በሳዑዲ የሞት ፍርድ የተላለፈባቸው ኢትዮጵያውያን ኤምባሲው ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ጠየቁ

Views: 174

በሳዑዲ ዐረቢያ ማረሚያ ቤት በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተከሰው ሰሞኑን የሞት ፍርድ የተላለፈባቸው ሁለት ኢትዮጵያውያን ‹‹ራሳችንን ለመከላከል የሚያችል አቅም ስለሌለን፣ በሳዑዲ ዐረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጠበቃ አቁሞ ይከራከርልን›› ሲሉ ጥያቄያቸውን አቀረቡ፡፡

ሠኢድ መሀመድ እና ያህያ አሊ የሚባሉት እነዚህ ኢትዮጵያውያ፣ ምንም በማያውቁትና ባልፈፀሙት ወንጀል ለሦስት ዓመታት ማረሚያ ቤት እንደቆዩና ለ16 ጊዜ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን፤ ሆኖም ግን ፍርድ ቤቱ 3 ጊዜ ብቻ ቃላቸውን ከተቀበላቸው በኋላ ይህን ውሳኔ እንዳሳለፈባቸው ተናግረዋል፡፡

የሞት ፍርድ የተፈረደባቸውን ጨምሮ በማረሚያ ቤቱ የ20 ዓመት ፍርድ የተላለፈበትን  ወጣት ጉዳዩ የሚመለከተው የኤምባሰው ተወካይ በጎበኛቸው ወቅት ነው ታራሚዎቹ ኤምባሲው እንዲረዳቸው የጠየቁት፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው በሳዑዲ ዐረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሞት ፍርድ ውሳኔውን ኮፒ በመያዝ በቀጣይ ኢትዮጵያውያኑ የፍርድ ውሳኔውን መቃወም የሚያስችላቸውን ኹኔታ በማመቻቸት፤ የይግባኝ ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ በማድረግ፤ እንዲሁም ጠበቃ ቀጥሮ ጉዳዩ እንዲታይ የሚቻለውን እገዛ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

እነዚህና እና ሌሎች የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸውን ዜጎች ኤምባሲው የሀገሪቱን ሕግ በመከተል ከሳዑዲ ዐረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከሚመለከተው የመንግስት ኃላፊዎች ጋር በመሆን መፍትሔ እያፈላለገ ነው፡፡

መንግስት ታራሚዎችን በምህረት እንዲለቅ ዲፕሎማሲያዊ ውትወታ እያደረገ እንደሚገኝም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡

ኤምባሲው በሀገሪቱ ማረሚያ ቤቶች ያሉ ኢትዮጵያውያን ታራሚዎች ስላለባቸው ችግር፣ ስለተከሰሱበት ጉዳይ እና ስለ ፍርድ ጉዳያቸው የራሱን ጉዳይ አስፈጻሚዎች በመመደብ ክትትል እንደሚያደርግም ገልጿል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com