ዳቦ! ለምን ከስንዴ ብቻ?

Views: 242

ስንዴ ዳቦ ቢሆንም፤ ዳቦ ከስንዴ ብቻ ነው- ያለው ማን ይሆን!?

መነሻ ጉዳይ፡-

የስንዴ እጥረት በመድረሱ ምክንያት፣ በከተሞች ውስጥ የዳቦ እጥረት ተከሰተ፤ ዳቦ ቤቶች የዳቦን ዋጋ እስከ እጥፍ ድረስ ጨመሩ፡፡  መንግሥት፣ ስንዴ ከውጭ ገበያ ሳይቀር ፍለጋ ውስጥ ገባ፡፡ ከዱባይ የተገዛው ስንዴ ጅቡቲ ወደብ ከደረሰ በኋላ እንኳን፣ ለማጓጓዝ ችግር ተከስቶ እስከ መበላሸት ደረሰ ተባለ፡፡ (ማጣቀሻ አንድ እና ሁለት ላይ ሪፖርተር ጋዜጣ ያወጣውን ተመልከቱ)፡፡

የግብርና ባለሙያዎች ስንዴን በመስኖ ወደ ቆላ ሄደን እናሳርሳለን ሲሉም ተደመጡ፡፡ በቅርቡም በጠቅላይ ሚንሥትሩ ግዙፍ የዳቦ ማምረቻ ሊከፈት መሆኑ ተወሳ፡፡ ይህ ጉዳይ በእውነት እረፍት የሚነሳ ነው፡፡  ስለዚህ፣ የተባለው ላይ ሐሳብ መስጠት፣ ወይም ሌሎች ያልተነገሩን መፍትሔዎችን መጠቆም ግድ ይላል፡፡

1ኛ. የተመረተውን የስንዴ ምርት በሙሉ ተመግበነዋል እንዴ? 

 • የተመረተውን የስንዴ ምርት በሙሉ ተመግበነዋል ወይስ ከቤት እንስሳት ጋር ተሻማን?
 • የተመረተው የስንዴ ምርት እና የፍርኖ-ዱቄት ጉዳይ ምን እና ምን ናቸው?

ስንዴ በአዝመራ፣ በማከማቸት ወዘተ የሚባክን መኖሩ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ስንዴው ከዱቄት ፋብሪካ ደጃፍ ደርሶ ዱቄት ሆኖ ሲወጣ የደረሰበት “አደጋ እና ብክነት” ስንት ነው? ሙሉ ስንዴው (እህሉ) በተለያየ መጠን ይገሸለጣል፣ ብዙ አካሉ ይነሳለታል፤ ፍሩሽካ እና ፍሩሽኬሎ ተብሎ ከወጣለት በኋላ ፍርኖ ዱቄት ተብሎ ይወጣል፡፡ ይህ ፍርኖ ዱቄት ከገባው ስንዴ መጠኑ ባክኖለታል፤ የአሰር፣ እና የብዙ ማዕድናት ይዘቱ ጠፍቷል፡፡ ለጤና ያለው ጥቅም ቀንሷል፡፡ በዚህ ዓይነት ፋብሪካው ከተመረተው ዋናው ስንዴ ላይ ትልቅ ብክነት እና ጥፋት አድርሶበታል፡፡ ይህ የተቀነሰለት እስከ 25 በመቶ ይሆናል፡፡

የተቀነሰለት የስንዴ ክፍል የት ገባ? ቢባል ለእንስሳት መኖ ተወሰደ ነው መልሱ፡፡ በእውነቱ ግን ለእንስሳት መኖ ስንዴ ተመራጭ አይሆንም፡፡ የሚሻለው ሳር፣ ለመኖ ተብሎ የሚለሙ ተክሎች፣ የጤፍ ጭድ፣ የእህል ገለባ እና ወዘተ ነው፡፡ እንጂ በአገሪቱ ሰው እየተራበ ስንዴ ላይ እንዲህ ያለ ብክነት ማድረግ እና ለእንስሳት መኖ ማቅረብ ትክክለኛ ሥራ አይደለም፡፡

