ዜና

የኢትዮጵያ ገዳማት በእየሩሳሌም ታሪክና ወቅታዊ ሁኔታ

Views: 768

ነሐሴ 23 ቀን 245 6 ዓ.ም/ August 31 2019

የዴር ሱልጣን የኢትዮጵያ ገዳማት እናድን ስብሰባ ላይ የቀረበ ዋሽንግተን ዲሲ

መግቢያ
ኢትዮጵያ በእየሩሳሌም ከተማ ውስጥ ለዘመናት በዴር ሱልጣን ገዳም ያላትና መነኮሳቷም የሚኖሩባት ብቸኛዋ የአፍሪካ አገር ናት። ቀደም ብሎ እንደ አሁኑ ጊዜ የመጓጓዣ አገልግሎት ባልነበረበት ወቅት የበቁ የነቁ መነኮሳትና ደናግላን በእግራቸው በረሃ በማቋረጥ፣ ከሞት የተረፉት ቅድስት ሀገር ክርስቶስ ተወልዶባት ፣ ተመላልሶ ያስተማረባት፣ ተዓምራት የሠራባትንና ኋላም ለሰው ልጆች ቤዛ ሲል ስቃይና መከራን ተቀበሎ የተሰቀለባትንና ሞትን ድል አድርጎ የተነሳባትን እየሩሳሌምን ተሳልመው፣
ፀልየውና ፆመው ሊኖሩባትም የወሰኑ ብዙ ኢትዮጵያውያን ወንዶችና ሴቶች ነበሩ። አሁንም አሉ።

የገዳሞች ሁሉ እምብርት በሆነችውና ዴር ሱልጣን (Deir el-Sultan) የሱልጣን ወይም የንጉሡ ከተማ የምትባለው የክርስቶስ መቃብር አጠገብ በምትገኘው ገዳም ጉልላት ላይ የኢትዮጵያ ይዞታ ይገኛል። አካባቢው የጥንቱ የእየሩሳሌም ከተማ ሲባል ልዩ መለያው የክርስቲያኖች ሰፈር ተብሎ ይታወቃል። የተቆረቆረውም በአራተኛ ክፍለ ዘመን ነው ይባላል። ይህ ክርስቶስ ተሰቅሎ የተቀበረበት ሥፍራ “ጎሎጎታ” በመባልም ይጠራል። ክርስቶስ የተቀበረበት ቦታ ይባላል እንጂ በሦስተኛው ቀን
መቃብሩን ከፍቶ ወደ ሰማይ እንዳረገ የክርስትና ሃይማኖት እምነት ተከታዮች በሞላ ያምናሉ። ስለዚህም የመቃብሩ ቦታ ባዶ ነው። ይህ ታላቅ የፀሎት ቦታ ሲሆን ሥፍራውም በአማኞችና በጎብኝዎች እጅግ የተጨናነቀ ነው።

በዚህ ታላቅ የሃይማኖት ማዕከል የሮማ ካቶሊክ፣ የግሪክ ኦርቶዶክስ፣ የአርመን፣ የግብፅ ኮፕትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ይዞታ አላቸው። ከጥንት ጀምሮ በነኝህ የተለያዩ የክርስትና ሃይማኖት መሐከል ያለው ግንኙነት የሀብትና የይዞታ ጥያቄ ብዙ ጊዜ አወዛጋቢ ነው። አንዳንዶቹም እንደ ሃይማኖት ወንድማማችነት ሳይሆን የሚተያዩት እንደ ባላንጣ ሲሆን በዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ይዞታ አስከፊ ሁኔታ ለዘመናት የተጋረጠባት ነች። እንደ ሚባለው ይዞታዋን በየጊዜው እየተቀማች፣ መነኮሳቱ እየተበደሉና ህንፃውም ከጊዜ ብዛት እየፈራረሰና እየወላለቀ ይገኛል። ከዚህ በላይ እንደ መግቢያ ሁኔታውን ካስጨበትኩ በኃላ አሁን ስለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን
አመሠራረት ታሪክ፣ ስለጠቅላላ ይዞታና ስለ ወቅቱ ጉዳይ ላስረዳ።

የይዞታው ታሪክ
በእየሩሳሌም የኢትዮጵያ ይዞታ ታሪክ የሚገልፁ ፅሁፎችና ሰነዶች በአሁኑ ጊዜ በልዩ ልዩ ምክንያት ስለ ወደሙ በአብዛኛው ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ይህንን በተመለከተ በሚቀጥለው አርዕስት ሥር ለመግለፅ እሞክራለሁ። ሆኖም ግን በታሪክ ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ (ማክዳ ወይም እንደኬ) የእየሩሳሌሙ የንጉሥ ሰለሞንን ጥበብና ዕውቀት ስለምትሰማ ይህንን ጠቢብ በዓይኗ አይታ ጥበቡንም ለመቅሰም ፈልጋ የአገሯንም ሀብት ለገፀበረከት ይዛ ወደ እየሩሳሌም እንደተጓዘች ይነገራል። ይህ ገና
ከክርስትና ሃይማኖት በፊት ነበር።

ንጉሥ ሰሎሞንም ብዙ ተከታዮችና የጭነት እንስሳት ይዛ ከሩቅ አገር ከኢትዮጵያ ስለመጣች ፣ ለዚህ ሁሉ ታላቅ ጓዝ ማረፊያ በከተማው በእየሩሳሌም ቦታ ሰጣት ይባላል። ያ ይዞታ በኋላም ኢትዮጵያ የክርስትና ሃይማኖት ከተቀበለች በኋላ በኢትዮጵያውያኖች እጅ ቀረ ወይም ይዞታ ሆነ። ይዞታውም በየጊዜው እየተወሰደባት ተሸራርፎ ያነሰ ሆነ። ሆኖም ግን የኢትዮጵያ መነኮሳት ሁሉንም ተቋቁመው የአገራቸውንና የሃይማኖታቸውን ጥሪት የሆነችውን ጎልጎታን አሻራዋ እንዳይጠፋ አቆይተውልናል። በኋላም አንዳንድ የኢትዮጵያ ነገሥታት፣ በተለይ መኳንንቱና ወይዛዝርቱ በገንዘባቸው ለመነኮሳቱ መኖሪያ ቦታ እየገዙና ቤት እየሠሩ አንዳንዶቹም የገዳም ኑሮ ሲኖሩ ለነፍሳችን ይሆናል ብለው ለቤተ ክርስትያናቸው በኑዛዜ አበርክተዋል። በዚህ ሁኔታ ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጅምሮ ከነበረው የዴር
ሱልጣን ገዳም ሌላ በ 1850 ዓ.ም በአፄ ዮሐንስ ተጀምሮ በአፄ ምኒሊክ ግንባታው የተጠናቀቀው በእየሩሳሌም የደብረ ገነት መድኃኒዓለም ገዳም፣ ሌላ አምስት ገዳማትና እንዲሁም የሚከራዩ ህንፃዎች ባለቤት ሆነች።

