መንግሥት ችግሮችን የሚያባብስ እንጂ የሚቀርፍ እርምጃ እንዳልወሰደ መኢአድ ገለጸ

Views: 183

የጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት፣ ችግሮችን የሚያባብስ እንጂ የሚቀርፍ እርምጃ አልወሰደም ሲል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፓርቲ አስታወቀ፡፡

መኢአድ፣ በኦሮሚያ ክልል ከሰሞኑ የተከሰተውን ኹከትና ግጭት ያስከተለውን ሞትና የንብረት ውድመት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ መንግሥት የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ተቀዳሚ ተግባሩ መሆን አለበት በማለት በተደጋጋሚ ማሳሰቡን ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 17 ቀን 2012 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አሳውቋል፡፡

ይሁን እንጅ፣ በመንግትት በኩል «ችግሮችን የሚያባብስ እንጂ ችግሩን ለመቅረፍ የተወሰደ እርምጃ የለም» ሲል ወቅሷል።
ድርጅቱ በመግለጫው «ከዚህ በፊት በተሰሩ ጥፋቶች በመንግሥት በኩል አጥፊዎች ተለይተው በፍትሕ አደባባይ ቆመው ሕጋዊ ቅጣት ባለመወሰዱ ሌሎች አዲስ አጥፊዎች እንዲፈጠሩ» ምክንያት ሆኗል ሲልም መንግሥትን ወቅሷል።

ኢትዮጵያውያን በተወለዱበት፣ ባደጉበት፣ ሀብት ባፈሩበት፣ ወልደው በከበዱበት በራሳቸው ሀገር በጠራራ ፀሐይ በአደባባይ ሲገደሉ መንግስት ሕግ አለማስከበሩና የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት አለማስጠበቁንም መኢአድ ተችቷል፡፡

የፌደራልና የክልል የፀጥታ ኃይሎች ያለ አድሎ የዜጎችን ህይወት ከማንኛውም አደጋ እንዲታደጉ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶችም ከዚህ የባሰ የእርስ በእርስ ግጭት እንዳይፈጠር የማሸማገል ስራ በመስራት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስቧል፡፡

ወጣቶችም በሌሎች የጥላቻና ፀብ ቀስቃሽ ንግግር ተነሳስተው በወገናቸው ላይ በክፋት ከመነሳት እንዲቆጠቡና የአካባቢያችውን ሰላም እንዲጠብቁ መኢአድ ጥሪ  አቅርቧል።

በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የሚዲያ ተቋማት ህዝብን ከህዝብ ከሚያጋጭ ክፉ ተግባር ይልቅ ህዝብን የሚያቀራርብ እና የሚያዋድድ ስራ እንዲሰሩ
እና  ሰሞኑን በኦሮሚያ የተለያዩ ቦታዎች በተከሰተዉ ግጭት «በግፍ ተገደሉ›› ላላቸዉ ዜጎችም የተሰማዉን ሀዘን ገልጿል።

ዘገባው የዶቸቬሌ ነው

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com