ዜና

በአዲስ አበባ ከመሬት ስር የሚሆን የትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል ሊገነባ ነው

Views: 167

በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የትራፊክ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠርና በከተማዋ ላይ የሚታየውን የጸጥታ፣ የአደጋ እና የወንጀል ድርጊትን ለመቆጣጠር የሚያግዝ የትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል ግንባታ ሊጀመር ነው፡፡

የህንፃው ግንባታ ከመሬት ስር ሆኖ አራት ወለሎች እንደሚኖሩት የተነገረ ሲሆን ከመሬት በላይ ያለው ያለው ቦታ ለአረንጓዴ ልማት እንደሚውል ተገልጿል፡፡

በአራቱ ወለሎች ከትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል በተጨማሪ መረጃ ማደራጃ ክፍሎች፣ የወንጀልና የአደጋ መከላከያ መረጃ ቢሮዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትም እንደሚኖሩት ተነግሯል፡፡

በከተማዋ የሚከናወኑ የትራፊክ እንቅስቃሴዎችን እንዲሁም የትራፊክ ቁጥጥሩን ለማዘመን የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ የሚረዳ ግዙፍ የቴሌቪዥን እስክሪኖች በማዕከሉ ይገጠሙለታል ተብሏል፡፡

በማዕከሉ ውስጥ የትራፊክ መረጃዎችን የመሰብሰብ፣ የትራፊክ መብራቶችን የቆይታ ጊዜ እንደ ትራፊክ ፍሰቱ መጠን የመቀያየርና ልዩ ልዩ የትራፊክ ፍሰት ማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ የማድረግ ስራም ይከናወንበታል፡፡

ይህ ማዕከል አሽከርካሪዎች የመንገዶችን የትራፊክ ሁኔታ ቀድመው እንዲያውቁና አማራጭ መንገዶችን እንዲፈልጉ መረጃ የመስጠት፣ የትራፊክ ህጎችን የሚተላለፉ አሽከርካሪዎችን የመለየት እንዲሁም የትራፊክ ፍሰት፣ የአደጋ እና የደህንነት መረጃዎች ወደሚመለከታቸው ልዩ ልዩ ተቋማት በጊዜው እንዲተላለፉ ማድረግ ያስችላል፡፡

የዚህ ማዕከል ወጪ ሙሉ በሙሉ በከተማዋ አስተዳደር እንደሚሸፈን የከተማዋ የትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል
የፊታችን እሑድ መስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም በሚከናወነው የግንባታ ማስጀመሪያ ስነስርዓት ላይ የከተማዋና የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች እንደሚገኙበት የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com