እነኝህም ገዳማት ሦስተኛው በእየሩሳሌም በ 1883 ዓ.ም የተቆረቆረው የቅዱስ ፊልጶስ ነው። እንዲሁም በ1915 ዓ.ም ቅድስት ሥላሴ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ በእያሪኮ ከተማ፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ በ1920 ዓ.ም አሁንም በእያሪኮ፣ አልአዛር ገዳም በ 1945 ዓ.ም ፣ በቢታንያ ከተማ (አሁን የአዛውንት መነኮሳት መጦሪያ አጠገቡ ተሠርቷል)። እንዲሁም በ 1982 ዓ.ም ቤተልሔም ገዳም በቤተልሔም ከተማ ይገኛሉ። እንዲሁም ንግሥት ዘውዲቱ በእየሩሳሌም ያሠሩት የሚከራይና ገቢው ለቤተ ክርስቲያን የሚውል ታላቅ ሕንፃ አለ።

እነኝህ ገዳማት ያሠሩት ነገሥታትና ታዋቂ ባለሥልጣናት ለመጥቀስ ያህል የሚከተሉት አሉበት:: የዛሬ 170 ዓመት ገደማ አፄ ዮሐንስ ጉራዕ ላይ ደርቡሾችን በጦር አሸንፈው በማረኩት ስድስት ሳጥን ወርቅ የእየሩሳሌምን ደብረ ገነት መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያንን መሬቱን ገዝተው ሕንፃውን አስጀመሩ። ለዚህም የመሬት ግዥና ግንባታ በህብረተሰቡ የታወቁት ኢትዮጵያዊ አባ ወልደሰማዕት ወልደዮሐንስ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል (ሮቢን ትውቴ)። ከንጉሡ ሞት በኋላ አፄ ምኒሊክ 200,000 ማርያ ትሬዛ ገንዘብ እየሩሳሌም በሚገኝ ክሬዲት ዩኒየን ባንክ አስገብተው ወለዱ ለመነኮሳት መተዳደሪያ እንዲውል አዘዙ(ጳውሎስ ኞኞ )።

ቤትና መሬት በመግዛት ገቢው ለኢትዮጵያ ገዳማት መተዳደሪያ እንዲውል ያደረጉት ከዚህ የሚከተሉት ይገኙበታል። ንግሥት ጣይቱ፣ ንግሥት ዘውዲቱ፣ ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት ፣ አፈንጉሥ ነሲቡ መስቀሎና ባለቤታቸው ወ/ሮ ደስታ፣ ራስ ወልዴ አሻግሬ፣ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ፣ አፄ ኃይለሥላሴ፣ እቴጌ መነንና ወ/ሮ አማረች ዋለሉ ናቸው። በዚህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ገዳማትና ቤተ ክርስቲያናት በእየሩሳሌም ወይም በእስራኤል ግዛትና በፍልስጤም አስተዳደር ሥር ይገኛሉ።

በታሪክም የአካባቢው አስተዳዳሪዎች የኦቶማን መንግሥት (ቱርክ)፣ እንግሊዞች፣ ዮርዳኖስ መንግሥት፣ አሁን ደግሞ እስራኤልና በቤተልሔም ፍልስጤሞች የታሪክ አሻራቸውን በኢትዮጵያ ገዳማትና ቤተ ክርስቲያናት ላይ አኑረዋል። እንዲሁም የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች እንደ የሮማ ካቶሊክ ፣ የግብፅ ኮፕትና የአርመን ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ገዳማት፣ ቤተ ክርስቲያንና ይዞታ ላይ አዎንታዊና አሉታዊ የሆነ አስተዋፅኦ ወይም ድርጊት ፈፅመዋል። ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው እነኝህ የሃይማኖት ተቋማት መጥፎ ትውስታ በመነኮሳትና በገዳማቷ ላይ አኑረዋል።

አሉታዊ ክስተቶች ከውጪ አካላት የተሰነዘሩ ብቻ አልነበሩም። በተለይ በመነኮሳቱ መሐከል የሚነሱ አለመግባባት አልፎ አልፎ የነበሩ ሲሆን በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ መረን የለቀቁ ንብረት ለመዝረፍ የተሰማሩና የጎሣ ፖለቲካ የሚያራምዱ ገዳማቱንና መነኮሳቱን መፈታተናቸው ይታወቃል። ሥፍራው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው የፖለቲካና የሥነ ምግባር ብልሹነት ነፀብራቅ ሆኗል ለማለትም ይቻላል። ይህን በተመለከት ተመልሼ እመጣበታለሁ። ለአሁኑ ግን ከታሪክ አኳያ መነኮሳቱንና ገዳማቱን የተፈታተኑትን ሁኔታዎች ልጠቁም። በእየሩሳሌም የኢትዮጵያን ገዳማትና መነኮሳትን የተፈታተኑ የታሪክ አሻራዎች የኢትዮጵያን ገዳማት በተለይም በታላቁ በዴር ሱልጣን ወይንም ጎሎጎታ በምትገኘው ገዳም በቅርሶቹና በመነኮሳት ላይ የተጋረጠው ችግር ከሁለት አቅጣጫ የመነጨ ነው። እነኝህም ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮች ናቸው።

፩ኛ) ውጫዊ ችግሮች
ይህ ገዳሙ ሆነ መነኮሳቱ ሊቆጣጠሩት የማይችሉ ከእነሱ አቅም ውጪ የሚመነጩ ችግሮች ሕልውናቸውን ተፈታትኖታል። ኢትዮጵያኖች በዚህ አካባቢ መኖር የጀመሩት፣ ቁጥራቸው ይብዛም ይነስም አንድ ሺህ ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት ነበር። ይዞታቸው ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው ንጉሥ ሰሎሞን ለንግሥት ሳባ የሰጣት ነበር። ይህ ይዞታ ኋላ ኢትዮጵያ የክርስትና ሃይማኖት ከተቀበለች በኋላ የገዳሙ ይዞታ ሆነ።

