ቅዱስ ሲኖዶስ እነ ቀሲስ በላይን ገሰጸ

Views: 127

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ እነ ቀሲስ በላይ መኮንን ‹‹የኦሮሞ ቤተክህነት ጽ/ቤት››ን ነጥለን እናቋቁማለን ብለው የጀመሩት አደረጃጀት በሲኖዶስ ሕጋዊ እውቅና የሌለው መሆኑን አስታወቀ፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ ጳጉሜ 2 ቀን 2011 ዓ.ም ባወጣው መግለጫው እንደገለጸው ቤተክርስቲያኗ እስካሁን ድረስ ባህልን፤ ቀለምን፤ ቋንቋንና ብሔርን መሠረት ሳታደርግ በተቻላት አቅም መንፈሳዊ እና ሀዋሪያዊ አገልግሎቷን ተደራሽ ለማድረግ ስትሰራ እንደኖረች ይታወቃል፡፡

ቤተክርስቲያኗ ለኦሮሞ ማኅበረሰብ የመንፈስ ቅዱስ ልጆች እንዲረዳ የጸሎት፤ የሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ እና ሀይማኖታዊ የትምህርት መጽሐፍትን በኦሮምኛ ቋንቋ በመተርጎም እና በማዘጋጀት፣ ከአምስት በላይ የካህናት ማሰልጠኛ ተቋማትን፣ አንድ ከፍተኛ መንፈሳዊ ኮሌጅን በጀት መድባ በማቋቋም መላውን የኦሮሞ ብሔር ህዝበ ክርስቲያን ስታገለግል እንደቆየች ተገልጿል፡፡

እነ ቀሲስ በላይ፣ የኦሮሚያ ቤተክህነት ጽ/ቤት በሚል በራሳቸው ሥልጣን መስርተው በመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት ግለሰቦች፣ ቅዱስ ሲኖዶሱን በአካል ቀርበው የተወያዩ ሲሆን፣ በውይይቱም ወቅት ከቅዱስ ሲኖዶሱ ፍቃድና እውቅና ውጪ አዲስ መዋቅር ፈጥረው መግለጫ መስጠታቸው አላግባብ መሆኑን አምነው ይቅርታ ለመጠየቅ ተስማምተው እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡

ለዛሬ ጳጉሜ 2 ቀን 2011 ዓ.ም ይቅርታ ለመጠየቅ የተቀጠሩት የኮሚቴው ዋና ተጠሪ ቀሲስ በላይ መኮንን (ሊቀአእላፍ) እና አባላቶቻቸው ያልተገኙ ሲሆን፣ ሁለት የኮሚቴው አባላት ብቻ ከተሰጣቸው ሰዓት አሳልፈው በመምጣት በጽሑፍ ባቀረቡት ምላሽ መሠረት በሕገወጥ አቋማቸው የፀኑ መሆናቸውን ገለፀዋል፡፡

ይህ በግለሰቦቹ የኦሮሞ ቤተክህነት ጽ/ቤት ተብሎ የተጠቀሰው አደረጃጀት ሕጋዊ እውቅና የሌለው መሆኑን ሁላችሁም የመንፈስ ቅዱስ ልጆች አውቃችሁ የግለሰቦቹን ሕገወጥ እንቅስቃሴ በመቃወምና በቀደመው አንድነታችሁ ጸንታችሁ ቤተክርስቲያናችሁንና ሀይማኖታችሁን ጠብቁ ሲል ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com