ስለዚህ፣ ለእኛ አገር ተስማሚው የፋብሪካ ዓይነት ሙሉ ስንዴውን አበጥሮ፣ አጥቦ፣ ፈጭቶ ሙሉ ዱቄት ሊያቀርብ የሚችለው እንጂ ስንዴን የሚገሸልጠው እና ለእንስሳት መኖ የሚያዘጋጀው መሆን የለበትም፡፡

ይህ እውነት ሥራ ላይ ቢውል እና ሙሉ ስንዴው  ሙሉ ዱቄት ሆኖ ለሰው ምግብ ከሄደ ከፍተኛ እጥረት የሚከሰተው በእንስሳት መኖ ላይ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የግብርና ሚ/ር ቶሎ ብሎ የእንስሳት መኖ ልማት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ አለበት፡፡

2ኛ. የስንዴ ዱቄት እና ከጤና ጋር ተያያዥ ጉዳዮች

የስንዴ ዱቄት ወደ ሌላ የምግብ ምርት ሲቀየር የተለያየ ዳቦ፣ ፓስታ፣ መኮረኒ፣ ብስኩት፣ ለኩኪስ፣ ኬክ፣ ፒሳ፣ ገንፎ፣ ወዘተ ይሆናል፡፡

የስንዴ ውጤት ከጤና ጋር በተያያዘ  ብዙ ጥያቄዎች አሉበት፡፡ ለምሳሌ

 • በስንዴ ውስጥ የሚገኘው ግሉተን የተባለ ንጥረ ነገር የማይስማማቸው ብዙዎች አሉ፤
 • የጨጓራ ህመም ያለባቸው፣
 • የስኳር በሽታ ታካሚዎች፣
 • የደም ግፊት ታካሚዎች
 • የነቀርሳ (ካንሰር) በሽታ ታካሚዎች፣
 • የልብ ታካሚዎች እና ሌሎችም የስንዴ ምግብ እንዳይበሉ፣ ወይም እንዳያበዙ ይመከራሉ፡፡ ነገር ግን በጥሩ ሁኔታ ከሌላ እህል የተዘጋጀ ዳቦ መብላት አለባቸው፡፡

ስለዚህ፣ ለሁሉም ሰው በጅምላ አንድ ዓይነት ዱቄት ከሚቀርብ በብዙ አማራጭ መቅረብ ይኖርበታል፡፡

ስለዚህ የዳቦ፣ ፓስታ፣ መኮረኒ፣ ብስኩት፣ ኬክ፣ ፒሳ፣ ወዘተ ዱቄት በብዙ አማራጭ እና የተለያየ ሰብል ከስንዴ ጋር ተመጣጥኖ ሲቀርብ ስንዴ ላይ ያለውን ከፍተኛ ጫና ይቀንሳል፡፡  ከሌሎች ሰብሎች በአማራጭ እና ስንዴን ከሌሎች ሰብሎች ጋር አመጣጥኖ ማቅረብ ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡

3ኛ. የዱቄት ምጥኑን በሌሎች ምርቶች ለማሻሻል የአማራጭ ሐሳብ

በፋብሪካ የሚቀናበረው ዱቄት እንደ አግባብነቱ ዱቄቱን በብዙ አማራጭ በእውቀት አመጣጥኖ አዘጋጅቶ ለተጠቃሚው ማቅረብ ይቻላል፤   ለምሳሌ

