ከሁለት ቀናት ፍለጋ በኋላ ከሆስፒታል የተሰረቀችው ህፃን ተገኘች

Views: 114

ከጋምቤላ ሆስፒታል የተሰረቀች የአንድ ቀን ተኩል ዕድሜ ያላት ህፃን ከሁለት ቀናት ክትትል በኋላ ከነሙሉ ጤንነቷ ተገኘች ።

በጋምቤላ ሆስፒታል ነሀሴ 28 ቀን 2011 ዓም አንዲት ህፃን በሰላም ወደ ዓለማችን ተቀላቅላለች ሲሉ የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኡቲያንግ ኡቻን ገልጸዋል ።

ከምጥ ጋር ታግላ ጤናማ ህፃን በሰላም የተገላገለችው እናት ድካሙ አልለቀቃትም ነበርና በማግስቱ አገር አማን ነው ብላ ጨቅላዋን አጠገቧ እንዳስቀመጠች እንቅልፍ ሸለብ አድርጓት ነበርም ብለዋል ።
ከእንቅልፏ ስትነሳ ግን የአንድ ቀን ተኩል እድሜ ያላት የአብራኳን ክፋይ እንዳስቀመጠቻት ከጎኗ የለችም ።

እናትም በድንጋጤ ተውጣ የድረሱልኝ ጥሪ በማሰማቷ የሆስፒታሉ ማህበረሰብ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ስለ ጉዳዩ ማውረድ ማውጣት ይጀምራል ።

የክልሉ ፖሊስም ነሀሴ 29 ቀን 2011 ዓም ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ ጠፋች የተባለችውን ጨቅላ ህፃን ለማግኘት ፍለጋውን ይጀምራል ።

የክልሉ ፖሊስ ከሆስፒታሉ ባገኘው የመነሻ ሃሳብ መሰረት በማድረግ ለሁለት ቀናት ባካሄደው ክትትል ህፃኗ በጋምቤላ ከተማ ቀበሌ 01 ተደብቃ ትናንት ከቀኑ 8 ሰዓት አካባቢ በአንድ ግለሰብ ቤት መገኘቷ ተሰምቷል።

ኮሚሽነር ኡቲያንግ እንደገለፁት ከሆነም ህፃኗ ከነሙሉ ጤንነትዋ የተገኘች ሲሆን ፖሊስ ለወላጅ እናቷ አስረክባቷል ።

ጨቅላዋን ሰርቃ ተሰውራለች የተባለችው ተጠርጣሪም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላ በምርመራ ላይ የምትገኝ ሲሆን የምርመራ መዘገቡ እንደተጠናቀቀ ተጠርጣሪዋ ለህግ እንደምትቀርብም ኮሚሽነሩ አስታውዋል::

አስገራሚው ነገር ግን እውነተኛዋ አራስም ሆነች በጨቅላ ህፃን ስርቆት ተጠርጥራ በቁጥጥር ስር የዋለችው ግለሰብ ከሁለት የተለያዩ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች የመጡ መሆናቸው ተብሏል ።

ለምን እንደመጣችና ህፃኗን ለምን መስረቅ እንደፈለገች በምርመራው የሚታወቅ ይሆናል ተብሏል ።

ዘገባው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com