በኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነት ሥጋት እየጨመረ ነው ተባለ

Views: 267

በኢትዮጵያ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የ‹‹ሣይበር›› ጥቃት እየጨመረ መሞጣቱን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አሰታወቀ፡፡ ጥቃቱ በግለሰቦች፣ በተቋማት እና በአገር እና መንግሥት ላይ ያነጣጠረ ነው- ተብሏል፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ፣ 791 የሳይበር ጥቃቶች መፈጸማቸውን ኤጅንሲው ያስታወቀ ሲሆን፣ የኢንፎርሜሽ ቴክኖሎጂ መምህር የሆኑት መምህር ዘላለም መንግሥቱ-ም ችግሩ ከእለት ወደ እለት በተቋማት እና በግለሰቦች ዘንድ እየታየ መምጣቱን ለኢትዮ-ኦንላይን ገልጸዋል፡፡

መመህር ዘላለም ሲናገሩም፣ የሳይበር ጥቃት የሀገርን ወይም የተቋማትን መረጃ በተደራጀ ቡድን፣ በግለሰብ አልያም በአንድ አገር አማካይነት የሚከወን አደገኛ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

የሳይበር ጥቃት መረጃን ያለ-ሕጋዊ ፈቃድ ከአንድ አካል፣ ተቋም ወይም ግለሰብ በመመዝበር ለሌላ ተቀናቃኝ አካል የሚያደርስ፣ አሊያም ትልልቅ ተቋማት በዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚከውኑትን ሥራ ማስተጓጎል አሊያም ማበላሸት መሆኑን የተናገሩት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምህር አቶ ዘላለም፤ ችግሩ ከፍ ሲልም የሀገርን ደህንንት የሚገዳደር ወይም ሉዓላዊነትን አሳልፎ የሚሰጥ ነው ሲሉ ነው ለኢትዮ-ኦንላይ የገለጹት፡፡

በሳይበር ጥቃት በሀገር ደረጃ በሚስጢር የሚያዙ መረጃዎች ባልተፈቀደላቸው አካላት ብርበራ ተከናውኖ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለተቀናቃኝ አካል የሚያደርስ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

እንደዋዛ በሚታይ የሳይበር ጥቃት እንኳ፣ በግለሰቦችና በሕዝብ መካከል የእርስ በእርስ አለመተማመንና ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሳይበር ጥቃቶች  በግለሰብ እና በተቋማት ላይ እየተፈጸሙ መሆኑን የተናገሩት መምህር ዘላለም፣ መንስዔዎቹም የቴክኖሎጂዎች በየጊዜው መቀያየርና ልውጥውጥ መሆን አንደኛውም ምክንያት ሲሆን፤ በዘርፉ የሰዎች ግንዛቤ አናሳ መሆን ደግሞ ለጥቃቱ መባባስ ከ80 እስከ 90 በመቶ ድርሻ ይይዛል ብለዋል፡፡

በተለይም አላስፈላጊ ሶፍትዌሮችን በኮምፒውተርና በስልክ ቀፎ ላይ መጫን አልያም መጠቀም፤ የሚሥጢር ቁልፎችን ቀላል ማድረግ፣ በዘርፉ ሥልጠናዎችን አለመውሰድ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል- መምህር ዘላለም፡፡

መፍትሔውም ይላሉ መምህር ዘላለም፣ ስለምንጠቀመው ‹‹ሶፍትዌር›› የዘርፉን ባለሙያዎች ማማከር፣ ሥልጠና መውሰድ፣ ለግልሰብም ይሁን ለተቋማት የተሻሻሉ ‹‹አንቲ ቫይረስ››ን መጠቀም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም፣ ጠንካራ እና በየወሩ የሚቀየር የሚስጥር ቁልፎችን ወይም ‹‹ፓስዋርድ›› መጠቀም  መፍትሄ ይሆናል ሲሉም መምህር ዘላለም አብራርተዋል፡፡

ከዛሬ ጥቅምት 24 ቀን እስከ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ‹‹የሳይበር ደህንነት ግንዛቤዎን በማሳደግ ራስዎን ከሳይበር ጥቃት ይከላከሉ›› በሚል መርህ ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ሳምንት በመከበር ላይ ነው፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com