“ከሰንጋ ተራ እስከ አምስተርዳም”

Views: 430

በአገራችን ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና ከነበራቸው ክስተቶች አንዱ እና ዋነኛው የ 1960ዎቹ “የያትውልድ” ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ነበር:፡፡ የዚህ እንቅስቃሴ አስኳል ደግሞ የያን ጊዜው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ፣ የዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው፡፡ ከዚህ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ከተወለዱ አንጋፋ ድርጅቶች ደግሞ አንዱ እና ግንባር ቀደሙ ኢ.ሕ.አ.ፓ እንደሆነ ይታወቃል:: ከዚህ ድርጅት መሥራች አባላት አንዱ፣ ዛሬም ድረስ በሕይወት የሚገኙት አቶ መላኩ ተገኝ የጻፉት ግለ- ታሪክ መጽሐፋቸው የዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን ነው፡፡

እንደተለመደው መጽሐፉን በወፍ በረር ቃኝቶ- ማስቃኘት እና ጥቂት በተነሱ ጉዳዮች ላይ አስተያየት መስጠት እንጂ ሒሳዊ ትንታኔ መስጠት አይደለም የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ፡፡ ደራሲው፣ ከልጅነት እስከ ዕውቀት የሄዱበትን የሕይወት ጉዞ፣ ከቤተሰብ እስከ ፖለቲካ ድርጅት አባልነት፣ ስደት፣ ትምህርት፣ የፍቅር ግንኙነት፣ የትግል ሜዳ ገጠመኝ በአጠቃላይ ከሞላ ጎደል አንድ የግለ ታሪክ መጽሐፍ ሊያካትተው የሚገባውን ዓላባውያን አካተዋል፤ በዚህ መጽሐፋቸው ፡፡ ይህንንም እንደ መጽሐፉ ሥኬት ልንቆጥረው እንችላለን፡፡

መጽሐፉ በአራት ምዕራፎች የተከፈለ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ ስለ ልጅነት ሕይወት፣ ስለ ቤተሰብ እና ደራሲው ተወልዶ ስላደገበት ሠፈር፤ እንዲሁም ስለ አዲስ አበባ ወቅታዊ ሁኔታ ምሥል ከሣች በሆነ መልኩ የተተረከበት ነው፡፡ ምዕራፍ ሁለት ደግሞ ስለ ጉርምስና፣ የፖለቲካ ንቃት (ተራማጅነት) በተለይ የ1953ቱን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ እና ስለፍቅር የተወሳበት ክፍል ነው፡፡ ቀጣዩ ምዕራፍ ሦስት ደግሞ ስለ መላኩ የፖለቲካ ሰውነት፣ ስደት፣ የፖለቲካ ሕይወት ጉዞ ጅማሮ በአጠቃላይ ሰውየውን በኢትዮጵያ ተማሪዎች የፖለቲካ ተሳትፎ፤ እንዲሁም በፓርቲው ውስጥ ያለውን ታሪካዊ ሚና የምናይበት ወሳኙ ክፍል ነው፡፡ የመጨረሻው ክፍል ምዕራፍ አራት በበኩሉ ስለ ሱዳን ሕይወት እና ስለ ኢ.ሕ.አ.ሠ (የኢህአፓ ወታደራዊ ክንፍ) ሕይወቱ ይተርካል- ደራሲው፡፡

የ’ዛ ዘመን ልጅነት

     የአንጋፋው ስፖርት ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ “የፒያሣ ልጅ” መጽሐፍ፣ የአዲስ አበባን ነባር መሥራች ሠፈሮች እና የልጅነት አኗኗርን እንዲሁም የቀድሞውን የከተማዋን ገጽታ በሚገርም ሁኔታ ያስቀመጡበትን መንገድ በቅጡ ያነበበ እና የወደደ፣ የመላኩ ተገኝን የአዲስ አበባ ልጅነት በማንበብ በአንድ ወቅት አዲስ አበባን ከነልጅነት ትዝታዋ ብሎም የከተማዋን መንፈስ ያውቅ ዘንድ ተጨማሪ ዕድል ይፈጥርለታል ባይ ነኝ፡፡

