በምዕራብ ወለጋ ውጊያ እየተካሄደ ነው ተባለ

Views: 148

በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ የቤጊ እና ቆንዳላ ወረዳ፣ በሀገር መከላከያ ሠራዊትና በታጠቁ ኃይሎች መካከል ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጹ፡፡

መንግሥት በአካባቢው ስለተፈጠረው ኹኔታ ለጊዜው መግለጫ ያልሰጠ ሲሆን፣ እየተካሄደ ያለው ውጊያ ከታጠቁ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አንድ ክንፍ ጋር መሆኑን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

በሀገር መከላከያ ሠራዊት እና በኦነግ ታጣቂ ክንፍ ውጊያው የተቀሰቀሰው ከአራት ቀን በፊት ጀምሮ መሆኑንም ነዋሪዎች አሳውቀዋል፡፡

ከቀናት በፊት የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኦነግ ታጣቂዎችን በመክበብ ለመማረክ ሙከራ ሲያደርጉ እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ኢትዮ-ኦንላይን ያነጋገራቸው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ፣ ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ገልፀው፤ አካባቢው ከወራት በፊት ጀምሮ በአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ እየተመራ መኖኑንም ጠቁመዋል፡፡

በዚህ ምክንያትም፣ ፓርቲያቸው በምዕራብ ወለጋ፣ በምስራቅ ጉጂ እና በምዕራብ ጉጂ ዞኖች ተንቀሳቅሶ ለመስራት መቸገሩን አስታውቀዋል፡፡

የምስራቅ ጉጂ ዞን የኦፌኮ ተጠሪ ከአምስት ወራት በፊት አስቀድሞ በኮማንድ ፖስት ካምፕ ውስጥ ታስረው እንደሚገኙም አቶ ጥሩነህ ገልፀዋል፡፡

በሀገር መከላከያ ሠራዊትና በታጣቂ የኦነግ ክንፍ የሚካሄደው ውጊያ ዛሬም መቀጠሉንና የንፁሃን ሰዎች ሕይወት እንደጠፋም የጀርመን ድምፅ ራዲዮ ዘግቧል፡፡

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com