ዜና

የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ ከባሕር ዳር ወደ አዲስ አበባ እየተጓዙ ያሉ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችን ጎሃ ፅዮን ላይ አገደ

Views: 469

ባሕር ዳርን ጨምሮ ከተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ተነስተው ወደ አዲስ አበባ እየተጓዙ ያሉ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ጎሃ ፅዮን ከተማ ላይ በኦሮሚያ ልዩ ኃይል መታገታቸውን በቦታው የሚገኙ ተጓዥ ለኢትዮ ኦን ላይን አስታውቀዋል፡፡

የታገቱ አውቶብሶች ከሰማንያ በላይ ናቸው፡፡ ተሸከርካሪዎቹ ወደ መጡበት ለመመለስ የሚያስችላቸው ነዳጅ የላቸውም፡፡

ተሸከርካሪዎቹ የታገቱት የፊታችን እሁድ ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት አስተባባሪነት በአዲስ አበባ በሚካሄደው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የሚሳተፉ ተሳፋሪዎች ይኖራሉ በሚል ጥርጣሬ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት የሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊዎችን ከደሴ እና ከባሕር ዳር ለማስመጣት አስቀድሞ አውቶብሶችን መላኩንም በቦታው የሚገኙ ፖሊሶች እያወሩ መሆኑን ተሳፋሪዎች ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም ሰላማዊ ሰልፉን ለማደናቀፍ ከየአቅጣጫው መንገዶች ሊዘጉ እንደሚችሉ ነው የተገለፀው፡፡

ከተሳፋሪዎች መካከል ለህክምና የሚጓዙ ህሙማን ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚጓዙ ተማሪዎች፣አዛውንቶች፣ሕፃናትና ነፍሰ ጡሮች ይገኙበታል፡፡

የታገቱባት ከተማ ጎሃ ፅዮን ሁሉንም መንገደኞች ሊያስተናግድ የሚችል ሆቴል ወይም ሌላ የእንግዳ ማረፊያ እንደሌላት ተሳፋሪዎች ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ በቅርቡ ከደብረ ብርሃን ወደ አዲስ አበባ መንገደኞችን አሳፍረው ሲሽከረከሩ የነበሩ አውቶብሶች በኦሮሚያ ወጣቶችና በፖሊስ ታግተዋል፡፡

በደብረ ብርሃን ከተማ ሁከት ፈጥረው በዚያው የታሠሩ የአሮሚያ ወጣቶች ካልተፈቱ መንግደኞቹ እንደማይለቀቁ መደራደሪያም አቅርበዋል፡፡ በመሆኑም እስረኞች ተፈተው መንገደኞች ተለቀዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com