በመላኩ የልጅነት ጉዞ አዲስ አበባ ከነ ሠዎቿ በአግባቡ ትታወሳለች፡፡ ጉርብትናና የልጅነት ጨዋታ፣ የከተማው ነዋሪ ስብጥር፣ የጋራ ድህነት እና በከተማዋ አዳዲስ ነገሮች መተዋወቅ፣ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች እና መሠል ታሪኮች በመጽሐፉ ሁለት ምዕራፎች በተለያዩ መንገዶች ቀርበዋል፡፡ “ዘር የማይቆጠርበት ዘመን” በሚል ክፍል ሦስት ላይ መላኩ የልጅነት ጎረቤቶቹን ያስታውሰናል … “ከይስሐቅ ቤተሰብ ጋር ሁለት ዓመት ያሕል አብረን በኖርንበት ግዜ ብዙ ነገሮችን ተማርን:: ከኤርትራ ክርስቲያኑ ክፍል ባህላቸውን ተማርን፡፡ ከሁሉም ትዝ የሚለኝ ሻይ ሲፈላልን አብሮ የሚቀርብልን ቂጣና አልፎ አልፎም ቅጫ (ጨጨብሳ) ነው፡፡ ሻይማ ነፍሳችን ነበር፡፡ እኔና ወንድሜ ከይስሐቅ ቤተሰቦች የኑሮ ዘይቤ ብዙዎችን እየወደድን ስንመጣ እነ ይስሐቅም ከኛ ቤተሰቦች የኑሮ ዘይቤ የሚወዷቸው ነበሩ፡፡ ማታ ማታ ሁለቱም ቤተሰቦች አብረው ይበላሉ፤ ከራት በኋላ ጨዋታ ይደራል፡፡ ጨዋታዎቹ ብዙ ግዜ በልጆቹ ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡” እንደዚህ ዓይነት ዘመኑን ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ማህበራዊ መስተጋብሮቻችን እምን ድረስ እንደነበሩ የሚያሳዩ የግል ገጠመኞቹን ደራሲው ያለስስት አካፍሎናል፡፡ ትላንትን በሚያስናፍቁ ውብ የልጅነት ትዝታዎች ተዋቅረዋል- ሁለቱ ምዕራፎች፡፡

አውሮፓ እና የተማሪ ማሕበር

የዚህ መጽሐፍ ደራሲ መላኩ ተገኝ፣ ቀድመው ወደ አውሮፓ ለትምህርት እና ለፖለቲካ ትግል ከወጡ የያኔው ወጣት ተማሪዎች አንዱ እንደመሆናቸው፣ በአውሮፓ በነበረው የተማሪዎች ማሕበር ንቁ ተሳታፊ ስለነበሩና፣ በኋላም የኢሕአፓን የውጭ ግንኙነት በዋነኛነት ሲሰሩ ከነበሩ ግንባር ቀደም አመራር እንደመሆናቸው ስለ አውሮፓ የተማሪዎች ሕብረት የሚናገሩት ነገር የዚህ መጽሐፍ ትልቁ ዋጋው ነው፡፡ የዚያ ዘመን ቀዳማይ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ኢ.ሕ.አ.ፓ እና መ.ኢ.ሶ.ን የተመሠረቱት እዚያው አውሮፓ በመሆኑ ጸሐፊው በወቅቱ የነበሩ የዐይን ዕማኝ እና ተሳታፊ በመሆናቸው የሳቸው ምሥክርነት ታሪካዊ ፋይዳው ቀላል አይደለም፡፡

