የኦሮሞ አመራር ሕብረ-ብሄራዊ ፌደራሊዝም ሥርዓትን ለማጠናከር እሰራለሁ አለ

Views: 61

በአንድ ጥላ ስር የተሰባሰበው የኦሮሞ አመራር (ጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ)፣ ሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓትን ለማጠናከር እሰራለሁ አለ፡፡

ስብስቡ፣ እሁድ ጥቅምት 23 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ፣ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር ማድረጉ ታውቋል።

አሁን ያለውን ሕብረ-ብሄራዊ ፌደራሊዝም ሥርዓት ለማጠናከርና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ እንሰራለን፤ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ የሚያደርገው ጉዳይ የኦሮሞን ህዝብ እና የሀገሪቱን ብሔር-ብሔረሰቦች ጥቅም ማስጠበቅ ላይ ትኩር ማድረጋችን ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እኩልነት፣ ነፃነት እና የህዝቦች ወንድማማችነት የተረጋገጠበት፣ ዴሞክራሲ ያበበበት እውነተኛ ሕብረ-ብሔራዊ ፌደራሊዝም ሥርዓት እንዲተገበር ለማድረግ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በመስማማት አቅጣጫዎችንም ማስቀመጡን አሳውቋል።

በሌላም በኩል፣ በኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል አለመግባባት ከተፈጠረ፣ በውይይት ከመፍታት ባለፈ፤ አንዱ በአንዱ ላይ ዘመቻ መክፈት ለማንም እንደማይጠቅም ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ስብስቡ ገልጿል፡፡

“አሁን ያለንበት ወቅት በጣም ወሳኝ በመሆኑ፣ እያንዳንዱ እርምጃ የኦሮሞን ህዝብም ሆነ የሀገሪቱን ብሔር ብሔረሰቦች የነገ ተስፋ ወደ ብርሃን የሚያሻግር አልያም ለከፍተኛ አደጋ ሊዳርግ የሚችል” መሆኑንም ስብስቡ በመግለጫው ላይ አስፍሯል።

ከዚህ ቀደም፣ እንደዚህ ዓይነት በአንድ ጥላ ስር የተሰባሰበ የኦሮሞ አመራር ቢኖር ኖሮ፣ በፓርቲዎቹ መካከል የሰፈነው ጥርጣሬ፣ ዛሬ ያለበት ደረጃ ላይ አይደርስም ነበር ብለዋል፡፡

ከዚህ በኋላም  በአንድ ጥላ ስር የተሰባሰበው የኦሮሞ አመራርን በማጠናከር፤ በመካከላቸው ለተፈጠሩ እና ለሚፈጠሩ ችግሮች፣ ስብስቡ በጋራ በመሆን መፍትሄ የማፈላለግ ስራ ይሰራል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም፣  በኦሮሚያ ክልል የሚስተዋሉ የሠላም ችግሮችን፣ ከሰሞኑ በክልሉ የተከሰቱ የፀጥታ ችግሮች መንስዔዎች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ፤ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የስራ ክፍፍል ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

እንዲሁም መጭው ሀገራዊ ምርጫ ሠላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሓዊ እንዲሆን ፓርቲዎቹ ምን አይነት መንገድ መከተል እንዳለባቸው የሚያሳይ አጭር ጥናት ከተካሄደ በኋላ፣ ሰፊ እና ጥልቅ ውይይቶችን በማካሄድ ቀጣይ አቅጣጫዎችን በጋራ ለማስቀመጥም ውሳኔ ማሳለፉ በመግለጫው ላይ ተብራርቷል፡፡

በመጨረሻም፣ እንደ ሀገር የተጀመረውን ለውጥ በጠንካራ እና አስተማማኝ መሠረት ላይ ለማቆም፣ ከሁሉም የሀገሪቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ቀጣይነት ያለው ውይይት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በማመንም፤ በሀገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ ከሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር በጋራ መስራት የሚቻልባቸውን ኹኔታዎች መፍጠር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር ለማድረግም ተስማምተዋል።

(ዘገባው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ነው)

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com