ኢትዮጵያና ግብፅ በአሜሪካ የሚገናኙት ለውይይት እንጂ ለድርድር አይደለም ተባለ

Views: 166

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በሚመለከት፣ ግብፅ አሜሪካ ታደራድረን በሚል ያቀረበችውን ሃሳብ ኢትዮጵያ አልቀበልም ማለቷ የሚታወስ ነው።

ከቀናት በፊት በሩሲያ ሶቺ ከተማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድና የግብፁ ፕሬዘዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ መገናኘታቸውን ተከትሎ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በህዳሴው ግድብ ግንባታ ጉዳይ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ሦስተኛ ወገን ቢገባ ምንም ችግር እንደሌለው መግለጻቸው ይታወቃል፡፡

ዛሬም የግብፅን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመጥቀስ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያና ግብፅ በመጭው ኅዳር ወር ማብቂያ ላይ ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ድርድር አዘል ውይይት እንደሚያደርጉ ዘግበዋል፡፡

ይሁን እንጂ፣ ቢቢሲ ምንጮቼ ነግረውኛው እልዳለው ከሆነም፤ አሜሪካ-ም፣ ሩሲያ-ም የማደራደር ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ለኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የአሜሪካ የንግድ ሚኒስቴር ባቀረበላቸው ግብዣ መሠረት፣ የሦስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ኅዳር ወር ላይ አሜሪካ  ለመገናኘት መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን፣ የሚገናኙት ለድርድር ሳይሆን፣ ለውይይት ብቻ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያና የግብፅ መሪዎች የቴክኒካል ስብሰባው እንዲቀጥል መስማማተቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አቋም አሁንም “የድርድር ነገር፣ ገና ነው” የሚል እንደሆነ ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል፡፡

“ሁለቱ መሪዎች የቴክኒክ ‹ቲም› ሥራውን ይቀጥል፤ ልዩነት ካለ እኛ እየተገናኘን እንፈታለን ነው ያሉት” ሲሉም አክለዋል።

ምንጮቹ እንደሚሉት ከሆነም፣ ወደ ድርድር ለመሄድ፤ መጀመሪያ ለአገራቱ አደራዳሪ ያስፈልገናል ወይ? ድርድሩ በምን ጉዳይ ላይ ነው የሚያተኩረው? በሚሉ ነገሮች ላይ መስማማት አለባቸው ብለዋል።

ቀጥሎም የአደራዳሪው ኃላፊነት ምንድን ነው? የሚለውን በጋራ ወስነው አደራዳሪውን በጋራ መምረጥ ይኖርባቸዋል።

እነዚህ ቅድመ ኹኔታዎች ሳይሟሉ ወደ ድርድር ሊኬድ አይቻልም፤ ወደ ድርድር መሄድ ራሱ ቀላል እንዳልሆነና የራሱ አካሄድ እንዳለውም አስረድተዋል።

በተጨማሪም፣ ከዲፕሎማሲ አንፃር አሜሪካን ያቀረበችውን ላወያያችሁ የሚል ጥያቄን አለመቀበል በራሱ ጫና ስለ አለው፤ ኢትዮጵያ ከዚህ የዲፕሎማሲ መርህ አንፃር መዝና ነገሮችን እንደምትፈትሽ አመልክተዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com