ዜና

ኢዜማ በመቀሌ ያደረግኩት ህዝባዊ ስብሰባ ተስፋ ሰጪ ነው አለ

Views: 368

– በቀጣይ በአደዋ፣ ተምቤን፣ አክሱም እና በሌሎች ሥፍራዎች ሕዝባዊ ውይይት ይኖረኛል ብሏል

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በትላንትናው ዕለት መስከረም 4 ቀን 2012 ዓ.ም ከመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ውይይቱን አካሂዷል፡፡

የፓርቲውን የፖለቲካ ዓላማ ለማስተዋወቅ ወደ መቀሌ ከተማ ያቀናው ኢዜማ ፓርቲ፣ ከትግራይ ሕዝብ ደማቅ አቀባበል እንደተደረገለት የኢዜማ ሊቀ መንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ለኢትዮ-ኦንላይን ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ሕዝብ  አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መመልከት አለበት፤ እኛም ፖሊሲያችንን ለማስተዋወቅ እና ሕዝባዊ ውይይት ለማከናወን አቅደን ወደ ትግራይ አምርተናል፤ በዚህም ተሳክቶልናል፤ ብለዋል አቶ  የሺዋስ አሰፋ፡፡

ከመቀሌ ሕዝብ ተሰብሳቢዎች መካከልም የመቀሌ ሕዝብ ይህን አይነቱን እድል አግኝቶ እንደማያውቅና አፈና እንዳለበት በስብሰባው ላይ ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም፣  በሕዝባዊ ስብሰባው ላይ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፤ የመሬት ጉዳይ፣ የሕገ መንግስቱ ጉዳይ  የፌደራል ሥርዓት አወቃቀር እና ሌሎችም ጥያቄዎች መነሳቱን አቶ የሺዋስ ገልጸውልናል፡፡

እንደ ሊቀመንበሩ ገለፃ፣ በሕዝባዊ ስብሰባው ላይ በርካታ ወጣቶችን ጨምሮ አረና ፓርቲ እና የህወሓት ደጋፊዎችም ስብሰባ ላይ ታድመዋል፡፡

በቀጣም በትግራይ ክልል በአደዋ፣ ተምቤን፣ አክሱም እና በሌሎች ቦታዎች አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ ያጣውን ወጣት ለማነጋገር እቅድ እንዳለም ከሊቀመንበሩ ለማወቅ ችለናል፡፡

ሆኖም፣ ኢዜማ ሕዝባዊ ውይይቱን ለማከናወን የተወሰነ የቢሮክራሲ ችግር እንደገጠው የገለጸ ሲሆን፣ የትግራይ ሀዝብ ግን ጨዋነቱን በአቀባበሉ መስክሮልናል ብሏል፡፡

ኢዜማ 404 ወረዳዎች ጽ/ቤት ያሉት ሲሆን፣ ከዚህ በኋላም ፓርቲው በተለያዩ ክልሎች በማምራት እና የሀገሪቱን ወቅታዊ ጉዳይ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ፕሮግራሞቹን እንደሚያስተዋውቅ ለኢትዮኦንላይ አስረድተዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com