ዜና

በድርቅ በተጎዱ የአርብቶ አደር አካባቢዎች የእንስሳት ደህንነት ጥበቃ መከናወን አለበት ተባለ

Views: 150

በኢትዮጵያ በድርቅ ለተጎዱ አርብቶ አደሮችና አርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ ለሚገኙ ማኅበረሰቦች አስቸኳይ የእንስሳት ደህንነት ጥበቃ አገልግሎት መስጠት፣ ማኅበረሰቡን መታደግ ነው ተባለ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ይህን እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል

ይህ ድርጅት፣ በተባበሩት መንግስታት ማዕከላዊ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ፈንድ እና በአውሮፓ ኮሚሽን የሰብዓዊ ዕርዳታ ክፍል በተደረገለት የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ ውስጥ በድርቅ ለተጎዱ አርብቶ አደሮች የገንዘብ ድጋፍ የማድረግና የህክምና ዘመቻዎችን የማከናወን ሥራ ላይ ይገኛል፡፡

በድርቅ በተጎዱት አካባቢዎች ያሉት አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን እንዲሸጡና ገንዘብ እንዲያገኙ በማድረግ ውስን የሆነውን የግጦሽ መሬት ጫና እንዳይበዛበት እያደረገ ነው፡፡

በተጨማሪም፣ አርብቶ አደሮቹ ለሌሎች አስፈላጊ ለሆኑ ፍላጎቶቻቸውን ለሟሟላት እንዲረዳቸው በድርጅቱ በኩል የጥሬ ገንዘብና የከብት መኖ ድጋፍ እየተሰጣቸው እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም፣ ማኅበረሰቦቹን ለማገዝ የእንስሳት እርባታ ዝግጅቶችን ለመንደፍ፤ ለመተግበርና ለመገምገም ቁልፍ መመሪያ ቀርጾ እየሰራ ነው ተብሏል፡፡

በአትዮጵያ የግብርና ሚኒስትር የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አለማየሁ መኮንን እንደሚናገሩት፣ ከአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ እና ሶማሊያ ክልል የሚመጣው የእንስሳት መድኃኒት አቅርቦት እጥረት ስላለው፣ ድርጅቱ በከብቶች ላይ በሚደርሰው ድንገተኛ አደጋ እና በሽታዎችን በመከላከልና ምላሽ በመስጠት ረገድ ቁልፍ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል፡፡

ይህ በድርጅቱ የሚቀርበው የእንስሳት መድኃኒት የእንስሳቱን ጤና በመጠበቅ እንዲሁሙ የመኖ አቅርቦቱ በአካባቢው ያለውን የድርቅ ተጋላጭነት (ተፅዕኖን) ለመቀነስ የሚረዳ ነው የሚሆነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የእንስሳት እርባታ ዘርፍ በአፍሪካ ውስጥ ትልቁ ሲሆን፣ ከጠቅላላው የሀገር ውስጥ ምርት 20 በመቶ ገቢ የሚያስገባ ሲሆን፤ ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች ደግሞ 15 በመቶውን ገቢ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡

ሆኖም፣ በሀገሪቱ የሚከሰተው የዓየር ንብረት ለውጥ በእንስሳት እርባታው፤ ምርታማነትና የማራባት አቅም ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡

ተደጋጋሚ ድርቅና ዝቅተኛ የዝናብ መጠን በመኖ ምርት፤ በውሃ አቅርቦት፤ በአትክልትና ዕፅዋት ላይ ተፅዕኖ በማሳደር እንስሳቶች እንዲታሙና እንዲጎዱ ያድርጋል፡፡ በአርብቶ አደሮች የምርት አቅርቦት ላይ ስጋት እየፈጠረ ይገኛል ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ተወካይ ወ/ሮ ፋጡማ ሰዒድ እንደገለጹት፣ ድርጅቱ ከ150 ሺህ በላይ አርብቶ አደር አባወራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የእንስሳትን የጤና እና የአካል ሁኔታ ወደነበረበት ለመመለስና የሚሞቱትን ቁጥር በመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም፣ የድርጅቱ ዓላማ በተከታታይ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች ላይ ያሉ ማኅበረሰቦችን ኑሮ ማሻሻልና በድርቅ የተጎዱትን ደግሞ በፍጥነት ማገገም እንዲችሉ ማገዝ ነውም ብለዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com