በእርግጥ፣ በዚህ ረገድ ደራሲው በኔ አስተያየት የሚጠበቅባቸውን ያሕል ስለ ጉዳዩ ፍንትው ያለ ነገር ጽፈዋል ብዬ አላምንም፡፡ በወቅቱ ከነበሩ ወጣት ፖለቲከኞች እንደ ደራሲው ለሽምግልና እና ለረዥም ዕድሜ የታደሉ ጥቂቶች መሆናቸውን ስናስብ፣ በሕይወት ያሉትም አንዱ አንዱን ለመውቀስ እና ለመወንጀል ብቻ መጻፍን ብዙዎቹ መምረጣቸውን ለታዘብን አንባቢያን፣ ደራሲው ጥንቅቅ ያለ ታሪካዊ ዶክመንት በጉዳዩ ላይ ይሰጡናል ብለን ከጠበቅነው አንጻር፤ መጽሐፉ ብዙ ጉድለት አለው ባይ ነኝ፡፡

ይሁንና ካጎደሉት ይልቅ፣ የሰጡን ላይ እንነጋገር ካልን፣ አንዳንድ ነገሮችን መጥቀስ እንችላለን :- ስለመጀመሪያው የኢሕአፓ ስብሰባ ገጽ 170 እና 71 ላይ ይህ ሠፍሯል

     “… ዋናው የስብሰባው አጀንዳ በብርሃነ መስቀል ፖለቲካል ሪፖርት ተጀመረ::

     ከሪፖርቱ ምንም አከራካሪ ጉዳይ አልተነሳም፡፡ በጉባዔው ክርክር ያስነሳው ነጥብ

     ቢኖር፣ በዓለማቀፉ ኮምዩኒስት እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ አደጋዎችን በሚመለከተው

     ላይ ነበር፡፡ ስለ ዓለማቀፉ ኹኔታ መንደርደሪያ ጽሑፍ ያቀረበው ኢያሱ ነበር፡፡

     በጽሑፉ የቻይና ኮምዩኒስት ፓርቲ በ1969 (እ.ኤ.አ) ዘጠነኛ ጉባዔው የወሰደውን

     አዲሱን አቋሙን የሚደግም ኾኖ፣ የሶቭየት ሕብረትን በሶሻል ኢምፔሪያሊስት

የሚፈርጅ ነበር፡፡ … የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲንና የአልቤኒያን ፓርቲ አቋም የሚያንጻባርቀው የኢያሱ አቋም፣ አከራካሪ የሆነበት ዋናው ምክንያት ከዚህ

ግምገማ ተነስቶ የተወሰደው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አከራካሪ በመሆኑ ነበር::

በዚህ አቋም መሠረት “የሶቭየት ሶሻል ኢምፔሪያሊዝም” በቃሉ ሶሻሊስት መስሎ በድርጊቱ ኢምፔሪያሊስት በመሆኑ፣ ይበልጥ አደገኛ በመሆኑ እሱን ለመነጠልና ለመታገል ከምዕራብ ኢምፔሪያሊዝም ጋርም ቢሆን ማበር ያስፈልጋል የሚል ነበር፡፡ ይህ ጨርሶ የሚዋጥ አልበረም፡፡ … ይኼ አቋም የዓለም ሬቮሊሽናዊ ነቅናቄን የሚጎዳ ነው ተባለ፡፡ ስለዚህም፣ በዚያ ጊዜ ለዓለም ኮሙኒስት እንቅስቃሴ ሁለቱ አደጋዎቹ የሶቭየት ሕብረት ከላሽነት እና በቅርጹ ግራ መስሎ በተግባር ቀኝ የሆነው የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ አቋም ነው የሚለው አስተያየት ባብዛኛው ተሳታፊ ድምጽ ጸደቀ፡፡” ይለንና ተስፋዬ ደበሳይ ከአዲስ አበባ ካነጋገራቸው መካከል ዋለልኝ መኮንን፣ ጸጋዬ ገ/መድህን (ደብተራው) እና ጸሎተ ሕዝቅያስ ጠቅሶ አቋማቸው ” … በጉባዔው ላይ በአልጄሪያ ጓዶች እንዲወከሉ፣ በውጭ አገር ካሉ ቡድኖችም በአውሮፓ ያለው የመኢሶን ቡድንና በአሜሪካ ያለው የቀድሞ የኢዙና ቡድን ፓርቲው ውስጥ እንዳይገቡ ጠየቁ፡፡”

የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ገና ከመጀመሪያው ስለነበራቸው የአቋም እና አመለካከት ልዩነት ይህ ዓይነተኛ ምሥክር ነው፡፡ በኋላ አዲስ አበባ ላይ በተለየ በመላው ኢትዮጵያ በአጠቃላይ የደረሰው የትውልድ እልቂት መሠረቱ ምን እንደሆነ ለመመርመር በየጉባዔው የተወሰዱ አቋሞች፣ የተነሱ የክርክር ይዘቶችን እና ግለሰቦቹ የወሰዷቸውን አቋሞች ማጥናት ግድ ይላል፡፡

     እንደዚ ዓይነት ታሪካዊ ፋይዳ ካላቸው ምሥክርነቶች ሌላኛውን ደሞ እንጥቀስ :-

” … የክርክሩ መንስዔ ኃይሌ ፊዳ ለሀገር ቤቱ የተማሪ እንቅስቃሴ በተለይ ስለ ኡዙዋ የተሰጠው ትችታዊ ግምገማ ነበር፡፡ ኃይሌ ያገር ቤቱ እንቅስቃሴ ግራ ቀደምትነትና (Left opportunism) ጀብደኝነት (Adventurism) የተጠናወተው ነበር ካለ በኋላ፣ ለማስረጃ የተጠቀሰው በ “ታገል” (የኡዙዋ ጋዜጣ) የኅዳር 1962 ዓ/ም ዕትም ላይ በርእስ አንቀፁ ለትጥቅ ትግል ጥሪ ማድረጉን፣ እነ ብርሃነ መስቀል ያደረጉትን የአውሮፕላን ጠለፋ ማወደሱን እንዲሁም በ1961 እና 1962 ዓ.ም ተወዳጅ የነበረውን “ፋኖ ተሰማራ” የተሰኘውን የተማሪውን የትግል መዝሙር ነበር፡፡ በተጨማሪም፣ ከ1962 የጥላሁን ግዛው ግድያ ተከትሎ ከተማሪዎች መረሸን በኋላ ከአገር ቤት ወደ አውሮፓና አሜሪካ የሄዱት የእንቅስቃሴ አባላት ይህንኑ ጀብደኝነት አንጸባርቀዋል አለ፡፡” ገጽ 179

እንግዲህ ገና በጠዋቱ በዚህ መልኩ የነበሩ ልዩነቶች እና መቆራቆዞች በሂደት እየተባባሱ መጡ፤ በመኃል ያለው ልዩነትም ሠፋ፡፡ የልዩነት መሠረቶች በመላኩ ዕይታ ምንድናቸው? ገጽ 211 ላይ ይህን ሃሳብ አስፍሯል፤ ደራሲው :-

“… በመሠረቱ ልዩነቱ የተነሳው በ1960 – 61 በኢትዮጵያ የተማሪ እንቅስቀሴ ተሳትፈው በሠላምም በስደትም ወደ ውጭ አገር በተለይም አልጄሪያ፣ ሱዳን፣ አውሮፓና አሜሪካ በወጡት ታጋዮችና በአውሮፓ ማኅበር ለረዥም ግዜ በኖሩት የአውሮፓው ማኅበር መሪዎች መሐል ነው፡፡ እንደሚታወቀው በ1962 ዓ.ም የጥላሁን ግዛው ግድያ ተከትሎ የመጣው ኹኔታ የተማሪው መሪዎች ገምግመው የደረሱበት መደምደሚያ አንደኛ የተማሪው እንቅስቃሴ ወደ ዓብዮታዊ እንቅስቃሴ መሸጋገር እንዳለበት፣ ሁለተኛ በሕዝቡ መሐል ገብቶ እየቀሰቀሱና እያደራጁ ትግሉን የሚመራ ፓርቲ ለማቋቋም የመጀመሪያ እርምጃ የሆነውን በጥናት ክበብ መደራጀት መጀመር ናቸው ::” ደራሲው ገጽ 212 ላይ ይለጥቅና

