብሏል፡፡

በዚህ ላይ መርማሪ የተባሉ ፖሊሶች ‹‹ጠቅላይ ሚንንስትሩን ታደንቃለህ ወይ? አዲስ አበባ ከተማ የማን ትመስልኃለች?›› የሚሉ ከታሰርንበት ጉዳይ ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ ጥያቄዎችን ያቀርቡልን ነበር ሲል የሕግ ባለሙያው አቶ ታከለ በቀለ ተናግሯል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ገለፃ ያደረጉ ሌሎች የኅሊና እሥረኞች እንደተናገሩት ‹‹በእሥር የአራት ወራት ቆይታችን ለ30 ቀናት ያህል ገላችንን የምንለቃለቅበት ውኃና የመታጠቢያ ስፍራ (ሻወር) አላገኘንም ነበር በማለት ለሰብዓዊ መብት ተቋማት ተናግረዋል፡፡

በእሥር ሥፍራው ውስጥ ለስድሳ (60) እስረኞች በወረፋ አንድ መጸዳጃ ቤት ብቻ ነው የነበረው በማለት አስረድተዋል፡፡

‹‹ፖሊሶች ጨለማ ቤት ውስጥ መርጠው ያሰሩት ሁሉ የአማራ ብሄር ተወላጆችን ብቻ ነው›› በማለት ምልከታውን የገለጸው የዐማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (ዐብን) ፓርቲ የፋይናንስ ኃላፊ፣ ‹‹የሌላ ብሄር ተወላጆችን ግን በጨለማ ቤት ከሁለት ቀናት በላይ አያሳድሩም ብሏል፡፡

በውይይቱ ላይ በርካታ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ተወካዮችና አክቲቪስቶች ተሳትፈዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com