የይዞታውን ባለቤትነት በተመለከተ
እየሩሳሌም በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ሥር ስትወድቅ በ 636 ዓም ካሊፋ ዑመር ባወጣው አዋጅ መሠረት ክርስቲያኖች፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ ይዞታቸው እንዲረጋላቸው አወጀ። ኋላም መስቀለኞች (crussadors) እየሩሳሌምን ከ 1099 እስከ 1187 ዓ.ም ለ 88 ዓመታት ሲያስተዳድሩም ሆነ በኋላም የአሸናፊዋ የቱርክ መሪ ሳላዲን በ 1187 ዓ.ም ኢትዮጵያውያኖችና ሌሎች ክርስቲያኖች ይዞታቸውን ይዘው እንዲቆዩ አወጀ። ወደ አካባቢው ይመጡ የነበሩም አውሮፓውያን ከ 1614 ዓ.ም የዛሬ አራት መቶ ዓመት ጅምሮ እየሩሳሌም ስለአለው የኢትዮጵያ ገዳም ይፅፉ ነበር። በአጠቃላይ በዴር ሱልጣን ያለው የኢትዮጵያ ይዞታ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በላይ አስቆጥሯል ለማለት ይቻላል። ሆኖም ግን ጥቁር ሕዝብ ይህንን ይዞታ ይሁዲዎች፣ ክርስቲያኖች የእስልምና እምነት ተከታዮች በጠቅላላው የአብርሃም ልጆች እስከ አሁን የሚፋለሙባትን የሃይማኖቶች ዕምብርት ውስጥ ይዞታ መያዛቸው በብዙዎች ተቀባይነትን አላገኘም። ስለዚህ በህዳር 30 ቀን 1850 ዓ.ም ከተፃፈ ዘገባና ከሌሎችም የተገኘው መረጃ የሚከተሉትን ውጫዊ ተፅዕኖዎችን ያመለክታሉ።

፩ኛ) የኢትዮጵያ ቀሳውስት ለምን በራሳቸው ላይ ነጭ ጥምጥም ያደርጋሉ በማለት የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እንደሚሳለቁባቸው፣
፪ኛ) የአርመን ቀሳውስት እንደሚያስቸግሯቸው፣
፫ኛ) አንዳንድ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች አበሾች አንድ ቀን መካና መዲናን ያጠፏታል ብለው ስለሚያምኑ በዚህ የተነሳሳተ እምነት የተነሳ ኢትዮጵያውያኖችን በጠላትነት እንደፈረጇቸው፣
፬ኛ) በ 1838 ዓ.ም በተነሳው የተስቦ በሽታ ብዙ ኢትዮጵያውያን በገዳሙ ውስጥ ሞተዋል። ከሞት የተረፉት (አንድ ሴትና አንድ ወንድ ነው ይባላል) አርመኖች መጥፎ ምግብ ይመግቧቸው እንደነበር፣
፭ኛ) የአርመን ፓትርያርክም የሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የበላይ ጠባቂ ስለነበሩ ግብፆች ፓትርያርኩን በማስፈቀድ ቱርኮችን በመወትወት በሽታውን እናጥፋ በማለት የኢትዮጵያውያኖችን የሃይማኖት መፃሕፍት፣ ወረቀቶቻቸውንና በተለይም የኢትዮጵያ ይዞታ የተመዘገቡበትን ሰነዶችን አብረው በእሳት አጥፍተዋል። ይህንንም ቃጠሎ ያዘዘው የቱርክ የእየሩሳሌም ገዢ ኢብራህም ፓሻ ነበር። ይህ ሰው የአሁኑን ሶርያን፣ ሌባኖን፣ ዮርዳኖስን፣ ፍልስጤምና እስራኤልን ከ 1831 እስከ 1840 ዓ.ም ይገዛ ነበር እንደ አሁኑ በወሰን ሳይላአያዩና ነፃ መንግሥታት ባልነበሩበት ጊዜ የኢትዮጵያና የግብፅ መሻከርም ከ 1838 ዓ.ም የተስቦ በሽታና ከኢትዮጵያ ገዳም ቃጠሎ በኋላ
ነበር ለማለት ይቻላል። ከ 3 ዓመት በኋላም በ 1841 ዓ.ም የኢትዮጵያ መነኮሳት ወደ እየሩሳሌም መምጣት ጀመሩ።
፮ኛ) በዚህ ሁኔታ የኢትዮጵያውያን ገዳም ቁልፉ ተውስዶባቸው ቅዳሴ በየበዓሉ ዕለት እንዳያደርሱና በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ እንዲቀድሱ ይፈቀድላቸው ነበር። በዚህ ሁኔታ ለ400 ዓመታት የእኛ ይዞታ ነበር በማለት ቤተ ክርስቲያኑንም አርመኖች ተቆጣጠሩት።
፯ኛ) መነኮሳቱም መጠለያ እያጡ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ይንገላቱ ነበር። በኋላ ከአርመኖች ጋር በስምምነት ቤተ ክርስቲያኑን ለሁለት መጠቀም ጀመሩ።

