ቅዱስ ሲኖዶስ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ተወያቶ ውሳኔ አሳለፈ

Views: 223
  • ስለ-ሠላም ታስተምራለች፤ ጥፋተኞች ሕግ-ፊት እንዲቀርቡ ጠይቃለች
  • በቋንቋዎች ሁሉ እኩል ታስተምራለች!

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

በዜጎች መካከል የተፈጠረው መገዳደል፣ መጎዳዳት፣ መፈናቀል እና ስደት ሊቆም ይገባዋል፤ መንግሥት ለዜጎች ብርቱ ጥበቃ እንዲያደርግ እና ጥፋተኞችንም በሕግ ፊት አቅርቦ እንዲጠየቁ እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡

በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረ ኹከትና ግጭት፣ ተጎጂ ሰዎች በዘላቂነት የሚያቋቁም እርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ እንዲቋቋም ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ቤተክርስቲያኒቱ ሀዋሪያዊ አደረጃጀት እንዳላት የጠቀሰው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ባለችበት ሥፍራ ሁሉ የልጆቿንና የሕዝቦቿን ፍላጎት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ አገራት እኩል ታገለግላለች ብሏል፡፡

የቤተክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ተከታዮች ባሉበት ሥፍራ ባሉ ቋንቋዎች ሁሉ ሀዋሪያዊ አገልግሎቷን ማጠናከር እንዲያስችላት፣ አንድ የቋንቋዎች ማሰልጠኛ ማዕከል ተቋቁሞ አገልጋዮች የአማኞችን የአፍ መፍቻ ቋንቋ አውቀው- እንዲያሳውቁ ለማድረግ ጥረት እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ማሳለፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ቤተክርስቲያኗ መንፈሳዊ ትምህርቷንና ሀዋሪያዊ አገልግሎቷን በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ሁሉ እንደምትሰጥ የገለጸው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ አገልጋዮቿ እና ተገልጋይ ልጆቿ በአግባቡ እንዲግባቡ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ለማስተማር የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንድትቀጥል ውሳኔ ማሳለፉን የቤተክርስቲያኗ ዜና ምንጫችን ለኢትዮ-ኦንላይን አሳውቀዋል፡፡

ቤተክርስቲያኒቱ ልጆቿ በሚገለገሉበት በሀገር ውስጥ እና በውጪ አገራት ቋንቋዎች  ማስተማሯንና መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠቷን አጠናክራ እንድትቀጥል ውሳኔ ያሳለፈው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በምሥራቅ አፍሪቃ- ኪ-ሲዋኋሊ ቋንቋ፣ በደቡብ አፍሪቃ ዙሉ፣ ጽዋና እና ቆሳ ቋንቋዎች፤ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በዓረቢኛ ቋንቋ፣ በአውሮጳና አሜሪካን አገራት በእንግሊዝኛ ቋንቋ፣  በጃማይካ፣ ትሪኒዳድ-ቶቤጎ እና አጎራባች አገሮች ባሉ ቋንቋዎች ሁሉ ሀዋሪያዊ አገልግሎቷን አጠናክራ እንድትቀጥል ውሳኔ ማሳለፉን ገልጸውልናል፡፡

ቤተክርስቲያኗ፣ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ የኖቤል ሽልማት ላይ ያላትን አድናቆት ገልፃ፣ ወደፊት ጠቅላይ ሚንስትሩ ሥለ-ሠላም የበለጠ እንዲሰሩ ድጋፏን ትቀጥላለች፡፡

የሕዳሴ ግድብ ተፋጥኖ ተጠናቆ፣ ግድቡ አገልግሎት እንዲጀምር፤ ቤተክርስቲያኒቱ አስፈላጊውን ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አሳውቃለች፡፡

በኢትዮጵያ እና ሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተጀመረው ሀዋሪያዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ውሳኔ አሳልፏል- ቅዱስ ሲኖዶስ፡፡

ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም የተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ፣ ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም መጠናቀቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com