ባለሥልጣናት ሥልጣን መልቀቂያ ስለማስገባታቸው መረጃ እንደሌላቸው የጠ/ሚ አማካሪ ገለጹ

Views: 136

የሀገሪቱን ርዕሰ-ብሔር ጨምሮ የተወሰኑ ባለሥልጣናትና ሚንሥትሮች ሥልጣን ሊለቁ ነው የሚል ወሬ ከሰሞኑ በማኅበራዊ የትሥሥር ገፆች ለብዙዎች ተደራሽ ሆኗል፤ ኹኔታውን ለማጣራት በተንቀሳቃሽ ስልካቸው የደወልንላቸው የጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ አማካሪ ‹‹በጉዳዩ ላይ መረጃ የለኝም›› ብለዋል፡፡

በማኅበራዊ የትሥሥር ገፆች ለጊዜው በውል ባልታወቀ ምክንያት ሥልጣን ሊለቁ መሆኑ ከተነገረው ውስጥ የሀገሪቱ ርዕሰ-ብሔር ሣህለወርቅ ዘውዴ እና የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ዶ/ር አሚር አማን ጉዳይ ዋና መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

ጉዳዩን ለማጣራት በተንቀሳቃሽ ሥልካቸው ላይ የደወልንላቸው የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት የፕሬስ ሴክሬቴሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን፣ ስለ ባለሥልጣናቱ መልቀቂያ ማቅረብ አለማቅረብ ምንም የማውቀው ነገር የለም፤ በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት መረጃ የለኝም ሲሉ አስተባብለዋል፡፡

ይሄ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ለጤና ጥበቃ ሚንስትር ዶ/ር አሚር አማን የግል ስልካቸው ላይ ደውለን ኹነቶን ለማወቅ ያደረግነው ጥረት ለጊዜው ምላሽ ባለማግኘታችን አልተሳካም፡፡

ነገር ግን፣ የሚንስትሩ የቅርብ ሰዎች ጋር ደውለን የአገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ ቀደም ሲል ጀምሮ የጤና ጥበቃ ሚንስትር ሚንስትርነት ቦታን ለመያዝ በኢሕአዴግ እህት ድርጅቶችና በአጋር ፓርቲዎች ውስጥ ፖለቲካዊ ፍትጊያ እንዳለ ገልጸው፣ ሚንስትሩ በተለያዩ ፖለቲካዊ ጫናዎች ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ስለመወሰናቸው ግን ተጨባጭ መረጃ እንደሌላቸው ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡

(በጉዳዩ ላይ ተጨባጭ መረጃ እንዳገኘን በፍጥነት የምናሳውቅ ይሆናል፡፡)

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com