ከተመረቁ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ውስጥ የተወሰኑት አገልግሎት መስጠት አልጀመሩም

Views: 162

ተመርቀው አገልግሎት የማይሰጡ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት፣ በአፋጣኝ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ፤ የተፈጥሮ ሀብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ይችላሉ ተብለው ከተከፈቱ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ውስጥ፣ የተወሰኑት ለኅብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት እንዳልጀመሩ ባደረግኩት የመስክ ምልከታ አረጋግጫለሁ ሲል ነው ቋሚ ኮሚቴው ያሳሰበው፡፡

የሰቆጣ፣ ጎንደርና መቀሌ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች አገልግሎት ከማይሰጡት መካከል ይገኙበታል ሲል ቋሚ ኮሚቴው ለአብነት ያህል ጠቅሷል፡፡

የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ ሲናገሩም “በሰቆጣ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ላይ ያጋጠመው ችግር የጉድጓዱ ውኃ የመስጠት አቅም አነስተኛ ስለሆነ ነው” ብለዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ወደ ጥናት ተገብቶ የገጸ- ምድር ውኃ ለማምረት እየተሠራ መሆኑን በመናገር፣ የጎንደርን የመጠጥ ውኃ ችግር በዘላቂነት የሚፈታው የመገጭ ግድብ ነው ተብሏል፡፡

ችግሩ እንዲፈታም ከአማራ ከክልል ውኃ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ጋር እየሰራን ነው በማለት ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

የመቀሌን የመጠጥ ውኃ ችግር አስመልክተውም ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ  የፕሮጀክቱ አቅምና ውኃ ፍላጎት አለመጣጣም የፈጠረው ችግር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታትም ከቻይና መንግሥት በተገኘ ብድር ጥናት እየተሠራ እንደሚገኝ ዶክተር ኢንጂነር ስለሽ መናገራቸውን የዘገበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com