፰ኛ) በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያኖች ይደበደቡ፣ ይጨቆኑና ወደ ቤተ ክርስቲያንም መግቢያው መንገድ ይዘጋባቸው ነበር።
፱ኛ) የኢትዮጵያ መነኮሳት ከይዞታቸው ሲፈናቀሉ ወንጀለኞች አርመኖችና ቱርኮች ብቻ አልነበሩም። ቀደም ብሎ በ 1770 ዓ.ም አካባቢ አንድ ግብፃዊ ኢብራህም ዘዋህሪ የሚባል 8 አገልጋዮችን አስከትሎ ኢትዮጵያውያኖችን ጥገኝነት ጠይቆ ተዳብሎ ይኖር ነበር። ይህ ሰው የተማረ ስለነበረ በቱርኮች ተቀጥሮ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ስለነበር ለቱርኮቹም ለአበሾች ተወካያቸው ነኝ ማለት ጀመረ። ቤቱንም እናድሳለን በማለት ኢትዮጵያውያኖችን ካስወጣ በኋላ እንዳይመለሱ አደረገ (አቡነ ፊልጶስ)። የኢትዮጵያውያኖች ዋናው ችግር አረብኛ ቋንቋ አለመቻላቸው ለከፋ ጥቃት ዳርጓቸዋል። ይህ ድክመት በአሁኑ ጊዜም እብራይስጥና አረብኛ ቋንቋ አለማወቃቸውና ለ 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የፖለቲካ ሁኔታ አለመዘጋጀታቸው ለከፋ ጥቃት ዳርጓቸዋል።
፲ኛ) በእየሩሳሌም የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብር ቆንሰላ አለመኖሩ ውስጣዊ ችግር ሆኖ ነበር። ስለዚህም መነኮሳቱም ሆኑ የኢትዮጵያ መሪዎች ጉዳዮቻቸውን ለማስፈፀም የፈረንሳይ፣ የጣልያንና የሩሲያን ቆንስላዎች ይጠቀሙ ነበር። ለምሳሌ ገንዘብ ከኢትዮጵያ የሚላከው በእነኝህ ቆንስላዎች በኩል ነበር።
በዚህ መሀከል መነኮሳት ለምሳሌ አንዳንዴ ከየት ቆንስላ የመጣ ምግብ እንቀበል አንቀበል የሚለውም አወዛጋቢ ነበር። እንዲሁም ብዙ መነኮሳት የኢጣሊያንን ፓስፖርት የያዙ ነበሩ። ስለዚህም በ1893 ዓ.ም የአቶማን ሹማምት ቅዋሜ አስምተው ነበር (ዳላቺንስ እና ለማር ፣ ገፅ 59)።
የገዳሙን ችግር በተመለከተ ለምሳሌ አባ ገብረማርያም የሚባሉ አለቃ ከገዥዎቹ ከቱርክ ጋር በነበረው ችግር የኢጣሊያን ቆንሰላ ጣልቃ እንዲገባ የጠየቁት በ 1875 እና በ 1880 ዓ.ም የተፃፉት ደብዳቤዎች ነበሩ (ዳላቺንስ እና ለማር ፣ ገፅ 63)።

እንዲሁም ራስ መኮንን እየሩሳሌም ሄደው ቤትና ንብረት እንዲገዛላቸው በእቴጌ ጣይቱ ታዘው ነበር። ነገር ግን ራስ መኮንን የእየሩሳሌም ነዋሪ ስላልነበሩና ሕጉም ስለማይፈቅድ በኢጣሊያን ቆንስላ አማካኝነት የመሬት ግዢው ተፈፀመ፣ የቤት ህንፃው ግንባታም በቆንስላው ተከታታይነት አሁን ያለው ህንፃ ተጠናቀቀ (ዳላቺንስ እና ለማር ፣ ገፅ 69 – 70)። የህንፃውን ሥራ በትጋት የሚከታተለውም ሰው ሴራፊን ስለሞተ ባለቤቱ በጠየቀችው መሠረት በአባ ማህፀንተ በኩል ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ተዋጥቶ ገንዘብ ታገኝ ነበር። በዚህ ዓይነቱ ህብረተሰቡ በእየሩሳሌም በሶሻልና በምጣኔ ሀብት፣ ለምሳሌ ሥራ በመፍጠርና በመሸመት በመሳሰሉ አስተዋፅኦ አድርጓል። ይህም አዎንታዊ ገፅታው ነበር።
ë 6ኛ) በመጨረሻ የግብፆችን ተንኮል የሚያመለክተው በ 2017 ዓ.ም በዴር ሱልጣን የሚገኘውን የኢትዮጵያ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ግሪኮች ከጎኑ ያለውን ይዞታቸውን በኢትዮጵያ ፓትርያርክ የግል ፈቃድ ሲያድሱ ጉዳት ደረሰበት። ይህም የፈቃድ አሰጣጥ ሁኔታ ግልፅነት የጎደለው ስለሆነም ከበስተጀርባው የ “እከክልኝ ልከክልህ” ግላዊ ጥቅም ልውውጥ ሳይኖር አይቀርም የሚለው መነጋገሪያ ነበር። ቤተ ክርስቲያኑ የዴር ሱልጣን ጎሎጎታ አካል ሲሆን የግብፅ ኮፕቶች አሁንም የእኛ ነው የሚሉት ይህ ቤተ ክርስትያን በዕድሜ ምክንያት ሊፈርስ ይችላል ተብሎ ይሰጋ ነበር። ኢትዮጵያ ገዳሙንም ልትጠግነው አልቻለችም። ምክንያቱም ኮፕቶችም የእኛ
ይዞታ ነው ስለሚሉ የዚህ የይገባኛል ወይም አወዛጋቢ የባለቤትነት ጥያቄ ሁኔታውን አወሳስቦታል። በአካባቢውም የኢትዮጵያ መነኮሳት ዋሻ የሚመስሉ ትንንሽ መጠለያ ውስጥ ሳይታደስ በሚያሳዝን ሁኔታ ተጠልለው ይኖራሉ። በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች በውጪ አካል በኢትዮጵያ መነኮሳትና ገዳማት ላይ የተፈፀሙና አሁንም የሚፈፀሙ ውጫዊ ችግሮች ናቸው።

የውጭ ችግር መዘዝ
ከላይ እንደተጠቀሰው የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ኮፕቶችም የእኛ ይዞታ ነው ስለሚሉና ሁሉም በያለበት በያዘው ይርጋ (status que) ሕግ ከዘመናት ጀምሮ የፀና ስልሆነ በሁለቱም መካከል ስምምነት ከሌለ ማንኛውም ወገን ለምሳሌ ቤት ሊያድስ አይችልም። ስለዚህም ሁኔታው ያሳሰበው የእስራኤል አገር ግዛት ሚኒስቴር ቀደም ብሎ በ 2014 ዓ.ም የመጠገኛ ገንዘብ ልስጥ ብሎ ነበር። ያም ተቀባይነት አላገኘም። ኋላ ግን ቤተ ክርስቲያኑ ከጣሪያው ላይ በግሪኮች ሥራ ምክንያት አደጋ ደረሰበት። በመስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም ጎሎጎታ ያለው ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አናቱ ተደረመሰ። ሁኔታውም ለሕይወት አስጊ በመሆኑ የእየሩሳሌም ማዘጋጃ ቤት ቤተ ክርስቲያኑ እንዲዘጋ አዘዘ። በወሩ ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም የፈረሰውን ለመጠገን ሠራተኞች ሲላኩ ኮፕቶቹ የእኛ ሀብት ስለሆነ እኛ
እንሠራዋለን በማለት ከፖሊስ ጋር ግጭት ተነስቶ አንድ የኮፕት ቄስ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋለ (ሐሬትዝ ጋዜጣ)። ይባስ ብሎ የኮፕት ፓትርያርክ ፅህፈት ቤት ይህ የማዘጋጃ ቤት ጥገና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ለመደገፍ ነው በማለት በአንባ አንቶኒዎስ የአቋም መግለጫ ወጣ። የግብፅም ኤምባሲ እርዳታ
እንዳልተለያቸው በመጥቀስ በግብፅና በዓለም በሞላ የሚገኙ ኮፕቶች ድጋፋቸው እንዳይለያቸውም ጥሪ አቅርበዋል (አንባ አንቶኒዎስ)። የግብፅ መንግሥት በእየሩሳሌም የኮፕት ገዳማት የበላይ ጠባቂ ስለሆነ በመንግሥት ስም ኤምባሲውም የተቃውሞ መግለጫ አውጥቷል።