 • ከዳቦ ስንዴ ሙሉ ስንዴ ዱቄት
 • ከዱረም ስንዴ ሙሉ ስንዴ ዱቄት (ለፓስታ እና ለመኮረኒ)
 • ሙሉ ስንዴ እና ኦትስ (ለብስኩት፣ ለኩኪስ፣ ለኬክ፣ ለፒሳ ተመራጭ ነው)
 • ሙሉ ስንዴ እና ገብስ፣
 • ሙሉ ስንዴ እና በቆሎ (ለልጆች ጥሩ ዳቦ ለመጋገር ይሆናል)
 • ሙሉ ስንዴ እና ማሽላ
 • ሙሉ ስንዴ እና ካዛቫ
 • ሙሉ ስንዴ እና ሬይ፣ ወይም ጆሎንጌ፡፡ (በዚሁ ድረ-ገጽ ላይ አንብቡ)
 • ሙሉ ስንዴ እና ትሪቲካሌ
 • ሙሉ ስንዴ እና ቡላ ዱቄት እና ሌሎችም፡፡

ግሉቲን የሌለው ወይም ግሉቲኑ አነስተኛ ዱቄት  (ለዳቦ፣ ለኬክ፣ ለኩኪስ፣ ለብስኩት፣ ለፒሳ  ወዘተ)

 • የገብስ ዱቄት፣
 • የሬይ ዱቄት
 • የኦትስ፣ ዱቄት
 • የኦትስ እና ኪኑዋ ዱቄት
 • የጤፍ እና ኦትስ ዱቄት
 • የትሪቲካሌ ዱቄት እና ሌሎችም፡፡

በዚህ ዓይነት ሰው እንደጤናው ኹኔታ፣ እንደ እድሜው፣ እንደ አቅሙ መርጦ ለመግዛት ይችላል፡፡ ዳቦ ቤቶችም በእነዚህ ዱቄት የተዘጋጀውን ዳቦ በብዙ አማራጭ ሊያዘጋጁ ይችላሉ፡፡

4ኛ. ለሁሉም የአዝመራ ምርቶች እኩል ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል

ለምርምር ድጋፍ፣ ለስርፀት፣ ለመስኖ ልማት እና ለመሳሰሉት የሚደረገው ርብርብ እና የበጀት ድጋፍ በሙሉ ለሁሉም አዝመራ በእኩል ደረጃ መደረግ አለበት እንጂ፣ እንደ እስከ ዛሬው ሌሎች ሰብሎችን በማሳነስ ለስንዴ ብቻ የሚደረገው የርብርብ ሥራ የምግብ ዋስትናን እንዳላመጣ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ እስከ ዛሬ በስንዴ ላይ የዋለው የአገሪቱ የምርምር እና የበጀት አቅም በጤፍ፣ በዳጉሳ፣ በትሪቲካሌ፣ በኦትስ እና እንደ ካዛቫ ባሉ የሥራ-ሥር ምርቶች፣ ላይ ውሎ ቢሆን እንደዚህ መከራ ባልበላን ነበር፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት ውስጥ ለምሳሌ ለማሳየት ያህል፡-

  4.1 ካዛቫ 

ካዛቫ የደረሰ የሥሩ ምርት

የሥራ-ሥር ተክል ነው፡፡ በምዕራብ አፋሪካ አገራት ትልቅ ምርት ነው፡፡ ተክሉን በሞቃት ወይናደጋ እና በቆላ ማልማት ይችላል፡፡ ይህ ተክል እድገቱ ዓመቱን ሙሉ ሲሆን፣ ምርቱ ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ተክል ላይ የልማት እና የምግብ ማቀናበር ቴክኖሎጂ መስፋፋት አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ቢለማ የስንዴን ዱቄት እጅግ ይረዳል፡፡ ከታች ያለው ምስል ካዛቫ እና ፍርኖ ዱቄት በእኩል መጠን ተደርጎ የተጋገረ ድፎ ዳቦ ነው፡፡

