ቀይሥር ለጤና

Views: 448

                                                             ምሥል 1፡- ቀይሥር ጎረድ-ጎረድ

መግቢያ 

ከብዙ ጊዜ ጀምሮ በእኛ አገር ውስጥ ቀይሥር ምንም ጥቅም የለውም”  የሚል አጉል ሀሜት ተወርቶበት ነበር፡፡ ሆኖም ቀይሥር ብዙ የጤና ጥቅሞች አሉት፡፡ ሐሜቱ ከማን ቀድሞ እንደ መጣ? ለምንስ እንደመጣ? የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡ ብቻ ያ ሐሜት ሥር አውጥቶ፣ ግንድ አበጅቶ፣ ቅርንጫፍ ዘርግቶ “ጉልበታም መረጃ” ሆነ፡፡ እናም ማንም ሰው “ቀይሥር ምንም ጥቅም የለውም”  ቢል እና መረጃ አቅርብ ቢባል፣ “አገር ያረጋገጠው ነው” ይላል፡፡

አገር የተባለው መረጃ ያ የገዘፈው ጉልበታም ሐሜት ነው፡፡  በምግብ ላይ ሆን ተብሎ ወይም ባለማወቅ ብዙ ጉልበተኛ ሐሜቶች ልክ እንደ ቀይሥር፣ በጤፍ ላይ “ጤፍ ጥቅም የለውም ጭድ ነው፣ ገለባ ነው ወዘተ” ተብሎ ነበር፡፡ የጤፉ ሐሜት እንኳን ተነቅቶበታል፡፡ ጤፍን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት እና ለመንጠቅ የተደረገ ሙከራ ነበር፡፡ ሙከራውም ከሸፎአል፡፡

በቀይሥር ጉዳይ ዋናዋናው ፍሬ ነገር፡-

  • በጣም ጠቃሚ የጤና በረከቶች አሉት፤
  • በሬ ለእርሻ የሚሉ እና ሥጋን ለማይበሉት አማራጭ ይሆናቸዋል፣ (ይሆነናል)፤
  • የአገር ምርት ነው በቀላል ዋጋ ዓመቱን ሙሉ መግዛት ይቻላል፤
  • በቀላሉ ለምግብ ማሰናዳት ይቻላል፤
  • በዓለም ላይ ባለ ብዙ ጠቀሜታ ነው፤

1ኛ/ የቀይሥር የጤና በረከት ማጣቀሻ አንድ

ሀ. ቀይሥር ምን ንጥር-ነገር አለው

ለምሳሌ አንድ መቶ ግራም የበሰለ ቀይሥር አነስተኛ ካሎሪ እና ፕሮቲን፣ ነገር ግን ተመጣጣኝ አሰር፣ ቫይታሚን ሲ፣ ቫይታሚን ቢ6፣ ናይትሬትስ፣ ማግኒስየም፣ ፖታስየም፣ ፎስፈረስ፣ ማንጋኒዝ፣ እና አይረን አለው፡፡

የደም ግፊት ሚዛን ይጠብቃል

ብዙ ናይትሬስ ስለያዘ የደም ግፊትን የመቀነስ ተጽዕኖ አለው፡፡ ይህም ለልብ ህመም እና ለልብ ድካምና እ‹‹ስትሮክ›› የመጋለጥን አደጋ ይቀንሳል፡፡

አቅም ያበረታል

የደም የናይትሬት ይዘትን ከ2 እስከ 3 ሰዓት ጊዜ ውስጥ ከፍ ያደርጋል፤ ስለዚህ የጉልበት ሥራ ከመሥራት በፊት፣ ረዥም የእግር መንገድ ከመጀመር በፊት፣ የተራራ ላይ ጉዞ ከማድረግ በፊት፣ የእስፖርት ልምምድ ከማድረግ በፊት ደህና አድርጎ የቀይሥር ጁስ፣ ጎረድ ጎረድ ወይም የቀይሥር ክትፎ ጥስቅ ማድረግ ነው፡፡ (እንደ አቅሙ አንድ ሰው ከ 1ዐዐ እስከ 2ዐዐ ግራም ሊመገብ ይችላል፣ ወይም ጁስ ቢሆን ከአንድ ኩባያ እስከ ግማሽ ሊትር ሊጠጣ ይችላል፡፡)

ለምግብ ስልቀጣ ይረዳል

የስነምግብ አሰር ስላለው ለምግብ ሥርዓተ-ስልቀጣ ይረዳል፡፡ ስለዚህም፣ የትልቁ አንጀት ድርቀትን በመከላከል፣ በፊንጢጣ አካባቢ የሚከሰቱ እንደ ብግነት፣ ማቃጣል እና የትልቁ አንጀት ካንሰር ለመከላከል እጅግ ይረዳል፡፡

የደም ዝውውር ያሻሽላል

በቀይሥር ውስጥ የሚገኘው ናይትሬት የደም ዝውውርን ያሻሽላል፡፡ የደም ፍሰት መሻሻል ብዙ የጤና ጥቅም አለው፡፡ ለምሳሌ በዓይነት 2 የስኳር በሽታ፣ የማስተዋል አቅም ለማጎልበት እና ለመሳሰሉት፡፡

ክብደት ለመቀነስ

ቀይሥር በተፈጥሮው የሥነምግብ አሠር እና ጣፋጭነት አለው፡፡ በትንሹ ሲበሉት በብዙ ያጠግባል፡፡ እናም ለጊዜው የምግብ ፍላጎትን ይቀንሳል፡፡ በዚህ ዘዴ ክብደትን ለማስተካከል የሚፈልጉት ሊጠቀሙት ይችላሉ፡፡