በአንፃሩ ከአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት መውደቅ በኋላ በኢትዮጵያ የመጡት ሁለት መንግሥታት በእየሩሳሌም የአገራቸው ሀብትና ታሪክ ለማስጠበቅና ለመንከባከብ ብቁ ተሳትፎ አላደረጉም። ይባስ ብሎም የህዋህት ካድሬዎች ሌላ ቦታ (ኢትዮጵያ ውስጥና በውጭውም ዓለም ) እንደሚያደርጉት ሁሉ ካህናት መስለው በመሰግሰግ ገንዘብ ከመዝረፍና የጎሣ ፖለቲካ ከማራመድ አልፈው የንግሥት ዘውዲቱን ህንፃ የመንግሥት ነው በማለት ከኤምባሲው ጋር ተሰባጥረው ሊሸጡ ሲሯሯጡ ህንፃውን ንግሥቲቱ በኑዛዜያቸው ለእየሩሳሌም ገዳም የተወሰነ የኪራይ ገቢውን ስለአወረሱ እየሩሳሌም በሚገኙ ምዕመናን ብርታት ተርፏል ብለው አጫውተውኛል። እንዲሁም እንኝሁ አስመሳዮች ከባንክ ገንዘብ ሊያወጡ ሲሉም በባንክ ሠራተኞች ጥቆማ ገንዘቡ መትረፉንም እያዘኑ ነግረውኛል። እነኝሁ ሰዎች ይባስ ብለው በእኩይ
ተግባራቸው ምክንያት ከሥራ ያባረሯቸውን በእየሩሳሌም የኢትዮጵያን ጳጳስ አቡነ እባቆምን ሲመቱ ግርግር ፈጥረው በፖሊስ ተርፈዋል። እንደሚዝቱባቸውም አጫውተውኛል። የመኖሪያ ፈቃዳቸው በእስራኤል መንግሥት ቢታገድም ባልተለመደ መልኩ ለምን ተባረርን በማለትም ክስ መሥርተዋል።

ከውጭ የተቃጣውን ችግር ውስጥ ያሉት አንድ ላይ ቆመው መቋቋም ካልቻሉ ቀዳዳ እየፈጠሩ ለውጭው አካል ኃይል ይሆናሉ። እንደሚባለው አምስተኛ ረድፍ ( Fifth Column) መክፈት ማለት ይህ ተግባር ነው። በሌላ በኩል በጠቅላላው በሁኔታው የሚያዝኑ አንዳንድ የቤተ እስራኤል አባላትና ቀደም ብሎ ያጫወተኝ የኬኔሰት (ፓርላማ) አባል በኢትዮጵያዊነት ስሜትም ሆነ የኢህአድግን መንግሥት በመቃወም ይሆን በገዳሙ የሚፈጠረው ሁኔታ፣ በተለይ የገቢው ሁኔታ እንደሚያሳስበው በ 2009 ዓ.ም ነግሮኝ ነበር።

በመጨረሻ የውጫዊ ችግር ዋና መነሻና መዘዝ በግብፆች አባባል ጎሎጎታ ወይም ዴር ሱልጣን በሱልጣን አብድ አልማሊክ ኢብን ማርዋን (ከ 684 እስከ 705 ዓም ይገዛ የነበረው) ለኮፕቶች ይዞታውን ሰጥቶናል ብለው ይከራከራሉ። ዴር ሱልጣን የሚባለው አሁን አወዛጋቢ ስፍራ ስም ያገኘው ወይም የተሰየመው በዚህ ሰው ሲሆን ሶርያንና ግብፅንም ይገዛ ነበር። እንደ ግብፆች አቀራረብ በጊዜው ለይዞታቸው ኢትዮጵያውያን ግብር መክፈል ባለመቻላቸው ግሪኮችና አርመኖች በ1654 ዓ.ም ግብር ከፍለው ቦታውን ተረከቡት። ግብፆች ግን በዚያን ወቅት ለኢትዮጵያ መጠለያ ሰጠናቸው ብለው ይከራከራሉ። ይህ ሁኔታ በዚህ እያለ በ April 25 ቀን 1970 ዓ.ም በዋለ የፋሲካ ምሽት የእስራኤል መንግሥት ወታደር በመላክ የመግቢያውን ቁልፍ በመለወጥ ቁልፉን ለኢትዮጵያውያን ሰጡብን ይላሉ። የኮፕት ቀሳውስት ሁኔታውን ሰምተው ተሯሩጠው ሲደርሱ የእስራኤል ፖሊሶች እንዳይገቡ አገዷቸው ብለው ግብፆች ይሟገታሉ (Al -Musry Al -Youm)። ለማስታወስ ያህል ወቅቱ በአረቦችና በእስራኤል መካከል የተደረገው የጥቅምት ወር ጦርነት ወይም ሃያ ቀናት የወሰደ የዬም ኪፑር ጦርነት (1973 ዓ.ም) ዋዜማ ነበር። ግብፅም ይህንን በፕሬዘዳንት አንዋር ሳዳት መሪነት በእስራኤል ላይ ያቀነባበረችው ጦርነት ነበር። የግብፅን ክርክር በተመለከተ ከኢትዮጵያ በኩል የተሰጠው መልስ በቅርቡ November 2018 ዓ.ም የወጣው መግልጫ ነበር። የዚህ መግለጫ ይዘት ይህ ነው። “ኮፕቶቹ ህገ ወጥ ሁኔታዎችን በመጠቀም፣ የተጭበረበረ ሰንድ በማቅረብና ለዘመናት የነበረውን የታሪክ አሻራ ለማጥፋት እየሰሩ ነው” ይላል (አህራም ኦንላይን)። መግለጫው ከሃይማኖታዊ አስተምህሮና ሰነዶች ባሻግር የኢትዮጵያ ይዞታ በታክስ ሰነዶችና የተለያዩ የእየሩሳሌም አስተዳዳሪዎች ያወጡት አዋጆች ዋቢ ናቸው በማለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ
ቤተ ክርስቲያን የኮፕቶችን እርምጃ ኮንናለች።

