ዜና

ሀገራዊ-ሻሂ ለጉንፋን

Views: 806

(ጨሞ-ሀገራዊ ሻይ)

 

(ምስል አንድ፡-  ለአገራዊ ሻይ  የሚሆኑ ቅመማት)

መግቢያ፡-

በብዙ ችግሮች የተነሳ፣ በየወቅቱ ጉንፋን ይከሰታል፡፡ ለምን እና እንዴት ተከሰተ በሚል ሃተታ ማብዛት ጊዜ ማባከን ነው፡፡ በየወቅቱ ለሚከሰቱ የጉንፋን በሽታ በቤታችሁ እራሳችሁን የማከሚያ መላው እነሆ በረከት-፡

የበሽታው ጫና ከሰው ሰው ይለያል፤ ሆኖም በአብዛኛው ጉሮሮ ይበላል፤ ይከረክራል፤ ዓይን ያስለቅሳል፤ አፍንጫን እስኪቀላ በፈሳሽ ያዝረበርባል፤ ያስላል፤ በተደጋጋሚ ያስነጥሳል፤ እራስ ያሳምማል፤ ሰውነት ያደክማል፤ ያደነዝዛል፤ ያፈዛል፤ ትክክል እንዳያስቡ ያደርጋል፤ እንቅልፍ ያበዛል፤ ብርድ-ብርድ ይላል፤ ያተኩሳል፤ ያንቀጠቅጣል፤ አክታ- ያበዛል፤ ያስቀባዣራል፤ ወዘተ፡፡

ደግነቱ ይህ ሁሉ የበሽታው ምልክት በአንድ ጊዜ አንድ ሰው ላይ አይከሰቱም፡፡ ጥቂቶቹ ብቻ በአንዴ ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ታማሚው ከጥቂት ቀናት እስከ ሳምንት ወይም እስከ ሁለት ሳምንት ሊታመም ይችል ይሆናል፡፡

በዘመናዊ ሕክምና የሚረዱ ነገሮች አሉ፡፡ በተጨማሪ ግን እነዚህን ሻይ መጠጣት የሚረዳው

 • የጉንፋኑን የበሽታ ጫና ለመቀነስ፤
 • ቶሎ ከጉንፋኑ ለመዳን፤
 • በተለይም በጊዜው ለተከሰው ችግር እፎይታ ለማግኘት ነው፡፡

ማሳሰቢያ

 • እራስን በቤት ውስጥ የማከም ጥረት ወይ በራሱ በታማሚ ነው፤ ወይም
 • በአስታማሚው ይሆናል፤
 • በቀን ማለት ቀንና ሌቱን ጨምሮ 24 ሰዓት ማለት ነው፤
 • የሚዘጋጀው ሻይ የዳማከሴ እና የጨሞ ሻይ ስኳር አይጨመርበትም፤
 • ከሻይው በተጨማሪ በቀን እስከ 3 ሊትር ውሃ መጠጣት ያስፈልጋል፤
 • ጨሞን ከ 6 ዓመት በታች የሆነ ህፃን አይጠጣም፤
 • ጨሞ በተለያየ ቦታ የተለያየ ስያሜ አለው፡፡

የጉንፋን መድኃኒት በቤት ውስጥ

1ኛ/ የዳማከሴ ሻይ

ዳማከሴ- የደጋ እና የቆላ የሚባል፣ ዱር በቀል እና የቤት፣ ሻካራ እና ለስላስ በማለት ብዙ ዓይነታት አሉ፡፡ የተገኘውን መጠቀም ይቻላል፡፡ አንድ ጭብጥ የዳማከሴ ቅጠል መውቀጥ እና ከአንድ ብርጭቆ ውሃ ጋር ማፍላት እና አጥልሎ መጠጣት፡፡  በቀን ሁለት ጊዜ እስከሚሻል ድረስ መጠቀም ጥሩ ነው፡፡

(ምስል ሁለት- የደጋ ዳማከሴ ተክል)

2ኛ/ ጨሞ ሻይ

የጨሞ ሻይ በዋናነት በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ይታወቃል፡፡ ለብዙ በሽታ ይረዳል ብለው ይጠጡታል፡፡ ዛሬ በዚህ ርዕስ ሥር ለጉንፋን ጥሩ ማከሚያ መሆኑን ለመንገር ነው፡፡ የሚዘጋጁ ነገሮች፡-

 • እርጥብ የቡና ቅጠል፤
 • ቀይ ሽንኩርት፤
 • ነጭ ሽንኩርት፤
 • ቃሪያ፤
 • ዝንጅብል፤
 • የበሶቢላ እርጥብ ቅጠል፤
 • እንስላል እርጥብ ቅጠል፤
 • ጤና አዳም ቅጠል፤
 • የድንብላል ቅጠል፤ (በምስሉ ላይ የለም)
 • ጨው፤

ከላይ በምስሉ ላይ ያሉት ሁሉን እና በምስሉ ላይ ያልተካተተ የድንብላል ቅጠል ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እንደየአካባቢው ከዚህም ሌላ ኮረሪማ ተወቅጦ እና የነጭ ሪያን ቅጠል የሚጨመርበትም አካባቢ አለ፡፡

