ዜና

በሰላማዊ ሰልፉ ድምፃችን የማይሰማ ከሆነ ወደ ሕዝባዊ እንቢተኝነት እንሄዳለን ሲል ባልደራስ ገለጸ

Views: 284

የአዲስ አበባ ባለአደራ ም/ቤት(ባልደራስ) እሁድ ጥቅምት 2 ቀን 2012ዓ.ም  በመስቀል አደባባይ የሚደረገውን ሰላማዊ ሰልፍ በማስመልከት በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የሰልፉ ዓላማዎችም በሕዝብ መስዋዕትነት የመጣው ለውጥ በገዥው ፓርቲ ውስጥና ከገዥው ፓርቲ ውጭ ባሉ ፅንፈኞች መጠለፉን ለመቃወም ነው ብሏል፡፡

ገዥው ፓርቲ አካሄዱን በአፋጣኝ እንዲያስተካክል ለማሳሰብ፣ በሀሳባቸውና በፖለቲካ ልዩነታቸው ብቻ በአስፈፃሚው አካላትና በአሻንጉሊት ፍ/ቤቶች ትዕዛዝ በኦሮሚያ፣ በአማራና በአደዲስ አበባ ታስረው የሚገኙ የሕሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ  ምክርቤቱ አብራርቷል፡፡

አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅዓላማ ሕገ-ወጥ እንደሆነ የሚደነግገው ሕግ በአስቸኳይ እንዲሰረዝ ለመጠዬቅ ፤ መንግስት፣ ፅንፈኛ ኃይሎችና ሁሉም የፖለቲካ አካላት በሀይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ እንዲሁም መንግስት ለሁሉም ሀይማኖቶችና ቤተ-ዕምነቶች አስፈላጊውን ጥበቃ እንደያደርግ በሰልፉ ላይ እንጠይቃለን ብሏል፡፡

መንግስት እየከፋ የመጣውን የዋጋ ንረትና ሥራ አጥነት ለመፍታት በትኩረት እንዲሠራ ለማሳሰብ  እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ላይ “ልዩ መብትና ጥቅም አለን” በሚሉ ቡድኖችና ግለሰቦች እየተካሄደ ያለውን የመብት ጥሰት ለመቃወምና በከተማዋም ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል መብት እንዳላቸው ለማሳወቅ እንደሆነ አስረድቷል፡፡

የባለአደራው ም/ቤት ሰብሳቢ እና  የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ  የአደባባይ ሰላማዊ ሰልፉን ለማድረግ ለአዲስ አበባ መስተዳደር ጥያቄ አቅርበናል በሕጉ መሠረትም መስፈርቱን አሟልተናል ሲል ተናገሯል፡፡

ከሰልፉ በላይ የሚበልጥብን የሕዝቡ ደህንነት ነው ፤ስለሆነም የመንግስት ኃላፊነት ጥበቃ ማድረግ ስለሆነ የከተማ ነዋሪ ያለ ስጋት ለመብቱ እንዲታገል ጥሪም አቅርቧል፡፡

ሰሚ ስላጣን ወደ ሰላማዊ ትግል ሄደናል ያለው እስክንድር ድምፃችን የማይሰማ ከሆነ በሰላማዊ ሰልፉ ብቻ ሳንቆም ወደ ሕዝባዊ እምቢተኝነቱ እንሄዳለን ብሏል፡፡

ታፍነናል መስራት አልቻልንም የእኛ ብቻ ችግር ሳይሆን የሁሉም ችግር ነው በማት  ድምፅ የምናሰማው ስለ አዲስ አበባ ሳይሆን  ስለኢትዮጵያ ነው ሲል አስረድቷል፡፡

ለአዲስ አበባ ብቻ ድምፅ ለማሰማት ዓላማ ያለቸው ሰዎች ለዚህ ብቻ ብለው የሚመጡ   ከሆነ ባይወጡ ይሻላል ሲል ተናግሯል

ይሁን እንጂ ጋዜጣዊ መግለጫው እየተሰጠ በሚገኝበት ቅፅበት ከአዳራሹ ውጭ ማንነታቸው ያልታወቀ በርካታ ወጣቶች መግለጫውን በጩኸት የረበሹ ቢሆንም መግለጫው ሳይቋረጥ ለመጠናቀቅ ችሏል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com