፪ኛ ) ውስጣዊ ችግሮች ከላይ የተጠቀሱት ከውጭ የተነጣጠሩ ችግሮችና ሁኔታዎች የኢትዮጵያን ካህናትና ይዞታ እጅጉን ጎድቷቸዋል። አሁንም እየጎዳቸው ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የማይተናነስ የውስጥ ችግሮች መኖራቸውን ማመንና መፍትሔም መፈለግ ተገቢ ነው።

፩ኛ) እነኝህ ውስጣዊ ችግሮች በተለይ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ገደማ በኢህአድግ ዘመን መረን የለቀቁና ሃይማኖቱንም ሆነ አገራዊ ሕልውናዋን የሚፈታተኑ ሆነው ታይተዋል። ሆኖም ግን የክፋቱ መጠንና የአደጋው ሁኔታ ይለያይ እንጂ በእየሩሳሌም ገዳም በካህናቱ ውስጥም ችግሮች እንደነበሩ ይነገራል። ነገር ግን ከአሁኑ ሁኔታ በተለየ መልኩ የኢትዮጵያ መንግሥታት ችግሮችን የሚቆሰቁሱና ቅራኔን የሚያሰፋ አልነበሩም። ለምሳሌ ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ በገዳሙ ውስጥ የነበሩ መነኮሳት አደብ እንዲገዙና ዳዊታቸውን እየደገሙ ለአገራቸው እንዲፀልዩ ያዙ ነበር። ለዚህ ሁሉ ገዳማዊ ኑሮ በእሳቸው ትዕዛዝ ለሚበሉትና ለሚለብሱት ገንዘብ ተቆራጭ ሆኖላቸው ነበር። ለምሳሌ (ግንቦት 20 ቀን 1898 ዓ.ም የተፃፈ ደብዳቤ ጳውሎስ ኞኞ እንደዘገበው እንዲህ ያላል።

ይድረስ እየሩሳሌም ካሉ ማኅበረ ኢትዮጵያ እኛ ለእናንተ አገራችሁን ትታችሁ ስለፅድቅ ብላችሁ ሄዳችኋል ብለን በእረፍትና በሰላም እንድትኖሩ እጅግ እንደክማለን። እናንተ ግን ሁልጊዜ ጠብና ክርክር ነው የምትወዱት። ሳታርሱ፣ ሳትነግዱ፣ የምትበሉትን፣ ሰጥተን አርፋችሁ ዳዊት ብትደግሙ አይሻልምን። አሁንም ስለመድኃኒዓለም ብላችሁ በፍቅር ተስማምታችሁ እንድትኖሩ እንለምናችኋለን። ክርክር እያደረጋችሁ እኛን ይታክተናል። ከሰው ባይስማማ ወይም አገሩ ናፍቆት እዚያ መቀመጥ
የማይችል ወደዚህ ልምጣ የሚል ሰው ግን ወደኛ ይምጣ። እኛም በደህና አድርገን እንቀበለዋለን።

ደግሞ በእየሩስለም የተሾመው መምህሩም፣ መጋቢውም፣ ማኅበሩም ቢሆን ያለኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ ቦታም ቤትም መሸጥ፣ ያንንም አስይዞ ገንዘብ መበደረም፣ ሌላም ቦታ ገዝቼ ቤት እሠራለሁ ማለት አይቻለውም። አልተፈቀደለትም። ይህ ወረቀት ለዘላለም ምስክር የሚሆን ነውና አይጥፋባችሁ።
ጳውሎስ ኞኞ ገፅ 237 – 238

፪ኛ) ሌላው ችግር እንደአሁኑ በጣም የከፋና መረን የለቀቀ ፍቅረ ነዋይ ባይኖርም በእየሩሳሌም ከሚሾሙት ውስጥ የገዳሙን ሀብት ለግላቸው ሊያደርጉ የሚፈልጉ ይኖሩ እንደነበሩም ይነገራል። ይህንን በተመለከተ አፄ ምኒሊክ ለእየሩሳሌም ከተማ አስተዳዳሪ ግንቦት 19 ቀን 1898 ዓ.ም የፃፉት እንዲህ ይል ነበር። የአፈ ንጉሥ ነሲቡ ቤት የባለቤትነት ስም ያለአግባብ ተፍቆ በገዳሙ አስተዳዳሪ በመምህር ፈቃደ ስም ከተፃፈ ያ ተቀይሮ በዋናው ባለቤት በአፈንጉሥ ነሲቡ ስም እንዲስተካከል። የሚል ደብዳቤ ነው።