2ኛ፣ ቀይሥር ለምግብ ማሳናዳት

ሀ/ የቀይሥር ክትፎ

ለማሰናዳት እና ሰርቶ ለማቅረብ የሚፈጀው ጊዜ 15 ደቂቃ፣

የሚያስፈልገው ወጪ ለቀይሥሩ ከ1 እስከ 2 ብር፣ ሌሎች ቅመሞች ከ 3 እስከ 1ዐ ብር፣

አሠራሩ

ቀይሥሩን ማጠብ፣ በመሸርከቻ መሸርከት (መፈቅፈቅ)፣ በድስት ውስጥ ዘይት፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት እና ጨው፣ ጋር ለ 5 ደቂቃ ማብሰል (ያለምንም ውሃ መጠባበስ) ከዚያም የሚፈልጉትን ቅመም ወይም ቅቤ መጨመር እና ማቅረብ፡፡ እንዲሁ በሹካ ይበላል፣ በእንጀራ ወይም በዳቦ ይበላል፡፡ በቃ ይኸው እንደዚህ፡፡

የቀይሥር ክትፎ

ለ/ የቀይሥር ጎረድ ጎረድ

ለማሰናዳት እና ሰርቶ ለማቅረብ የሚፈጀው ጊዜ  አንድ ሰዓት

የሚያስፈልገው ወጪ ለቀይሥሩ ከ1 እስከ 2 ብር፣ ሌሎች ቅመሞች ከ 3 እስከ 5 ብር፣

አሠራሩ ቀይሥሩ ይታጠባል፣ ሳይላጥ በውሃ ይቀቀላል፣ ከ5ዐ ደቂቃ በኋላ ይበስላል፡፡ ከበሰለ በኋላ ይላጣል፣ በሚፈልጉት መጠን ጎረድ፣ ጎረድ አድርጎ መክተፍ፡፡ የሎሚ ውሃ፣ ጨው፣ ዘይት፣ ወይም የፈለጉትን ቅመም መጨመር እና ማቅረብ፡፡ ለምሳሌ እንደዚህ፡፡

የቀይሥር ጎረድ ጎረድ

ሐ/ የቀይሥር ጁስ

ለማሰናዳት እና ሰርቶ ለማቅረብ የሚፈጀው ጊዜ  አንድ ከሩብ ሰዓት

የሚያስፈልገው ወጪ ለቀይሥሩ ከ1 እስከ 2 ብር፣ ሌሎች ቅመሞች ከ 3 እስከ 6 ብር፣

አሠራሩ ቀይሥሩ ይታጠባል፣ ሳይላጥ በውሃ ለአንድ ሰዓት ይቀቀላል፣ ከበሰለ በኋላ ይላጣል፣ ይከተፋል፣ በ5ዐ ግራም (አንድ መካከለኛ ቀይሥር) ላይ አንድ ኩባያ ውሃ ይጨመርና በጁስ መፍጫ በደንብ ይፈጫል፡፡ ትንሽ የሎሚ ውሀ፣ ማር ወይም ሌላ የሚፈልጉትን ቅመም መጨመር ይችላሉ፡፡ ይህ በምስል ላይ ያለው ሁለት አነስተኛ ብርጭቆ ከአንድ መካከለኛ ቀይሥር የተሠራ ነው፡፡

የቀይሥር ጁስ

ማሳሰቢያ

  • ቀይሥር የኩላሊት ጠጠር በሽታ ያለበት ሰው መመገብ የለበትም፡፡ ጠጠሩን ታክሞ ካስወገደ በኋላ ግን መመገብ ይችላል፡፡
  •  ሌሎቻችሁ ያለምንም ጭንቀት በሳምንት እስከ ሁለት ቀን (በሳምንት እስከ 4 ጊዜ) መመገብ ትችላላችሁ፡፡ ስትመገቡ ግን ሽንት ወይንጠጅ ቀለም ይኖረዋል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ አትረበሹ፡፡

3ኛ ቀይሥር በሌሎች አገራት

ቀይሥር በሌሎች አገራት እንደ እኛ መቀለጃ አይደለም፡፡ ከምግብነት አልፎ ለምሳሌ ለመድኃኒት ይውላል፣ ለመድኃኒት ማሳናጃ፣ ለምግብ ቀለማት እና ለሌላም ተግባራት የትየለሌ ይጠቀማሉ፡፡ ለምሳሌ ጀርመን በከፍተኛ መጠን ታመርታለች፣ በከፍተኛ መጠን ወደ አገር ውስጥ ገበያ ገዝታ ታስገባለች፡ እንደገና መልሳ ወደ ውጪ ገበያ ትልካለች፡፡ ሌሎችም እንዲሁ በጥሩ ሁኔታ ይጠቀማሉ፡፡

ማጠቃለያ

ቀይሥር ጥሩ ምግብ ነው፡፡ ባልተረጋገጠ ወሬ ጥቅም የለውም መባሉ የሚያሳዝን ነው፡፡ አሁን ገበያ ላይ የሚሸጥበት ዋጋ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ (ለምሳሌ አንድ ኪሎ ከ 5 እስከ 1ዐ ብር ነው) በዚህ ዋጋ እየተሸጠ ተመጋቢ በበቂ መጠን አለመጠቀሙ ቅር ያሰኛል፡፡ እንግዲህ ተመጋቢ ከጠፋ ወደ ውጪ መሸጥ፣ ወይ ለእንስሳት መኖ መጠቀም ይከተላል፡፡

ጤናችሁን ተንከባከቡ፣ በወቅቱ ገበያ ላይ ያሉትን አትክልት በአግባቡ ተመገቡ፡፡

ማጣቀሻ

ማጣቀሻ አንድ     https://www.healthline.com/nutrition/benefits-of-beets

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com