ግጭት ቀስቃሽ ዘገባዎችን የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙኃን በብሮድካስት ባለስልጣን ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

Views: 123

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ዘገባዎችን የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙኃን አደብ ካልያዙ ሊዘጉ እንደሚችሉ በመግለፅ ማስጠንቀቂያ ሰጠ፡፡

ባለሥልጣኑ ሚዛናዊነት የሚጎድላቸውንና ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ መረጃዎችን በማሰራጨት የተጠመዱ የመገናኛ ብዙኃን ያላቸውን ተቋማት ማስጠንቀቂያ መስጠት እንደጀመረ አሳውቋል፡፡

በማስጠንቀቂያው መሠረት ቶሎ ወደ አግባባዊ ሙያዊ ሥራ ካልተመለሱ፣ የብዙኃን መገናኛ ተቋሙን እስከመዝጋት የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ በደብዳቤ እንዲያውቁት እየተደረገ መሆኑንም ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡

የብሮድካስት ባለሥልጣን የአገር ህልውና አደጋ ውስጥ ከመውደቁ በፊት መገናኛ ብዙኃኑን አደብ እንዲያስገዛም የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳስቧል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም፣ የሕግ መስመር እየጣሱ ኹከትና ብጥብጥ በሚያስተጋቡ መገናኛ ብዙኃን ላይ ባለስልጣኑ እርምጃ አልወሰደም ሲሉ ወቀሳ አቅርበዋል፡፡

በቴሌቪዥንና ሬዲዮዎች ሥራ ክትትል 16 የሕግ ጥሰቶች እንደተገኙ በባለሥልጣኑ ሪፖርት ቢጠቀሰም፣ ጥሰቶችና ግድፈቶች እንዳልታረሙና የችግሩ ምንጭ የሆኑ መገናኛ ብዙኃን ላይም እርምጃ እንዳልተወሰደ እንደራሴዎቹ ኮንነዋል፡፡

ባለስልጣኑም በበኩሉ ለመገናኛ ብዙኃኑ የተሻለ ነፃነትና ትዕግስት እየተሰጠ ቢሆንም፣ ጥቂት ተቋማት ነፃነታቸውን በአግባቡ እየተጠቀሙበት አይደለም፤ ከዚህ ተግባራቸው ካልታረሙ መገናኛ ብዙኃኑን ለመዝጋት ይገደዳል ሲልም አሳውቋል፡፡

(ዘገባው የአሐዱ ቴሌቪዥን ነው)

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com