የፍርኖ ዱቄት እና ካዛቫ ምጥን ዳቦ

4.2 የእንሰት ተክል ያልተዘመረለት ኢትዮጵያዊ ጸጋ ነው፡፡ የምርቱ ውጤት የሆነው ቡላ ከፍርኖ ዱቄት ጋር ጥሩ ዳቦ ለመጋገር ያስችላል፡፡ በጉራጌ ማኅበረሰብ እንሰትንና የስንዴ ዱቄትን አቀላቅለው የሚጋግሩት ዳቡ ‹‹ቁሙስ›› እንዴት እንደሚጣፍጥ የቀመሰ ያውቀዋል፡፡ (በዚሁ ድረ ገጽ ላይ እንሰት ‹‹ጉና ጉና›› ክፍል አንድ እና ሁለት ላይ ሰፊ ገለፃ ቀርቧል-ይመልከቱ፡፡)

የፍርኖ ዱቄት እና የቡላ ምጥን ዳቦ

4.3 ሬይ (ጆሎንጌ)፣ ኦትስ ወይም ትሪቲካሌ በጣም ደጋ በሆኑ አካባቢዎች ሊበቅሉ ይችላሉ፡፡ ለስንዴ ወይም ለገብስ የማይሆን ለምነቱ የደከመ መሬት ላይ ያለ ኬሚካል ማዳበሪያ ተዘርተው ጥሩ ምርት ይሰጣሉ፡፡ ውርጭን፣ በሽታን መቋቋም ይችላሉ፡፡ ሬይ በምስራቅ አውሮፓ ምርቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ተወዳጅ እና በዋጋም ከፍ ያለ ዳቦ ይጋግሩታል፡፡ በዚሁ ድረ ገጽ ላይ የጆሎንጌ ጤና ዳቦ የሚለውን አንብቡ፡፡

የትሪቲካሌ ዘለላ

ሬይ፣ ትሪቲካሌ፣ ኦትስ፣ በተለይ ስንዴ በሚዘራበት ምድር ለመሬት ማከር (ለማፈራረቅ) በእጅጉ ጠቃሚ ናቸው፡፡ ያለ በቂ ምክንያት በግብርና ሚ/ር በኩል ትኩረት ተነፍገዋል፡፡ እነዚህ እህሎች መሬትን የሚያክሩት ያለ ኬሚካል ማዳበሪያ ተዘርተው ነው፡፡ ስንዴ በሚዘራበት መሬት ቢዘሩ አንድም፣ መሬት ቢያክሩ፣ ሁለትም ለጤና ዳቦ ማዋል ከቻሉ ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡

5ኛ. ስንዴን እና ማዳበሪያን በመስመር መዝራት

በመሥመር መዝራት ጥቅሙ ምንድንነው ቢባል?

የሚዘራው የስንዴው መጠን እና የማዳበሪያው መጠን ይቀንሳል፤ ማዳበሪያ ከዘሩ ጋር በአንድ ቦታ ይዘራል እንጂ፣ የትም ተበትኖ አረም እንዲበዛ አያደርግም፡፡ በመስመር ሲዘራ ምርቱ በጣም የተሻለ ይሆናል፡፡

በእጅ በብተና የሚዘራው የስንዴ መሬት በአብዛኛው እስከ 15ዐ ኪሎ/በአንድ ሄክታር ነው፡፡ ማዳበሪያውም ከ15ዐ እስከ  2ዐዐ ኪሎ በሄክታር ይደርሳል፡፡  በጥሩ መዝሪያ በመስመር ቢዘራ በሄክታር 5ዐ ኪሎ ይበቃል፡፡ በአገሪቱ 2 ሚሊዮን ሄክታር ያህል የስንዴ ማሳ አለን ብንል፤ በሄክታር አንድ ኩንታል ዘር ላይ ቁጠባ ቢደረግ፤ ከጠቅላላው 2 ሚሊዮን ኩንታል ትርፍ ተገኘ ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት በዚህ ዓመት ከዱባይ የተገዛውን ያህል ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ 1.56 ቢሊዮን ብር ማለት ነው፡፡ (ማጣቀሻ አንድ ከታች ባለው ሊንክ ስታነቡ ታገኙታላችሁ፡፡)

