በኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን ክልሉ እንዲያቋቁም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ጠየቁ

Views: 72

በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረ ግጭት ምክንያት፣ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉና በየዕምነት ተቋማት ተጠልለው የሚገኙ ዜጎችን ክልሉ በአፋጣኝ መልሶ እንዲያቋቁም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ጠየቁ፡፡

አቶ ተመስገን ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ የአማራ ሕዝብ ከክልሉ ውጭ በአብዛኛው የአገሪቷ አካባቢዎች ከሁሉም ጋር በጋራ መኖር የሚችልና የዜጎችን በነፃነት ተንቀሳቅሶ መሥራት የሚደግፍ ነው።

ያም ሆኖ በተለያዩ ጊዜያትና አካባቢዎች የብሔርና የሃይማኖት መልክ የሚይዙ ግጭቶች እየተቀሰቀሱ ንጹሐን ዜጎች ሰለባ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ‹‹የፀጥታ ኃይል ባለበትና በፖለቲካ ልዩነት ንጹሐን ዜጎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት የሚወገዝ ነው›› ብለዋል።

‹‹ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭትም ተዋልዶና ተሳስሮ የሚኖር ሕዝብ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን በመጻረር በንጹሐን ላይ የደረሰውን ጥቃት የክልሉ መንግሥት ያወግዘዋል›› ብለዋል።

ወደ አገር ልማት የሚገባው ቅድሚያ የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ሲቻል መሆኑን ገልጸው መንግሥት ሕግ የማስከበር አቅሙን መወጣት እንደሚገባው አሳስበዋል።

በግጭቱ ሁሉም ሕዝብ ተጎጂ መሆኑን ገልጸው በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት ንጹሐን ዜጎች ላይ ጥቃት መድረስ እንደሌለበትም አስገንዝበዋል።

የክልሉ መንግሥት ከሰሞኑ በደረሰው ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች በአፋጣኝ ማቋቋም እንዳለበትም አሳስበዋል።

የአማራ ክልል መንግሥት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለማቋቋም ለሚደረገው ተግባር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com