ፌዴራላዊ ሥርዓቱ የተተገበረበት መንገድ ዜጎችን ለሰብዓዊ መብት ጥሰት አጋልጧል ተባለ

Views: 201

በኢትዮጵያ ላለፈው ሃያ አምስት ዓመታት ፌዴራላዊ የመንግሥት ሥርዓት የተተገበረበት መንገድ፣ ዜጎችን ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጋላጭ ማድረጉ ተገለጸ::

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ፣ ‹‹ዜጎችን ለሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭ ያደረገው ፌዴራላዊ ሥርዓቱ የተተገበረበት መንገድና የፌዴራል ሥርዓቱ የመንግሥት አወቃቀር አንዱ ችግር ነው›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲ አወቃቀሩም ሌላው ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም የጠቆሙ ሲሆን፣ በተለይ ማንነት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱም ለግጭት ዳርጓል ብለዋል- ዶ/ር ዳንኤል፡፡

ኮሚሽነሩ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አወቃቀር፣ የመንግስት አወቃቀርና ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ መፈተሽ አለብን፤ የፖለቲካ አወቃቀራችን በተፈጥሯቸው የአግላይነት ጸባይ ስላላቸው፣ በውጤታቸው ደግሞ ለግጭት፣ ለብጥብጥና ለእርስ በእርስ አመጽ የሚጋብዙ ሆነው የሚታዩ ስለሚመስሉ ጉዳዩ ሊመረመር፣ ሊጠና እና ሊታይ ይገባዋል ብለዋል፡፡

የፖለቲካ መሪዎችም በእዚህ ጉዳይ መወያየት መጀመር የሚገባቸው ይመስለኛል በማለት፣ በእኔ እምነት ለሰብዓዊ መብት ተጋላጭ ያደረገው ራሱ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ሳይሆን፣ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ የተተገበረበት መንገድና የፌዴራል ሥርዓቱ የመንግሥት አወቃቀር አንዱ ሊሆን ይችላል በማለት አስረድተዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲ አወቃቀሩ፣ በተለየ ማንነት ላይ (የዘር ማንነት፣ የብሄር ብሄረሰብ ማንነት፣ የአካባቢ፣ የሃይማኖት ማንነት ላይ የተመሰረቱ አደረጃጀቶች) ላይ የተመሰረተ ፓርቲ፣ ለግጭት ስለሚዳርግ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች እንዲህ አይነት የፖለቲካ አደረጃጀት በሕጎቻቸው አልፈቀዱም ወይም በግልጽ ከልክለዋል ሲሉም ኮሚሽነሩ አብራርተዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ አይነት የፖለቲካ አስተዳደር እንዳለን ይታወቃል፡፡ ታሪካዊ መሰረትና ምክንያት አለው›› ብለዋል፡፡

ዶክተር ዳንኤል፣ እስካሁን የመጣንበት መንገድ ያስገኘው ውጤትና የፈጠሩት ተግዳሮቶችም አሉት፤ ከተደረሰበት የፖለቲካ ምዕራፍ አንጻር ሂደቱን መርምሮ ችግሮችና ያስገኘውን ውጤት በማስመልከት ግልጽ ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡

ለሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭ ያደረገ የመንግሥት አወቃቀር ካለውም አወቃቀሩን መፈተሽ ያስፍልጋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

‹‹ይህ ማለት ግን የፌዴራላዊ አስተዳደርን ማፍረስ ማለት አይደለም፣ ኢትዮጵያ ካላት ብዝሃነት አንጻር እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ብሄር ብሄረሰብ ላላቸው አገራት የፌዴራላዊ አስተዳደር ተገቢ አስተዳደር ነው በማለት አስታውቀዋል፡፡

ፌዴራላዊ አወቃቀር ህዝቦች፣ ሰዎች፣ ዜጎች በየአካባቢያቸው የራሳቸውን ጉዳይ በየራሳቸው የሚያስተዳድሩበት መንገድ መሆኑን በመጠቆምም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ የሆነው አስተዳደር ግን በተለይ ከብሄር ብሄረሰብ ማንነት ጋር በጣም የተቆራኘ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በተለያዩ ክልሎችና በክልሎቹ ውስጥ ባሉ የተለያዩ የማንነት ጥያቄዎች እና የድንበርና የወሰን ልዩነት ላይ እጅግ አወዛጋቢ ክርክር የፈጠረ መሆኑ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጋላጭ ማድረጉንም ዶክተር ዳንኤል አልሸሸጉም፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታዩ ግጭቶች ከማንነት ጥያቄና ከአካባቢ እና ከድንበር ጉዳይ ጋር ተያይዞ ‹‹ይህ የእኔ አካባቢ ነው፣ ይህ አካባቢ የአንተ አይደለምና ከእዚህ ትወጣለህ፣ የአንተ ድንበር እዛ ጋር ነው›› ከሚሉ ጥያቄዎች ጋር የተያያዘ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

አገራችን ውስጥ በየክልሎቹ ብቻ ሳይሆን፣ በየቀበሌዎቹና በየወረዳዎቹ ደረጃ ያለ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን፤ የአስተዳደር ወሰን መሆኑ ቀርቶ ልክ ከአጎራባች አገራት ጋር እንዳለ አይነት የድንበር ወሰን ጋር የሚመሳሰል እየሆነ መጥቷል ብለዋል፡፡

አሁን የተፈጠሩት ግጭቶችም በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የአስተዳደር ወሰኖችን እንደ ድንበር በመቁጠር ከሌላ አገር ጋር የተፈጠረ ችግር የሚመስል አይነት አዝማሚያ እንደሚታይበት ኮሚሽነሩ ገልጽው፤ የፌዴራል ሥርዓቱን በሚያጠንክር መልኩ የአስተዳደር ወሰኖችና የማንነት ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ተወያይቶ የፖለቲካ መፍትሄ መፈለግ ይሻላል ሲሉ መመክከራቸውን የዘገበው አዲስ ዘመን ነው፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com