ጳውሎስ ኞኞ ገፅ 236
እኝህ በዴር ሱልጣን የተሾሙት መምህር ፈቃደ አስቸጋሪ ግለሰብ እንደነበሩም አፄ ምንሊክ ለእየሩሳሌም ገዥም እንዲሁ ግንቦት 19 ቀን 1899 ዓ.ም በፃፉት ደብዳቤ በእስታቡል እና በእየሩሳሌም “ክፉ ነገር በመስራት ተፈርዶበት ነበር” ቢሉም ክፋቱ ምን እንደነበር አልገለፁም። አከታትለውም በእየሩሳሌም የሚሾም መምህርም ሆነ መጋቢውና ማህበሩ በጠቅላላ ያለ ኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ ቤትና ቦታ መሸጥ፣ ይህንንም አስይዞ ገንዘብ መበደር፣ አዲስ ቤትም ማሠራት አይቻልም ብለው ለከተማዋ ሹም ደብዳቤ ፅፈው ነበር የላኩት (ጳውሎስ ኞኞ ገፅ 237)። አፄ ምኒሊክ እንደገና የስርቆትን ነገር አስመልክተው የሚከተለውን ደብዳቤ ፅፈው ነበር።
ይድረስ ከእየሩሳሌም ባሻ፣ ሰላም ላንተ ይሁን። በእየሩሳሌም ቅጥር ውስጥ በኔ፣ በዳግማዊ ምኒልክ ስም የተገዛ ቤትና ደብሮች፣ ከእየሩሳሌም ቅጥር ውጪ፣ እቴጌ ጣይቱ በ ë 43 ዓ.ም ያሠራችውን ትልቁን ቤት ማኅተሟ ያለበት፣ 2ኛ ካጠገቡ ከሸመአን ይሁዲ የገዛቸው ቤት፣ ከደብረ ገነትም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በ ë 4 ዓ.ም
በእቴጌ ጣይቱ ስም የተሠሩት ሁለቱ ቤቶች፣ የአፈንጉሥ ነሲቡ ቤት፣ ራስ ወልዴም የገዙት ቤት፣ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያኖቹም፣ እንዚህ ሁሉ ቤቶች ያለ ኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ መነኮሳትም ቢሆኑ፣ ራይሱም ቢሆን፣ ማንም ቢሆን እንዳይሸጥና መያዣ አድርጎ ገንዘብ እንዳይበደር ይህ በመንግሥታችሁ መዝገብ እንዲፃፍልን ይሁን። ከዚህ ቀደም የዴር ሱልጣን ነገር አስቸግሮን እጅግ አልፍቶናልና ስለዚህም እንለምንሃለን።”
መጋቢት 2 ቀን ë 4 ዓ.ም
ከጳውሎስ ኞኞ ገፅ 253
እንግዲህ ሌብነት በአሁኑ ጊዜ ከሚከሰተው ባይብስም ይህ ውስጣዊ በሽታ ገዳሙን ተፈታትኖት ነበር። ይህ ገዳም አሁንም ቢሆን በጣም በተቀነባበረና በረቀቀ መንገድ የሚካሄደው ሙስና፣ ጎሰኝነትና አድሎአዊነት አገሪቷንና የሃይማኖት ተቋማትን በአገር ውስጥና በውጭው አገር ክፉኛ እየተፈታተነ ነው። የመንፈሳዊ ኑሮንም የሚፈታተን ሁኔታ ተከስቷል። ለምሳሌ እየሩስሌም ለመጀመሪያ በ 2009 ዓ.ም የሄድኩ ጊዜ ይህንን ሁኔታ ታዝቤአለሁ። ይሄውም መነኮሳትም “የመንግሥት ሰው” የሚሏት ወጣት “መነኩሴ” ቤተ ክርስቲያኑን አምሳ በፖሊስ ኃይል ከገዳሙ ተባራ ነበር። ይህም በእየሩሳሌም ጋዜጦች እንደ ዜና ወጥቶ ነበር። አንዳንድ ካህናትም በተለይ በውጭ አገር ሥልጣነ ክህነታቸውን የንዋይ ምንጭ አድርገውታል። ሥርዓቱም ተፋልሷል። ለምሳሌ ሰባኪ፣ ካህናትና ዲያቆናት እየመሰሉ አምስተኛ ረድፈኞች
በዋልድባ ገዳማት በመሳሰሉና እንዲሁም በአሜሪካንና በሌላ አገራት በሌላቸው ትምሀርት ቤተ ክርስቲያናትን የሚያምሱ፣ የሚገነባውን አፍርሰው አፈር የሚያለብሱ እንደተባለው “የመንግሥት ሰዎች” ከተባባሪዎቻቸው ጋር ቤተ ክርስትያናትን አዋርደዋል። ይህንን ቤተክርስቲያን ካላፀዳች ሕልውናዋ አደጋ ላይ ይሆናል። የወንበዴዎች ዋሻ ከሆነች መሳለቂያም ትሆናለች።

ይህ ሁኔታ፣ በተለይ በእየሩሳሌም ገዳማት ውስጥ ብዙ ገንዘብና ንብረት ስለአለ መነኮሳት መስለው ሀብቷን ሊዘርፉ የተሰማሩ እንዳሉ አይተናል። በእየሩሳሌም ንብረቷን ዘብ ሆነው የሚጠብቁ ምዕመናን መሆናቸውም ይታወቃል። በመጨረሻም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰት የፖለቲካ ቀውስ ለዘመናት በእየሩሳሌም መነኮሳትም ላይ
ክፉኛ ተፅዕኖ አሳድሯል። ለምሳሌ በኢጣሊያን ወረራ ፣ በአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት ውድቀት በኋላም በወታደራዊው መንግሥትና ከሱም በኋላ ጎሣ ተኮር በሆነው በኢህአድግ መንግሥት ጊዜ በሥራዓቶቹ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች መካከል መነኮሳቱ ታምሰዋል። እንደታዘብኩት ከሆነ ጳጳሱን ለመደብደብ ከተቃጣው ሁኔታ በኋላ መነኮሳቱ ለመናገር እንኳን አካባቢያቸውን በዓይናቸው ቃኝተው ነው። አንድ ለአምስት የተባለውን የኢህአዴግ የስለላ መረብን ያስታውሰናል። ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ኢ-ሰብአዊ ሁኔታ ነፀብራቅ ነው ማለት ነው። ይህም አንዱ መርዘኛ የውስጣዊ ችግር መንስኤ ነው።

ምክረ ሀሳቦች በእየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳም ታሪኩና የተጋረጡበት ችግሮች ጠቅለል ባለ መልኩ ለማስረዳት ሞክሬአለሁ። አሁን ደግሞ ለችግሮቹ መፍትሄ ይሆናሉ የምላቸውን ምክረ ሀሳብ ልጠቁም። ይህም እየሩሳሌም ሦስት ጊዜ ሄጄ ካየሁት የመነጨ ነው። የመጀመሪያ ጊዜ በግሌ( 2009 ዓ.ም)፣ ሁለተኛ ጊዜ በአሜሪካ ብሔራዊ የይሁዲዎች ተቋም ግብዣ (2017 ዓ.ም) ሲሆን ሦስተኛው ቴልአቪቭ ዩኒቨርስቲ የታዋቂው ፉልብራይት አንጋፋ መምህር ሆኜ (2018 ዓ.ም) አስተምሬ ነበር።
፩ኛ) መነኮሳቱ ከሃይማኖት ትምህርትና ሥልጠና ጎን የቋንቋ ትምህርት (በተለይ ዕብራይስጥና አረብኛ) ለመግባቢያ ያህል ቢሰጣቸው አስፈላጊ ይመስለኛል።

፪ኛ) መነኮሳቱ አንዳንድ የቴክኒክ ሥልጠና ቢሰጣቸው የገዳሙን ንብረት በእንክብካቤ ይይዛሉ። ከዚህም ጎን ሌሎቹ እንደሚያደርጉት በእጅ ሥራና በጥበብ ሙያ ሠልጥነው የሥራ ውጤታቸውን ለገበያ ቢያቀርቡ ለጤናቸውም ጠቃሚ ነው የገቢ ምንጭም ለገዳሙ ይሆናል።