… “ዋነኛው ልዩነት ኢትዮጵያ ውስጥ በጊዜው የነበረውን ኹኔታ በመገምገም ላይ የተነሣ ነው፡፡ እኛ ዓብዮታዊ ኹኔታ አለ፤ ለዓብዮቱ መነሣት አመቺ ኹኔታ ተፈጥሯል፤ በነባራዊ ጠባዩ (Objective Conditions) በአገሪቱ ለዚህ የተመቻቸ ኹኔታ አለ፣ ስለዚህ ሕዝቡን አደራጅቶና አስተምሮ የሚያታግል ዓብዮታዊ የሆነ ድርጅት ያስፈልጋል አልን፡፡ የመኢሶን መሪዎች በበኩላቸው

“እስከዛሬ በኢትዮጵያ መሬት ላይ የፖለቲካ ፓርቲ ታይቶ አይታወቅም፡፡ እስከዛሬ የህዝቡ አንድ ክፍል ወይም መደብ ወይም የሙያ ማሕበር በአንድ የተቀናበረ የፖለቲካ ድርጅት ሥር ተሠልፎ ሥራ ሲያቆም፣ ማመልከቻ (ፔቲሽን) ሲጽፍ፣ ሠላማዊ ሠልፍ ሲያደርግ፣ ከፖሊሱ ጋር ሲጋጭ አልታየም፤ ስለዚህ፣ ከዚህ ሁሉ የሚፈልቀው መደምደሚያ የህሊናዊ ኹኔታ (Subjective Condition) ወደ ኋላ መቅረት ነው፡፡” አሉ፡፡ ይለናል መላኩ ተገኝ፡፡

ይህ ልዩነት ተባብሶ በየ ጉባዔያቱ መዘላለፍንና መወነጃጀልን አስከትሎ ተማሪዎቹ በሁለት ድርጅቶች ተከፋፍለው በኋላም በዓብዮቱ ዘመን ለቀጠለ ጠላትነት እንደበቁ እንታዘባለን፤ በየገጾቹ የተከተቡትን ጽሑፎች ስናነብ፡፡

ሌላው ደራሲው በድፍረት ያነሳውና ድርጅቱን ለመተቸት ባሳየው ቁርጠኝነት የሚያስመሰግነው ሃሳብ ገጽ 227 ላይ ተጽፎ እናገኛለን፡-

“… የከተማው የትጥቅ ትግል ከመጀመሪያውኑ አልተዋጠልኝም፡፡ ግን የፓርቲውን አቋም ከፓርቲ ውስጥ ኾኖ ማስቀየር እንጂ ከውጭ ኾኖ ፓርቲው ላይ መዝመትን መቃወም ብቻ ሳይሆን፣ እንደምታገለው ግልጽ አደረግሁ፡፡ ጉዳዩ ወደ ክፍፍል እንዳያመራ መጀመሪያ በፓርቲው ኮሚቴ ደረጃ መፍታት ጥሩ እመርታ ይሆናል ብዬ ገምቼ እያሱን እንደምንም አግባባሁና ከአውሮፓ የፓርቲ ኮሚቴ ጋር አብዱል መጂድ ሁሴን፣ ከበደ ታደሠ፣ ፍቅሩ ማሩ፣ ብሩክ ላቀው ፓሪስ ላይ ገነት ግርማ ቤት ተሰበሰብን፡፡ …

