አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፉ ተጠናክሮ ቀጥሏል

Views: 131

• የማሰባሰባሰቢያ ቀን ተራዘመ

በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በችግር ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን በፍጥነት ለመርዳት የተለያዩ የአስቸኳይ ግዜ እርዳታዎችን በሀገር ፍቅር ቴአትር እየተካሄደ ያለው ሰብዓዊ እንቅስቃሴ እስከ መጪው ማክሰኞ ድረስ ሊራዘም መቻሉ ታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ በነቂስ በመውጣት ድጋፉን እየገለጸ በመሆኑ፣ በሳምነቱ መጨረሻ ሊደርሱ የሚችሉ ድጋፎችን ለማሰባሰብ እንዲያስችል ቀነ ገደቡን ለማራዘም መገደዱ ታውቋል፡፡

ዛሬ ቅዳሜ ከአዛውንት እናት-አባቶች ጀምሮ እስከ ታዳጊ ሕፃናት ድረስ ለወገኖቻቸው በፍላጎታቸው ድጋፍ ለማድረግ በቦታው መገኘት የቻሉ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ ታዳጊ ሕፃን ሩት ከምትለብሳቸው ልብሶች ውስጥ የተወሰኑነትን ለወገኖቿ ለማካፈል በቦታው መገኘቷን ለኢትዮ-ኦንላይን ዘጋቢ ገልፃለች፡፡

በ25 በጎ ፍቃደኛ አባላት ለጊዜያዊ አስቸኳይ ሰብዓዊ ዘመቻ የተቋቋመው “የሰብዓዊ ድጋፍ ጥምረት” ካለፈው ሰኞ ጥቅምት 17 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ከህብረተሰቡ የሚደረገልትን ድጋፍ ሲያሰባስብ የቆየ ሲሆን፣ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ያለ ኢትዮጵያዊ በነቂስ ተሳትፎ በሰጠው ቀና ምላሽ፣ የታሰበውን ግብ በመምታቱ፤ በዚህ በጎ ምግባር ላይ ለተሳተፋችሁ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና ማህበራት እንዲሁም የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በሙሉ የላቀ ምስጋናውንም አቅርቧል፡፡

እስከ አርብ ጥቅምት 21 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ የተሰበሰቡ ምግቦች እና ንብረቶች በበቂ ሁኔታ ወገኖቻችንን ለማገዝ በቂ በመሆኑ፣ እርዳታው ለታቀደው ግብ ለማዋል የማጓጓዝ ስራ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሎጅስቲክ ድጋፍ መጀመሩ ታውቋል።

ከጥምረቱ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ በቀጣይ 5 ቀናት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ለወገኖቻችን በማድረስ ሁሉንም መረጃ የምናሳውቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዛሬ ቅዳሜ ጥቅምት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ማክሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ፣ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ ለተጎዱ እና አፋጣኝ እርዳታ ለሚያሻቸው ወገኖቻችን በቀይ መስቀል በኩል እርዳታዎች እንዲደርሱ ቀጣይ ልገሳዎች ለዚህ ተግባር የምናውል መሆናችንን ለማሳወቅ እንወዳለን ብሏል።

በዚህም መሠረት ከቅዳሜ ጥቅምት 22 ቀን 2012 ዓ.ም እስከ ማክሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በሀገር ፍቅር ቴአትር ብቻ የሚሰበሰቡ የአስቸኳይ ግዜ ምግቦች እና ቁሳቁሶች በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ ችግር ላይ ለሚገኙ ወገኖቻችን አስቸኳይ እርዳታ የሚውል መሆኑን እንድትገነዘቡ በታላቅ ትህትና እናሳውቃለን በማለት “የሰብዓዊ ድጋፍ ጥምረት” ገልጿል።

በመሆኑም፣ እስከ መጪው ማክሰኞ ድረስ ሁሌም ፈጥኖ ደራሽ የሆነው ወገናችን በቀጣይ 3 ቀናት በሚኖረን የእርዳታ ማሰባሰብ ተግባር ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪያችንን እያቀረብን በኢትዮጵያዊ ባህላችን፣ በሰብዓዊ ስሜቶቻችን ዛሬም ለወገናችን በልገሳዎች ላይ በንቃት እንድትሳተፉ ጥሪ እናቀርባለን ብሏል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com