ለችጋር አዲስ መፍትሔ የሚሻ ጉባዔ ሊካሄድ ነው

Views: 196
  • ተቀማጭነቱ በአዲስ አበባ የሆነ አዲስ ተቋም ይመሰረታል

ኢትዮጵያን ጨምሮ በከፍተኛ ደረጃ ለምግብ ዕጥረት የሚጋለጡ አገራት ከረሃብ አደጋ ሊታደግ የሚችል ዓለም አቀፍ ጉባዔ በመጪው ሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይከፈታል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ከብሔራዊ  የአደጋ  ስጋት ሥራ  አመራር ጋራ በመቀናጀት በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባዔ መሪ ቃል  “Transformative Food Assistance for Zero Hunger” በሚል እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በጉባዔው የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ፣ የሰላም ሚንስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ይገኛሉ ተብሏል፡፡

በጉባዔው በማጠቃለያ ላይ፣ ተቀማጭነቱ በአዲስ አበባ የሚሆን፣ “Global Center for Transformative Food Assistance“ ተብሎ የሚጠራ አዲስ ተቋም እንደሚመሰረት ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከ26 አገራት በላይ የተወጣጡ፣ በሦስት ምድብ ሊከፈሉ የሚችሉ ከ200 በላይ ተሳታፊዎች በጉባዔው እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ ተሳታፊዎቹ፣ ከፖሊሲ አውጪዎች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በምግብ እርዳታ ውስጥ ተሳታፊ ከሆኑ ባለሙያዎች እና ከታዋቂ ዓለም አቀፍ ከፍተኛ የትምህር ተቋማት የተወጣጡ ምሁራን፣ ተመራማሪዎች እና አጥኚዎች የተካተቱበት ነው፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ጽ/ቤት ኢትዮ ኦንላይን ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ የሦስቱ ቀን ጉባዔ ዋና ዋና ተብለው የተቀመጡ ዓላማዎች አራት ናቸው፡፡

በዋነኝነት የጉባዔው ጥቅል ዓላማ በመላው ዓለም ከምግብ ዕርዳታ ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን ጊዜ ያለፈት የምግብ እርዳታ አቅርቦትን መለወጥ የሚያስችሉ አዳዲስ ልምዶችን በማሰባሰብ፣ በቀጣይ በዘልማድ ሲካሄድ የነበረውን ድጋፍ በዘላቂነት ለመፍታት የሚያግዙ አቅሞችን ለማዳበር ነው፡፡

በዚህም መሠረት ከምግብ እርዳታ ጋር በተያያዘ በብሔራዊ፣ በአካባቢያዊ እና ዓአለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ እና ይዘት ለይቶ በማስቀመጥ የረሃብ አደጋን ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት የሚያስችል ግንዛቤን መፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ጉባዔው የተለያዩ አገር ልምዶችን  መሠረት በማድረግ የሚመክር ሲሆን፣ የምግብ እርዳታዎች አዋጪ፣ የታለመላቸውን ግብ የሚመቱ፣ የረሃብ አደጋን የሚያስወግዱ እና ዘላቂ ልማትን ዕውን የሚያደርጉበት አማራጮች የሚፈተሹበት እና በዘርፉ ስኬታማ አገሮች ልምድ የሚገመገምበት ሌላው የጉባዔ ዓላማ መሆኑ ታውቀዋል፡፡

አገሮች ከምግብ እርዳታ ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን ፖሊሲ ፈትሸው ተስማሚ የፖሊሲ ሪፎርም እንዲያደርጉ፣ ይህንንም የሚያስተገብሩ አዳዲስ ተቋማትን እና የኢንቨስትመንት እድሎችን በሚፈጥሩበት ሁኔታ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ከጉባዔው አጀንዳዎች የሚጠበቅ ነው፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com