ኢያሱ የሰጠው ገለጻ አብላጫው የሌሎች ፓርቲዎችን የከተማ ዐመጽ ተሞክሮ በተለይም የቪየትናም እና ካምፑቺያን እየጠቀሰ በመርህ ደረጃ በከተማ ጥይት መተኮስ የለበትም የሚለው ትክክል አለመሆኑን ማስረዳት ነበር፡፡ ፍቅሩ ትንሽ ሊከራከር ሲሞክር አብዱልመጂድ ጭራሽ ወደኛ ግልብጥ ብሎ በቪየትናም የከተማ ተሞክሮን በማስረዳት “ከገጠር ከተማ” የሚለው ቀኖና መሆኑን አስረዳና ሰው ሁሉ ገረመው፡፡ ከበደ እና ብሩክ ማንንም ሳይናገሩ ቀሩ፡፡ ባጭሩ “ከገጠር ከተማ” የሚለው ቀኖና በቅጡ ተመታና ስብሰባው አለቀ፡፡” ብሎ ምሥክርነቱን ይሠጣል ደራሲው፡፡

     በወቅቱ የተደረጉ ክርክሮችንና ዛሬም ድረስ ለምን እንደተወሰኑ ግራ የሚያጋቡ ክስተቶች ሙሉ በሙሉ ባይሆንም፣ የተወሰኑ ጥቁምታዎችን ይሠጣል መጽሐፉ፡፡ በተለይ በውጭ አገር ስለተደረጉ ስብሰባዎች፡፡ ከነዚህ ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳ ካለቸው ታሪኮች እና ምሥክርነቶች ባሻገር ስለሱዳን ህዝብ ደግነት እና ደራሲው ስለነበራቸው የፍቅር ግንኙነት ያስነበቡን ታሪኮች ልብ ይነካሉ፡፡

ለመጽሐፉም ተነባቢነት ተጨማሪ ውበት ናቸው፡፡ መጽሐፉ ግለ ታሪክ እንደሆነና ከ1953 ዓ.ም በተለምዶ “የታኃሳሥ ግርግር” በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ተወልዶ ስላደገ ልጅ ታሪክ እንዲቆጠር ደራሲው እንደፈለጉት ብቻ ብንቆጥረው ብዙ መሳጭ እና አስገራሚ የሕይወት ጉዞ እና ገጠመኝ የተካተተበት እምብዛም እንከን አልባ መጽሐፍ አድርገን ልንወስደው እንችላለን፡፡

     ደራሲው ግን፣ በአንድ በአገሪቱ ፖለቲካዊ ታሪክ ላይ ቀላል የማይባል አሻራ ያሣረፈ ድርጅት አባልና አመራር እንዲሁም መሥራች እንደመሆናቸውና ይህንንም መጽሐፍ ለማበርከት እንደመዘግየታቸው ብዙ ታሪካዊ ሂሳብ የሚወራረዱባቸውን ዶክመንቶችን (በእጃቸው ያለ ወይም የሰበሰቡት) ቢያጋሩን፣ በወቅቱ ድርጅቱ ስለወሰዳቸው ፖለቲካዊ አቋሞች ትክክለኝነት እና ጥፋት ጥልቅ ትንታኔና ምልከታቸውን ሠነድ እየጠቀሱ የግል ልምዳቸውን እያጣቀሱ ቢያካፍሉን እንዲሁም የትላንትን እና የዛሬን ፖለቲካ ኹኔታ ገምግመው ነገን ቢያመላክቱን እንደ አንድ አንጋፋ ፖለቲከኛ ሲያንሳቸው እንጂ ሲበዛባቸው አይደለም፡፡ ምናልባት በቀጣይ ሌላ መጽሐፍ ጀባ ይሉን ከሆነ፣ ይህ እንደ ማሳሰቢያ ይቆጠር፤ ላሁኑ ግን ምስጋና ብናቀርብ ይገባቸውል እንላለን፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com