በአምቦ ወጣቶች “ዳውን ዳውን” ማለት ጀመሩ

Views: 195

በኦሮሚያ ክልል እና አጎራባች አካባቢዎች የተፈጠረውን ኹከት፣ ግጭት እና ሕገ-ወጥነት ለመከላከልና ችግሩ ዳግም እንዳይከሰት በዘላቂነት ለመፍታት፣ ነዋሪዎችን ለማነጋገር ወደ አምቦ ከተማ ያመሩት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ተቃውሞ ሊያጋጥማቸው ችሏል፡፡

የሀረር ሕዝባዊ ውይይታቸውን አጠናቀው በሔሊኮፕተር ወደ አምቦ ከተማ ያመሩት ጠ/ሚ ዐቢይ፣ ሳይፈቀድላቸው ወደ ውይይት አዳራሽ እንገባለን ያሉ ወጣቶች የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል ተብሏል፡፡

ይሁን እንጂ፣ በአሁኑ ጊዜ ተቃውሞው በሠላም ተጠናቅቆ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መጀመሩንና መንገዶች ክፍት መሆናቸውን የአካባቢው ምንጮች ለኢትዮ-ኦንላይ ገልጸዋል፡፡

ጠ/ሚ ዐቢይ፣ ሕዝባዊ ውይይቱ በሚካሄድበት አበበች መታፈሪያ ሆቴል አዳራሽ ከገቡ በኋላ፣ ከውጪ ወደ ሆቴሉና ወደ አዳራሹ እንገባለን ያሉ ወጣቶች ረብሻ የፈጠሩ ሲሆን፣ ጠ/ሚ ዐቢይ አዳራሹ የቻለውን ያህል ሰዎች መግባት እንዲችል ለሚመለከታቸውን አካላት ትዕዛዝ በማስተላለፋቸውና ያልተጋበዙ የተወሰኑ ወጣቶች መግባት ችለዋል በማለት በሥፍራው የነበሩ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በሕዝባዊ ውይይቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ፣ መድረኩን በመምራት ከሕዝብ ጋር የተወያዩ ሲሆን፣ የሕዝብ ጥያቄዎችን ተቀብለዋል፡፡

ከምዕራብ ሸዋና ከአካባቢው የተመረጡ ነዋሪዎች ጋር በአበበች ውይይት ሲካሄድ፤ ከሆቴሉ ቅጥር ግቢ ውጪ፣ እንዲሁም በከተማዋ ጎዳና ላይ በርካታ የከተማዋና የአካባቢው ነዋሪዎች የተቃውሞ ድምጽ ሲያሰሙ ተስተውሏል።

የተቃውሞ ኹኔታው የተፈጠረው ጠዋት ጠ/ሚ ዐቢይ እንደሚመጡ ሲታወቅ በርካታ ወጣቶች ወደ ሆቴሉ ቅጥር ግቢ በመግባት በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ ሲሞክሩ ነው፡፡

በከተማዋ ዋና ጎዳና እና በሆቴሉ ዙሪያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመከላከያና የኦሮሚያ ፓሊስ አባላት ሰፍረው የነበረ ሲሆን፤ በመንግሥት በኩል ኹኔታውን ለማረጋጋት ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ ሠሞኑን ተከስቶ በነበረው ተቃውሞ በአምቦ ከተማ አንድ የ80 ዓመት አዛውንትን ጨምሮ ስድስት ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ትናንት ከሐረር ከተማ ነዋሪዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን፤ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞችም ሕዝባዊ ውይይቶች እየተካሄዱ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአምቦ በተዘጋጀው የሰላም ኮንፍረንስ ላይ ለመሳተፍ ወደ ከተማይቱ የገቡት ከመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ እና ከኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ጋር በመሆን ነበር። አምቦ ከተማ ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው ኮንፍረንስ ላይ ከምዕራብ ሸዋ፣ ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ቡራዩ፣ ሆለታ እና አምቦ ከተሞች የተውጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

ውይይቱ እየተካሄደ ባለበት ወቅት በአምቦ ዋና አውራ ጎዳና ላይ የተሰባሰቡ ወጣቶች ተቃውሟቸውን በግልጽ ሲያሰሙ ተደምጠዋል፤ የጸጥታ አካላትም ተቃዋሚ ወጣቶችን በትዕግሥት አስተናግደዋቸዋል።

“ቄሮዎች በስብሰባው ላይ መሳተፍ ነበረባቸው” የሚል ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ የነበሩት ወጣቶች “የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ ሲያቀርብ የቆየው ‹‹ቄሮ›› እንጂ አሁን በስብሰባ ላይ የተሳተፈው አካል አይደለም” ማለታቸውን በሥፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

ወጣቶቹ “ዐቢይ እኛን ለማስተዳደር አይችልም፤ አሁንም ሊያታልለን ነው የመጣው” ሲሉ መደመጣቸውንም እማኞቹ ለዶይቼ ቬለ ተናግረው፣ ወጣቶቹ ሲያሰሟቸው ከነበሩት መፈክሮች መካከል “ዳውን ዳውን ዐቢይ፣ ዳውን ዳውን ቲም ለማ” የሚል እንደሚገኝበትም አስረድተዋል። በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ እና ቀይ መለዮ ያደረጉ ወታደሮች በአምቦ አውራ ጎዳና ላይ ጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥር ሲያደርጉ ታይተዋል።

አምቦ ባለፈው ሳምንት በመላው ኦሮሚያ ከተደረገ ሰልፍ በኋላ የ67 ሰዎች ሕይወት የቀጠፉ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለጉዳት የዳረጉ ግጭቶች ካስተናገዱ ከተሞች አንዷ ነች።

 

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com