ዜና

መንግሥት አትራፊ የልማት ድርጅቶችን በዓለማቀፍ ገበያ ለመሸጥ የያዘው እቅድ ውዝግብ አስነሳ

Views: 225

በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢቲዮ-ቴልኮም፣ መብራት ኃይል ያሉ አትራፊ ሀገራዊ ትልልቅ የልማት ድርጅቶችን ለመሸጥ የያዘው እቅድ ውዝግብ አስነሳ፡፡

በሀገሪቱ የሚገኙ የምጣኔ ሃብት ባለሟሎችና በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦች ዛሬ ጠዋት በአዲስ አበባ ተገናኝተው እንደ ኢትዮ-ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመሳሰሉ ታላላቅ የህዝብ ተቋማትን ወደ ግል ይዞታነት የመቀየር አስፈላጊነት እና ጎጂነት ላይ መክረዋል፡፡

መድረኩ በአትዮጵያ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች ላይ የውይይት መድረኮችን በሚያዘጋጀው ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (forum for social studies (FSS)) በተባለ ድርጅት የተካሄደ ነው፡፡

በውይይቱ ላይ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ካቀረቡ የምጣኔ ሃብት ምሁራን መካከል የቀድሞው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ነበሩት አቶ ክቡር ገና አንዱ ናቸው፡፡  የምጣኔ ሃብት ባለሟሉ አቶ ክቡር፣ ‹‹ላለፉት 50 ዓመታት ያህል በአይ ኤም ኤፍ እና በዓለም ባንክ መመሪያ በተሰጡት የመንግሥትንና የማኅበረሰብን ንብረት ወደ ግል ይዞታ ማዞር (ፕራይቬታይዜሽን) ፖሊሲ አማካይነት ተታልለናል›› ብለዋል፡፡  አቶ ክቡር ገና በጽሑፋቸው ከዚህ ቀደም ሩስያ እና ቻይና እንዴት ተቋማቸውን ወደ ግል ይዞታነት በዘዴ እንደቀየሩ እና ህዝባቸውን ተጠቃሚ እንዳደረጉ በምሳሌነት አውስተዋል፡፡  በሌላ በኩል፣ ጎረቤታችን ኬንያ ከአስር ዓመት በፊት የአየር መንገድ ንግዷን ወደ ግል ይዞታነት በማዞሯ የገጠማት ኪሳራ በአቶ ክቡር የጥናት ወረቀት ላይ የተጠቀሰ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግስትም  የኬንያ ተመሳሳይ እጣ እንዳይደርሰው ነገሩን ቆም ብሎ ቢያጤነው መልካም እደሆነ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ዓላማው የተቋማቱን የአገልግሎት ደረጃ ማሻሻል እና ማብቃት ከሆነ ሌሎች የተሻሉ አማራጮችን በስፋት መመልከት እንዳለበት የገለጹት አቶ ክቡር ገና፣ ከዚህ ጀርባ ሌላ አጀንዳ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም፣ እንደ ዓለም ባንክ ያሉ ታላላቅ የገንዘብ ተቋማት ተጽእኖ ስር እንደሆንን ያላቸውን ስጋት አስቀምጠዋል፡፡

አቶ ክቡር ገና በጥናት ጽሑፋቸው ላይ በርካታ የመፍትሄ ሃሳቦችን ያስቀመጡ ሲሆን፣ ተቋማቱን መሸጥ ግድ ከሆነ ደግሞ ለሃገር ውስጥ ባለሃብቶች መሸጥ ወይንም ህብረተሰቡ አክሲዮን እንዲገዛ በማድረግ የሀገሩ ባለቤት የሆነውን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ አስፈላጊ ነው የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉ በርካታ ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው፣ ጉዳዩ የሃሪቷን ሉዓላዊነት እና የህዝቦቿን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ መከናወን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹የኑሮ ውድነት፣ የተቋማቱ መዳከም፣ እንዲሁም ሃገሪቱ የገባችበት የውጭ እዳ፣ መንግሥት በፍጥነት ኢኮኖሚውን ለማስተካል አንዳንድ ትልልቅ ተቋማትን ለመሸጥ እንዲገደድ አድርገውታል››  ያሉት ደግሞ ዶ/ር ብሩክ ተስፋዬ፣ በኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስትር አማካሪ ናቸው፡፡

አቶ ብሩክ የኢንዱሰትሪያል ፓርኮችን ወደ ግል ይዞታነት ለመቀየር በስፋት የታሰበ መሆኑን ገልጸው፣ ለሃገር ውስጥ ባለሃብች በሮች ክፍት እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

በሃገሪቷ 44.3 ከመቶ የሚሆነው የማህበረሰብ ክፍል ብቻ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የሚያገኙ ሲሆን፣ መንግሥት ይህን ቁጥር ወደ 86.2 ከመቶ ለማሳደግ መስራት እንዳለበት በውይይቱ ተገልጻል፡፡

በተለይም፣ ብዙ ክፍተቶች ያሉበት የኢትዮጵያ ኤሌክትክ ኃይል ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም መዋዕለ-ነዋይ ፈሶበት በርካታ በጨለማ የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እዲያገለግል ያስፈልጋል ነው የተባለው፡፡

አቶ ክቡር ገና ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ አየርመንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የመብራት ኃይል እና ሌሎች ትርፋማ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን መሸጥ የሚያስከትለውን ሀገራዊ ኪሳራ የሚያመላክቱ ጥናታዊ ጽሑፎችን በማቅረብ መንግሥት ታሪካዊ ስህተት እንዳይፈጽም በመወትወት ላይ ናቸው፡፡

‹‹እነዚህን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ባንሸጥ አንሞትም›› የሚለው ንግግራቸው ደግሞ ተጠቃሽ ነው፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com