ዜና

የኢትዮ-ጃዝ አባት ሙላቱ አስታጥቄ ዳግም ከበረ

Views: 531

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ፣ ከፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ (‹‹ባለ ዋሽንቱ እረኛው››) ለጥቆ፣ በኢትዮጵያ ሙዚቃ አድማስ ላይ የናኘው የሙዚቃ ሰው ሙላቱ አስታጥቄ፤ ዳግም (በተደጋጋሚ) በአውሮጳ/ዓለም የሙዚቃ መድረክ ላይ ከበረ፡፡

‹‹የኢትዮጵያ-ጃዝ ሙዚቃ አባት›› የሚል የክብር ሥም የተሰጠው ሙላቱ አስታጥቄ፣ የፈረንሳይ (‹‹ኦርድሬ ዴስ አርትስ ኤት ዴስ ሌትሬስ››) በተሰኘ ተቋም፣ የከበረ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡ በሥነስርዓቱ ላይ የክብር እንግዳ የነበረው ኢትዮጵያዊው የሙዚቃ ባለሟል፣ በፈረንሳይ የባሕል ሚንስትር ፍራንክ ሪስተር ጋባዥነት በአዲስ አበባ ተበርክቶለታል፡፡

‹‹በዓለም የሙዚቃ ዘውግ ጥቂት አርቲስቶች ብቻ ሀገራዊ ባሕላቸውንና ቀለማቸውን እንደያዙ እውቅና ያገኛሉ፤ ሙላቱ አስታጥቄ ከነዚህ ጥቂቶች አንዱ ነው›› ሲሉ ፍራንክ ሪስተር በፈረንሳይኛ በቲውተር ገፃቸው ላይ ገልጸዋል፡፡ ከፈረንሳዩ ጃዝ-ቫዮሊንስት ቲዮ ጋር በአዲስ አበባ በጋራ የተጫወተውንም ሙዚቃ ‹‹ፖስት›› አድርገዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ1943 ዓ.ም ጅማ ክፍለ ሃገር የተወለደው ሙላቱ አስታጥቄ፣ የሙዚቃ ትምህርቱን በለንደን፣ ኒዮርክ፣ ቦስተን ከተሞች የተማረ ሲሆን፣ ባለአምስት ቅኝቱን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ከፍ አድርጎ የጃዝ ሙዚቃ ቃናን በማከል፣ የላቲን አሜሪካ የሙዚቃ ድምፆችንና ‹ሪትም› በመጨመር እና ከኢትዮጵያ ባሕላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች በተለይ ትንንሽ ከበሮ (ድራም) መሳይ የሙዚቃ መሳሪያዎች ጋር በማዋሃድ፣ በሚፈጥረው ልዩ ጥዑመ-ዜማ፣ አድናቆትን ከአድማስ ባሻገር ባለ ማኅበረሰብ ያገኘ ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ አድርጎታል፡፡

የ75 ዓመት የእድሜ ባለጸጋው ሙላቱ አስታጥቄ፣ ከበርካታ ሙዚቃ ባንድ ጋር የሰራ ሲሆን፣ ዋሊያስ ባንድ እና ኢትዮ-ጃዝ ቡድን ዋና ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ኦርድሬ ዴስ አርትስ ኤት ዴስ ሌትሬስ በ1957 በፈረንሳይ የተመሠረተ ሲሆን፣ በጥበብ ላይ እና በሥነጽሑፍ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ላበረከቱ የጥበብ ሰዎች እውቅና የሚሰጥ ተቋም መሆኑን ቢቢሲ ገልጿል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com