ዜና

ኢትዮጵያዊው ፎቶ-ጋዜጠኛ በሀገረ ካናዳ ትኩረት ስቧል ተባለ

Views: 182

ኢትዮጵያዊው ፎቶ-ጋዜጠኛ ዳዊት ጥበቡ፣ በቀን ተቀን የምስለ-ትረካ (ፎቶግራፍ) ሥራው፤ የብዙኃንን ቀልብ በሀገረ-ካናዳ መሳብ ችሏል፡፡

ከሀገሩ ኢትዮጵያ ከተሰደደ ሁለት ዓመት የሆነው ፎቶ ጋዜጠኛ ዳዊት ጥበቡ፤ በፍጥነት በሚንቀሳቀሰው የምዕራቡ ዓለም ውስጥ፣ አስደናቂ ኹነቶችን በፎቶ በማንሳትና በምስል በመተረክ እየታተረ ይገኛል፡፡

በዚህ የቀን ተቀን ሥራው የቶሮንቶው ግሎባል ኒውስ ትኩረትን ስቦ የዳዊትን የእለት ተዕለት እንስቃሴ ለብዙሃኑ እወቁለት ብሎ መረጃውን ይፋ አድርጓል፡፡

ዳዊት ከዚህ ቀደም በዓለም አቀፍ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች፤ በቢል እና ሚልንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን እንዲሁም በሴቭ ዘ ችልድረን በሙያው አገልግሏል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ካናዳ ያቀነው ዳዊት፣ በእንያንዳንዱ የሕይወት እርምጃው ፎቶግራፍን በመጠቀም ታሪኮችን ለመንገር እና ለማጋራት ቆርጦ ይነሳል፡፡

‹‹ፎቶግራፍ ማለት፣ እኔ ማን እንደሆንኩ ታሪኬን የሚነግርልኝ ጥበብ ነው፤ከልጅነቴ ጀምሮ ፍላጎቴ ይኼው ነው፡፡  ትምህርት ስሄድ ህልሜን አንግቤ ነበር፤ አሁን በቃ የኔ ምኞት ፎቶ ጋዜጠኛ መሆን ነበር›› ሲል ለግሎባል ኒውስ ጋዜጠኛ ለሆነችው ሱዛን ገልጿል፡፡

ዳዊት ሃሳቡን ለሱዛን ሲገልጽ ‹‹በመንገድ ላይ የማገኛቸውንና ሰዎች ሊማሩባቸው ይችላሉ ብዬ የማስባቸው ታሪኮችን በ‹‹ጉዞ ስቶሪስ›› ላይ አጋራዋለሁ፡፡

ዳዊት ስለ ‹‹ጉዞ-ስቶሪ›› ትርጉም ሲያብራራ  ‹‹ይህን ስያሜ  የሰጠሁትም  በሁሉም ዘንድ የሚታወቅ ነገር በመሆኑ እና ለመተዋወቅ እንዲሁም  ለመማማር የሚያስችል በመሆኑ ነው›› ብሏል፡፡

ፎቶ ጋዜጠኛው ዳዊት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ወስጥም 200 ታሪኮችን በኢንስታግራም እና በፌስቡክ ማጋራትም ችሏል፡፡

በዚህም ብዙ ሰዎች፤ ጥሩ ልምድ እንደሆነ መስክረውለታል፡፡

ጉዞ ስቶሪስ፤ ታሪኬን ለመንገር ጥሩ አጋጣሚ ሆኖኛል የሚለው ዳዊት  ሌሎችም ቢሆን ታሪካቸውን ለማጋራት ወደውታል፡፡

ስለ ካናዳ እና ቶሮንቶ ነዋሪዎች የተጠየቀው ዳዊት፣ ሲመልስ  እዚህ ሀገር  ሰዎች እርስ በእርሳቸው የሚያወሩበት አጋጣሚ የለም፤ ሁሉም ያለው ስልኩ ላይ ብቻ ነው፤ እሱን ብቻ ነው የምንመለከተው  አጠገባችን ማን እንዳለ እንኳን አናውቅም ብሏል፡፡

ቶሮንቶ ከተለያዩ አገራት ለሚመጡ ሰዎች ቤታቸው ሆናለች፤ ግን አሁንም ቢሆን ጎረቤቶቻችን ማን እንደሆነ አናውቅም ይላል የብዙ ሰዎችን ታሪክ በፎቶ የሚያጋራው ዳዊት፡፡

እኔ በማጋራው ታሪኮች ውስጥ ስለ ሕይወት የተወሰነ ግንዛቤ ይሰጣል ብዬ አምናለሁ፤ ምክንያቱ እዚህ ሁሉም ሰው ሩጫ ላይ ነው ያለው፡፡

እነዚህ ታሪኮች ግን የሰዎችን የሕወት ውጣ ውረድ ለማሳየት የራሳቸው ድርሻ ይኖራቸዋል ብሎ የሚያምነው ፎቶ ጋዜጠኛ አሁንም ቢሆን በጣም ውጥረት ውስጥ ባሉ ካናዳውያን መካከል ሆኖ የሌሎችን ታሪክ እያጋራም ይገኛል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com