የትምህርት ሥርዓቱ እድል ነፋጊ፤ የትምህርት ሚንስትር ውሳኔ ደግሞ አግላይ ነው ተባለ

Views: 157

ትምህርት ሚንስትር የ12ኛ ክፍል መልቀቂያና የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ውጤት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለማረም የወሰደው መፍትሄ፣ ተማሪዎችን ማዕከል ያላደረገ አግላይ ነው ሲሉ የትምህርት ባለሟሎች በጉባዔ ላይ ገለጹ፡፡

ትምህርት ሚ/ር ተማሪዎቹን ለመመዘን ሂሳብ፣ እንግሊዝኛ፣ ፊዚክስ፣ አፕቲትዩድ እና ጂኦግራፊ የትምህርት ዓነቶችን ብቻ መምረጡ የበርካታ ተማሪዎችን እድል የሚዘጋ ነው ሲሉ ነው ለዘጋቢያችን የገለጹት፡፡

‹‹ውሳኔው ልክ አይደለም፤ መጀመሪያውኑ ልጆቹ እንዲማሩ የሚደረገው ትምህርት ውስንና የጠበበ ነው›› የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የድህረ ምረቃ የካሪኩለም ትምህርት መምህር ዶ/ር ሰለሞን በላይ፣ በተማሪዎቹ ሥህተት ባልተፈጠረ የውጤት ‹‹ግሽበት›› ዩኒቨርስቲ ለመግበታ በአራት የትምህርት ውጤት ብቻ ልዳኛችሁ ማለት እድል መንፈግና መጨቆን ነው ብለዋል፡፡

ልጆች በተፈጥሯቸው ባለ ብዙ ተሰጥዖ ናቸው የሚሉት ዶ/ር ሰለሞን፣ ሥርዓተ ትምህርቱ ግን በቋንቋና በሂሳብ ዘርፎች ብቻ ለሁለት ተከፍሎ ገድቧቸዋል ብለዋል፡፡

እንደ ሀገር የልጆችን ብዝሃ-ተሰጥዖ የምንጠቀምበት የትምህርት ሥርዓት መዘርጋት ሲገባን፤ እስከ አሁን ውስን የቀለም ትምህርት ላይ ብቻ ተጣብቀናል፤ የባዮሎጂ፣ የኬሚስትሪ፣ የስፖርት፣ የሙዚቃ፣ የፈጠራ ችሎታ ያላቸውን ልጆች እያገለልክ  ደግሞ ሀገርህን ልታሳድግ አትችልም ብለዋል ደ/ር ሰለሞን በላይ፡፡

‹‹ተማሪዎችን ሰባት የትምህርት ዓይነት አስተምረህ፣ በአራቱ ብቻ ስትዳኛቸው፣ በአንድ በኩል የተወሰነ ተሰጥዖ ላላቸው ብቻ እድል እየሰጠህ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለሌሎች እድል እየነፈግክ መሆኑ መታወቅ አለበት የሚሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ዓለሙ ተስፋዬ ናቸው፡፡

መምህር ዓለሙ ችግሩ መፈታት የነበረበት ችግሩን በፈጠሩት አካላት የእርምትና የቅጣት እርምጃ እንጂ በተማሪዎች ኪሳራ መሆን አልነበረበትም ሲሉ ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ላይ ለፈተና መሰረቁ  ‹‹ለውጤት መጋሸቡ››  ምክንያት የሆኑትን ሰዎች መቅጣትና እርምጃ መውሰድ ሲገባ፣ አድበስብሶ ማለፉ ለሥርዓተ ትምህርቱ አይጠቅምም፤ ለመንግሥትም አይበጅም ብለዋል፡፡

እንዲህ አይነት ድርጊት በኢትዮጵያ የትምህርት ታሪክ መታየት ከጀመረ ሁለት አሥር ዓመታት አልፈውታል የሚሉት መምህር ዓለሙ፤ በዩኒቨርስቲም ስናስተምር የአንድ አካባቢ ሰዎች በብዛት ሲገቡ ይታያል፤ በኋላም ትምህርቱን መዝለቅ አቅቷቸው ሲያቋርጡ መመልከት የተለመደ ነው፤ ይህ የሚያመላክተው በሆነ ምክንያት ተገፍተው በገፍ የሚገቡ አሉ ማለት ነው ብለዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com