፫ኛ) የገዳሙ ጳጳስ ጽሕፈት ቤት በእየሩሳሌም ከፍተኛ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ በማድረግ ተሰሚነትን እንደ ኮፕቶች ማግኘት ይቻላል። በጋዜጣ፣ በመፅሄትና በብዙኃን መገናኛ ገዳሙን ማስተዋወቅ አጋር ያስገኛል። ለዚህ ሁሉ የተማሩና ልዩ ክህሎት ያላቸውን የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን መቅጠርን ይጠይቃል።

፬ኛ) በእየሩሳሌም ካሉት ትውልደ ኢትዮጵያ ቤተ እስራኤሎች ጋር በቅርብ መገናኘትና መወያየት አስፈላጊ ነው። በከኔሰት (ፓርላማ) ያሉትንም ማቅረብና አጋዥ እንዲሆኑ ማድረግ ተገቢ ነው።

፭ኛ) በእየሩሳሌም የሚገኛው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የገዳሙን ደህንነትና አንድነት (በአስተዳደር ጣልቃ ሳይገባ) ማጠናከርና ከግብፅና ከሌላ የሚመጣውን ግፊት በዲፕሎማሲ መመከትና የኢትዮጵያን ጥቅም ማስከበር ይኖርበታል። እስከአሁን የነበረው ማተራመስ ይቆማል ብለን ተስፋ እናደርጋልን። በተለይ በቅርቡ በእስራእኤል የተሾሙት አምባሳደር አዲስ ተስፋ አጭረዋል። ይህም ይቀጥላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

፮ኛ) በእየሩሳሌምና በዓለም በሞላ የሚገኙ ምዕመናን የገዳሙን ህልውና የመጠበቅ ታሪካዊ ግዴታ አለባቸው። በእየሩሳሌም በጥናቴ እንዳየሁት ከሆነ ለሃይማኖታቸው ቀናኢ አስተሳሰብ ያላቸው ለአገራቸው ታሪክና ሕዝብ መብት የቆሙ ዜጎች መኖራቸው ተስፋ ይሰጣል። እንዲሁም የትውልድ አገራቸው ፍቅርና ስሜት ያላቸው ቤተ እስራኤሎች አንዳንድ ወጣቶች የኢትዮጵያን ታሪክ እየተረዱ የእዚያ የባለታሪክ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ነን እያሉ ዘረኝነትንም ለመቋቋም መፍትሔ እያገኙለት እንዳሉና ሊረዱም እንደሚፈልጉ ከጥናቴ አኳያ መረዳቴ ሌላው ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ነው። ከታሪክ አኳያም በመነሳት ከገዳሙ ጎን የሚቆሙ ቀና የሆኑ እስራኤላውያን እንዳሉና የዲፕሎማሲ ሥራ ቢሠራ ብዙ ጥቅም ሊገኝ እንደሚችል ተገንዝቤአለሁ። ስለዚህ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንም በውስጧ የተከሰቱትን አሉታዊ ሁኔታዎች በአግባቡ አስወግዳ ለ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሚመጥን ብቃትና ጥራት ያላቸውን መሪዎች ማሰለፍ ይጠበቅባታል። ያለበለዚያ በእየሩሳሌም ያሉት ገዳማት ከውጭም ከውስጥም በተነሱና በሚነሱ አፍራሽ ኃይሎች የበለጠ ልትጎዳ ትችላለች። ሕልውናዋም አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል።

፯ኛ) የገዳሙን ታሪክ የያዙ ሰነዶች በጥንቃቄ በአዲሱ ቴክኖሎግጂ ታግዘው መያዝ አለባቸው። ለዚህም አዲስ የሚሰራው ህንፃ ታላቅ እገዛ ያድርጋል፣ በዓለም በሞላ የሚገኙትን ተመራማሪዎችንም እንዲረዳ ማድረግ ወሳኝ ነው።

፰ኛ) በመጨረሻ በእየሩሳሌም ቴዎፍሎስ ሳልሳዊ፣ የግሪክ ፓትርያርክና እንዲሁም በዚሁ በእየሩሳሌም ኑርሃን ማኑኒያን፣ የአርመን ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ የሆኑት በኢትዮጵያና በግብፅ ቤተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታትና ለማስታረቅ ሞክረው ሳይሳካ ቀርቷል። የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ከአገሩ ኮፕቶች ጎን ቆሞ ነበር። የኢትዮጵያም ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የዲፕሎማሲ ኃይሏን አጠናክራ፣ ከገዳሙ ጎን ቆማ፣ ደጋፊዎቿን አበራክታና ሁሉን የሚያሳምን መረጃዎቿን አቅርባ ለውይይት ወደ ኋላ ማለት የለባትም።

መደምደሚያ
በእየሩሳሌም በሚገኘው በዴር ሱልጣን ወይም በጎሎጎታ ያለው የኢትዮጵያ ገዳምና ቤተ ክርስቲያናት ጠቅላላ ሁኔታ ይህን ይመስላል። ይህን የኢትዮጵያ ይዞታ ለማስከበር የኢትዮጵያ ቤተ ክህነት፣ እንዲሁም ለዘመናት እራሷን የምታስተዳድረው ገዳም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ካህናትና በተለይ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በሃይማኖት ሳይለያይ በጥናት በተደገፈ መከራከሪያ ፣ በተለይም ሁሉን አሳማኝ የሆነ ሰነድ ማቅረብ የሚጠበቅ ነው። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም መጀመሪያ እራሷን መመርመርና ተቋሟን አሻሽላ፣ ቤቷን አፅድታ ለሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ውስብስብ ሁኔታዎች መዘጋጀት አለባት።

የውጭውን ችግር ለመመከት ውስጣዊ ጥራትና ጥንካሬ ላይ ማተኮር ለሃይማኖት አባቶች ብቻ ሳይሆን ለፖለቲካ መሪዎችም ዓይነተኛ መመሪያ መሆን አለበት። የኋላ ኋላ “ጠላታችንን አፈላልገን አገኘነው፣ ጠላታችን እኛው ሆነን ተገኘን” ካልን ብዙ ርቀት ወደ ኋላ ቀርተናል ማለት ነው። ልበ እውራን የሆኑ የዛሬን ብቻ ያያሉ። ልበ ብርሃኖች ግን የወደፊቱን ትውልድ አሻግረው ያስተውላሉ። ይህ የዛሬ ጽሁፌ ይህን ያመለከተ ይመስለኛል።ስለተሰጠኝ ዕድል አመሰግናለሁ። እግዚአብሔር ይስጥልኝ።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com