ሁሉም የእርሻ ባለሙያዎች ስንዴ እና ማዳበሪያን በመስመር መዝራት የስንዴን ምርት እንደሚያሻሻል ያውቃሉ፡፡ ችግሩ የመዝሪያው ማሽን በስፋት የለም፡፡ አብዛኛው ገበሬ በእጅ በብተና ይዘራል፡፡ ጥቂቶች የውሃ ፕላስቲክ ውስጥ ስንዴን እና ማዳበሪያን ጨምረው አጎንብሰው ለመዝራት ብዙ ሙከራ አድርገው ነበር፡፡ በዚህ ዘዴ በመስመር መዝራት ፈጽሞ ከባድ፣ አሠልቺ የማያልቅ ሥራ ነው፡፡

ሆኖም በአንዳንድ ጽሑፍ ላይ አርሲ ውስጥ ስንዴን በመስመር የሚዘራ ማሽን ተጠቅመናል፣ ምርታችን ጨምሯል የሚሉ አሉ፡፡ ይህንን የተባለውን የመዝሪያ ማሽን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ (ማጣቀሻ ሶስት ላይ አንብቡ፡፡)

ከዚህም ሌላ በጣም በአነስተኛ ማሳ ላይ አመቺ የሆኑትን በመስመር መዝሪያ ማሽን በአገር ውስጥ የተሠሩም ሆነ ከውጪ አገር የሚገዙትን ማቅረብ ግድ ይላል፡፡

ማጠቃለያ

ጥሩ እና በቂ ዳቦ ለማግኘት የሁሉም ጥረት ወሳኝ ነው፡፡

ሀ/ የብዙዎች ከፍተኛ ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡

 • የእርሻ ባለሙያዎች፣
 • የእርሻ ባለሐብቶች፣
 • የምግብ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂስቶች፣
 • የምግብ ዱቄት ማቀነባበር ባለሙያዎች፣
 • የስነ ምግብ ተመራማሪዎች፣
 • የባልትና ውጤት አቅራቢዎች፣
 • የምግብ አብሳዮች (ዳቦ ጋጋሪዎች፣ ሼፎች) እና የሌሎችም ጥረት ያስፈልጋል፡፡

ለ. የስንዴን ምርት በስፋት ማረስ ብቻውን በቂ የምግብ አቅርቦት አያስገኝም፡፡ የዱቄት ፋብሪካን በማሻሻል ሙሉ ስንዴ  ወደ ሙሉ ዱቄት በመቀየር እንጂ ስንዴን ወደ እንስሳት መኖ አለመቀየር ተገቢ ይሆናል፡፡

ሐ. የግብርና ሚ/ር ስንዴን በመስመር መዝራት ላይ በአንክሮ መሥራት አለበት፡፡

መ. ከስንዴ ጋር ተመጥነው ለዳቦ የሚውሉት ምርቶች ላይ በትኩረት መስራት፤ በቆላ ምድር ካዛቫ፣ ጤፍ፣ ዳጉሳ፣ ኪኑዋ ወዘተ መዝራት፤ በጣም ደጋ ምድር ለሆኑት ጆሎንጌ (ሬይ)፣ ኦትስ፣ ትሪቲካሌ፣ ለመዝራት ሰፊ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡

የተመረተውን ስንዴ ባለማባከን፣ ስንዴን ከሌሎች ምርቶች ጋር በማመጣጠን፣ ለሁሉም አዝመራ በቂ ድጋፍ በማድረግ፣ ስንዴን በመስመር በመዝራት ስንዴን በመቆጠብ፣ የስንዴን ምርት በማሻሻል የኢትዮጵያን የዳቦ ችግር ለመፍታት የበኩላችንን ጥረት እናድርግ፡፡

ማጣቀሻ

አንድ፡- https://www.ethiopianreporter.com/Suppliers fear wheat contamination at port storage
ሁለት፡- https://www.ethiopianreporter.com/index.php/article/16700
ሦስት፡- https://www.press.et/Ama/?p=13347

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com