አሠራሩ፡-

 • ቀድሞ እርጥብ የቡና ቅጠል ለብቻው ይወቀጣል፤

(ምስል ሦስት፡- የቡና ቅጠል እና ከተወቀጠ በኋላ)

 • በተጣደው አንድ ሊትር ውሃ ውስጥ ቀድሞ ይፈላል፡፡ ጥቂት ጊዜ (ከ 5 እስከ 1ዐ ደቂቃ) ከፈላ በኋላ

ቀጥሎ ቀይ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ቃሪያ እና ዝንጅብል በአንድ ላይ ይወቀጣሉ፡፡ ይህ ድቁስ (ከሥር ምስሉ ላይ ያለው) ተጨምሮ እስከ 3 ደቂቃ ይፈላል፡፡

(ምስል አራት ድቁሱ)

በመጨረሻም የበሶቢላ፣ የእንስላል፣ የጤና አዳም እና የድንብላል ቅጠላቸው ተጨምሮ አብሮ ለ 2 ደቂቃ ይፈላል፡፡ ጨው በመጠን እየታየ ይጨመራል፡፡

(ምስል አምስት፡-  እንስላል፣ በሶሲላ ጤናአዳም እና ጨው)

አሁን ይህን የመሰለ የጨሞ ሻይ ይቀዳል፡፡ ቡና አረጓ ቅጠሉም ቢሆን ተወቅጦ ሲያፈሉት ቡናማ ቀለም

አለው፡፡

 

(ምስል ስድስት፡- የጨሞ ሻይ)

ከአንድ ሊትር ውሃ ከ 4 እስከ 6 የሻይ ብርጭቆ ጨሞ ሻይ መቅዳት ይቻላል፡፡ የጨሞ ሻይ በተጨመሩት ቅመማት እና በተለይም በቃሪያው ምክንያት ጉሮሮን ያተኩሳል፡፡ በዚህ ጊዜ በጉንፋን ለተያዘ ሰው እፎይታን ይለግሳል፡፡ አንዴ የተቀቀለውን አሳድሮ ዳግም ማፍላት ይቻላል፡፡ ነገር ግን፣ ትንሽ ጨው መጨመር ያስፈልጋል፡፡  ከአንድ እስከ ሁለት የሻይ ብርጭቆ ጠጥቶ መተኛት፡፡ በቀን ሁለት ጊዜ መጠጣት ጥሩ ነው፡፡ ለአንድ ሳምንት ወይም ከዚያም በላይ መጠጣት ይቻላል፡፡ ጉንፋኑ ይዳከማል፣ ታካሚው ቶሎ ያገግማል፡፡ (አስተውሉ! ጨሞ የሚጠጣው ከምግብ በኋላ ነው፡፡)

ማጠቃለያ፡-

የዳማ ከሴ ሻይ እና የጨሞን ሻይ እያፈራረቁ መጠጣት ይበልጥ ይረዳል፡፡ ሌሎችንም እንደ ተስማሚነታቸው ጁስ እና ውሃን አብዝቶ መጠጣት ይረዳል፡፡

ጨሞን አሁን ለጉንፋን መሆኑ ተነገረ እንጂ፣ በተለመደበት አካባቢ ለምሳሌ ዳውሮ፣ ቤንች፣ ማጂ፣ጎፋ፣ እና ሌሎችም አሁን ለጊዜው ያልተጠቀሱት ዘንድ ተዘውታሪ እና የተቀቀለ በቆሎ፣ የጐደሬ ሥር እና የሐረግ ቦዬ ሥር እንዲሁም የተቀቀለ የኮቴ ሐሬ (ባየር ቦዬ) ፍራፍሬ ማባያ ትኩስ መጠጥ ነው፡፡ እንደዚህ ሲያቀርቡት ለዕራት ወይም ለቁርስ ሊሆን ይችላል፡፡

ሌሎቻችሁ ለጉንፋን እስቲ ሞክሩት፣ የተሻለ መፍትሔ ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡ አለዚያም እድል ገጥሞችሁ ወደ እነዚህ አካባቢ ስትሄዱ ጨሞን በወጉ አጣጥሙት፡፡

ጨሞ የሚፈላው ተለቅ ባለች ሸክላ ማሰሮ ነው፤ ደግሞም በቅል መጠጫ ነው የሚጠጣው፤ ከተሜዎች ማሰሮ ላታገኙ ትችሉ ይሆናል፤ የምታፈሉት እቤት በሚገኝ የሻይ ማንቆርቆሪያ ነው፡፡

በምስሉ ላይ ያለው መጠን ጨሞን ለማያውቁት “ይህ ሁሉ ብዙ ነው- ይፋጃል” ይሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን፣ ለአካባቢው ተመልካች ከማነሱ የተነሳ “ይቺን ታህል ምን ብለው ያፈላሉ” ነው የሚሉት፡፡  ብቻ ይህን ትኩስ መጠጥ ቀን ያነሳው ዕለት አገር አቀፍ መጠጥ ይሆናል፤ ጠብቁት፡፡

የጨሞ ሻይ በመጠጣት ጉንፋንን ተከላከሉ!

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com