ግብፅ፣ ደቡብ ሱዳን እና ዑጋንዳ ኢትዮጵያ ላይ እያሴሩ ነው ተባለ

Views: 270

የግብጽ፣ የደቡብ ሱዳን እና የዑጋንዳ መሪዎች የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ በድብቅ እየመከሩ ነው፤ አስተባባሪዋም ግብጽ ናት ሲል የደቡብ ሱዳን የዜና ወኪል ዘገበ፡፡

የዜና ወኪሉ አንድ የቀድሞ የዑጋንዳ የደህንነት ሠራተኛ ያደረሰውን ባለ ሦስት ገፅ ዶክመንት ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ሦስቱ አገራት መጠነ ሰፊ ምክክር እና ሤራ በኢትዮጵያ ላይ በድብቅ እያካሄዱ እንደሆነ አውጥቷል፡፡

ዶክመንቱ እንደሚያሳየው፣ ሦስቱ አገራት በዲፕሎማሲ እና ወታራዊ መንገዶች አማካይነት በኢትዮጵያ ላይ የበለጠ ጫና ሊያሳድሩ እና ፍላጎቶቻቸውን ለማሳካት በምስራቅ አፍሪካ ክልል ውስጥ አንድነታቸውን እንዴት እንደሚያቀናጁ ያሳያል፤ ይህም የአብዱልፈታ አል ሲሲ መንግሥት በግብጽ መንበረ ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ፣ አፍሪቃ ላይ ሚሰሩት የዲፕሎማሲ ሥራ ውጤት ነው ብሏል፡፡

ይህ የደህንነት ሰው እንደሚለው፣ ዑጋንዳ በቀጠናው ካሉ የላይኛው የዓባይ ተፋሰስ አገራት ውስጥ የግብፅ የመጀመሪያ ተባባሪ ሆናለች፡፡ አንድ ሉዓላዊ ለሆነች ሀገር ተባባሪ መሆን ችግር የለውም፤ ነገር ግን ትብብሩ ችግር የሚፈጥረው በሌሎች አገራት ላይ ጉዳት ለማድረስ ሲሆን ነው ብለዋል፡፡

የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታ አል ሲሲ፣ የዑጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩሪ ሙሴቪኒ እና የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር፣ ኢትዮጵያ እየገነባቸው ያለችው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወደ ፊት እንዳይሄድ በአንድነት እያሴሩ ናቸው ሲል ባለ ሦስት ገፁ ዶክመንት ያስረዳል፡፡

የሦስቱም አገራት መሪዎች ለማሳካት የሚፈልጉት የራሳቸው ፍላጎት አላቸው፤ የግብፁ መሪ የአባይ ወንዝ ውሀን መቆጣጠርን መቀጠል ይፈልጋሉ፤ የዑጋንዳው መሪ ደግሞ ሳልቫ ኪር በሥልጣን እንዲቆዩ ስለሚፈልጉ ግብፅ መሪውን እንድታግዘው፤ የደቡብ ሱዳኑ መሪ ሳልቫ ኪር የወደ ፊት በሥልጣን የመቆየት እቅድ ደግሞ በዑጋንዳው መሪ ተስፋ የተጣለበት ነው ተብሏል፡፡

በሠነዱ ውስጥ የደህንነቱ ሰው እንደሚለው፣ ኢትዮጵያ ግድቡን እንዳትጨርስ ለመከላከል የታቀዱ ከባድ ቴክኒኮች እንዳሉም ይናገራል፡፡

በዕቅዱ መሠረት ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ለመዋጋት ከወሰነች ዑጋንዳና ደቡብ ሱዳን ግብፅን እንደሚረዷት ያስረዳል፡፡

የዑጋንዳው የስለላ ተቋም፣ ግብፅ የጦር መሳሪያዎችን ለደቡብ ሱዳን በድብቅ የሽፋን ሰርጦችን በመጠቀም እንደምትረዳም ሠነዱ ይናገራል፡፡

አል ሲሲ ሁልጊዜም መሳሪያዎችንና ጥይቶችን ወደ ጁባ በሁለት የተለያዩ መንገዶቸ ያቀርባል፤ አንደኛው በመድኃኒት ወይም በግብርና ምርቶች መልክ ይሰጣቸዋል ወይም ዑጋንዳን በመሐል ይጠቀምባታል፤ እነዚህ ሁሉ የሽፋን ሰርጦች ናቸው ብለዋል

ይህ የደህንነት ሰው፣ በዑጋንዳና በደቡብ ሱዳን መካከል ያሉትን ሚስጥሮች ለማጋለጥ የመጀመሪያው የባዕድ አገር ሰው ነው ሲል የዘገበው የደቡብ ሱዳን የዜና ወኪል ነው፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com